ከ2ሺህ በላይ ኤክስፖርተሮች የቻይናን መስፈርት አሟልተው ምርት መላክ ጀምረዋል

አዲስ አበባ፡- 2ሺህ በላይ ኤክስፖርተሮች የቻይናን መስፈርት በማሟላት የግብርና ምርቶችን እንዲልኩ ማድረግ መቻሉን የግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ።

የግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከ2ሺህ በላይ ኤክስፖርተሮች የቻይናን መስፈርት በማሟላት የግብርና ምርቶችን እንዲልኩ ማድረግ ተችሏል። የላኪዎቹ መረጃም ከሀገራቱ ጋር የሚናበብ መሆኑን ጠቁመዋል።

አምባሳደሩ ተቋሙ ወደ አውሮፓ እና ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ሰሊጥ፣ ቦለቄ እና ቡና የሚልኩ ኤክስፖርተሮችም በመመዝገብ የመላክ ሂደቱን እንደሚከታተልም ገልጸው፤ ተቋሙ ምርቶች ላይ ክፍተቶች ሲገኙ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚከራከር መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሞጎሊያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ የተቀቀለ ስጋ ለቻይና ለማቅረብ እየሠራች ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ የቻይናን ትልቅ የስጋ ምርት ገበያ ለመጠቀም ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የስጋ ምርቷን ቻይና መላክ ከጀመረች ከቻይና የገበያ መስፈርት ጋር ተመሳሳይ ለሆኑት የአውሮፓና ኤዥያ ገበያ ማቅረብ እንደምትችልም ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በቻይና ሀገር የምርት ጥራትና ደህንነት በሚቆጣጠረው ተቋም የሚሠሩ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢትዮጵያን የስጋ አመራረት መመልከታቸውን ተናግረዋል። የቻይናው ተቋም ለኢትዮጵያ የላከው ከአንድ ሺህ በላይ ገጽ ያለው ዶክመንት በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ተሞልቶ መላኩን ገልጸዋል። በቅርቡ ምላሽ ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።

ከበሽታ ነጻ የሆነ የእንስሳት አረባብ ሂደትን ለመከተል እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ የቻይና ገበያ በስፋት ያለው በመሆኑ አሁን ባሉት ቄራዎች ብቻ ፍላጎትን ማዳረስ እንደማይቻል እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቄራዎችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከተቋቋመ ሶስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ተቋሙ በሁለት ዘርፎች ስምንት ቴክኒካል ክፍሎች እና 45 የቁጥጥር ጣቢያዎች እና አራት ማዕከላት እንዳሉት ተናግረዋል።

በሁለቱም ዘርፎች ውጤትን ለማምጣት ተቋሙ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ወደ ዓለም ገበያዎች የሚላኩ ምርቶች ከበሽታ ነጻ እንደሆኑ እና የተቀባይ ሀገራት መስፈርቶችን እንደሚያሟሉ የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርቶቹ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሆነው ሲገኙ የፋይቶ ሰኒተሪ ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በዚህም የ2017 በጀት ዓመት 96 በመቶ የእቅድ ክንዋኔ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በተቋሙ የሚሰጡ 66 አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ከሰው ንክኪ ነጻ እና ዲጂታላይዝድ እንዲሆኑ ተደርጓል። ሰዎች የተቋሙን አገልግሎቶች ሲፈልጉ በበይነመረብ ጥያቄ ማቅረብ እና ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የፋይቶ ሰኒተሪ ሰርተፍኬትም በበይነ መረብ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ ሲላክ የነበረውን የአበባ ምርት የአውሮፓ ህብረት በሰጠው ግብረመልስ መሠረት የሲስተም አፕችን በመከተል የአበባ ኤክስፖርት ንግዱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

የቁጥጥር ሥርዓት አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከ17 በላይ መመሪያዎችን እና ደንቦችን በማውጣት ግማሽ ያህሉን ማጸደቅ ተችሏል። ሙሉ በሙሉ ሲጸድቅም የቁጥጥር ሥርዓቱን መልክ የማስያዝ ሥራ ውጤት የሚኖረው መሆኑንም ገልጸዋል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You