የጀሪካኖችን ሰልፍ ያስቀሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች

ቀደም ባሉት ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ይስተዋልባቸው ከነበሩ የሀገራችን ከተሞች እንደሻሸመኔ፣ አርሲ ነጌሌና መሰል ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው:: ውሃ በሚገኝባቸው ጥቂት ቦኖዎችና ጉድጓዶች ረጃጅም የጀሪካን ሰልፎች ተደርድረው ማየት የከተሞቹ የአንድ ወቅት መገለጫ ሆኖ እንደነበር ነዋሪዎቿ ያስታውሳሉ፡፡

የሻሸመኔ ነዋሪና የማህበረሰቡ ተወካይ አቶ አለሙ ጉርሙ እንደሚያስረዱት፤ ‹‹ሻሸመኔ ከተማ ከዚህ በፊት የነበረባትን የውሃ ችግር አሁን ካለው ጋር እናስተያየው ብንል ለመግለጽ ያዳግታል:: ከመሠረቱ በፊት የተዘረጋው የውሃ መሠረተ ልማት 25 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎችን ታሳቢ አድርጎ ነው:: በየጊዜው የሕዝቡ ቁጥር እያደገ ሲሄድ በዚያው ልክ የውሃ እጥረትም መከሰት ጀመረ›› ይላሉ::

ከ15 ቀን እስከ ሁለት ወር ባለው ጊዜ ውሃን በፈረቃ ለማዳረስ ጥረት ይደረግ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: ከተማውን የአህዮች እና የጀሪካን ሰልፍ ያጭናንቀው እንደነበር የተናገሩት አቶ አለሙ፤ ይህን ችግር ለመፍታት የከተማው ሕዝብ በራሱ ፍላጎትና ተነሻሽነት በውሃ ታሪፍ ላይ ጭማሪ በማድረግ ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ እንዲሁም ከሻሸመኔ ከተማ የመጠጥ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት አምስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ አስቆፈረ›› ነው ያሉት:: የሻሸመኔ ሕዝብ አንድ ሆኖ በመሥራቱ አስደሳች ለውጥ እንደተገኘም አቶ አለሙ ይገልጻሉ::

አቶ ባቦ ገልቦ የነጌሌ አርሲ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ እንደሚገልጹት፤ ከዚህ በፊት የነበረውን የኔጌሌ አርሲ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ እቸገራለሁ:: አብዛኛው ነዋሪ 24 ሰዓት ደዳባ ከሚባል ወንዝ ድፍርስ ውሃ በአህያ እያመላለሰ ነበር ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀመው:: ችግሩን ለማስወገድም ሕዝቡ ጥረት ያላደረገበት ጊዜ አልነበረም:: በአንድ ወቅት የሆነ ቦታ ላይ የውሃ ጉድጓድ አስቆፍሮ መጠቀም ጀምሮ ነበር፤ ነገር ግን በጣም ድፍርስና መጠኑም አነስተኛ ስለነበር እንደታሰበው የነዋሪውን ችግር ሊቀርፍ እንዳልቻለ ነው ያስታወሱት::

በወር አንድ ጊዜ እንኳን የማግኘት እድል አልነበረንም:: በዚህም ላይ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ አገልግሎቱም ይቋረጥ ስለነበር:: አሁን በከተማዋ ዳርቻዎች በርካታ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ:: በየሁለትና ሶስት ቀን ልዩነት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ጀምረናል::አንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች እንዲያውም በየቀኑ ያገኛሉ፤ እናም ትልቅ መሻሻል ታይቷል::ነጌሌ አርሲ ከተማ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት አንጻር ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡

እንደ ድሮው በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት አገልግሎቱ ይቆማል ተብሎም አይታሰብም፤ ውሃውን ከጉድጓድ የሚስብና የሚያሰራጭ የሶላር ሃይል ተገጥሟል:: ቀን ከሌት ሠርተው የኔጌሌ አርሲ ከተማ እና አካባቢው የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ላደረጉ ሙያተኞች እና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋና አቀርባለሁ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

‹‹ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ከተማ ነው፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ካምፕ ወደ ሚባል ቦታ ረጅም መንገድ እየተጓዝኩ በእንስራ እና በጀሪካን ውሃ ስቀዳ ኖሬያለሁ›› የሚሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ እጅጋየሁ ደምሴ ናቸው::‹‹ነጌሌ አርሲ ከተማ አረቄ በማውጣትና ከብት በማድለብ የሚተዳደሩ በርካታ ሰዎች ያሉባት በመሆኗ የከተማዋ የውሃ ፍጆታ ከፍተኛ ነው::

አሁን እግዚአብሄር ይመስገን የውሃ ችግራችን ተቃሏል:: እኔም የውሃ ቧንቧ ቤቴ እስከማስገባት በቅቻለሁ:: ይሁንና አቅርቦቱ ቢሟላም አሁንም የጥራት ችግር ይስተዋላል:: ከሰዓት በኋላ ንጹህ ውሃ ይመጣል አንዳንድ ጊዜ ማታና ሌሊት ሲሆን ድፍርስ ውሃ እንቀዳለን:: ከድሮው አንጻር ሲታይ ተመስገን ቢባልም ድርጅቱ የውሃውን ጥራት አሻሽሎ ደስታችንን ሙሉ ቢያደርገው ደግሞ ርካታችን የበለጠ ይሆናል›› ሲሉ ወይዘሮ እጅጋየሁ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

የምዕራብ አርሲ ዞን ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል አብዱሮ እንደሚገልጹት፤ የአካባቢውን የውሃ ችግር ለመፍታት የኦሮሚያ ክልል፣ የምስራቅ አርሲ ዞን እና ወረዳዎች በመቀናጀት በርካታ የውሃ ፕሮጀክቶችን ሠርተዋል:: ህብረተሰቡ እና ሲቪል ማህበራትም የጎላ ተሳትፎ አድርገዋል:: በዚህም አብዛኛውን የዞኑ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል::

እስከ አሁን በተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ከ450 ሺህ በላይ ለሚገመቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ሆኗል::

ውሃውን ወደሚፈለግበት ቦታ ለማድረስ ራሱን የቻለ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር በተሠራው ሥራ በሶላር የመጠቀም ጅምሮች እንዳሉም ተናግረዋል:: በዚህም ከኤሌክትሪክ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ አገልግሎት መስጠት እየተቻለ እንደሆነ አስረድተዋል::

ነጌሌ አርሲን ፣ ሻላን፣ ሻሸመኔን እና ሲራሮን ያስተሳሰረው ይህ ግዙፍ የውሃ ፕሮጀክት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት እንደሆነም ጠቅሰዋል:: የውሃ ሃይልን ወደ አንድ ቦታ በማሰባሰብ እና ረጃጅም ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታዎችን በማድረግ ከፍተኛ የውሃ ችግር ወዳለባቸው ቆላማ አካባቢዎችም በማዳረስ በአጠቃላይ የዞኑን የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከ80 በመቶ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰዋል::አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You