“ኮሪዶር ልማት የክልል ከተሞችን ከእርጅና እየታደገ ነው”- አቶ አብዱ አህመድ የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ

አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ ተጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው ኮሪዶር ልማት የክልል ከተሞችን ከእርጅና እየታደገ መሆኑን በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ አህመድ ገለጹ።

አቶ አብዱ አህመድ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የኮሪዶር ልማት በአዲስ አበባ ተጀምሮ በክልሎች ከተሞች እየተስፋፋ መጥቷል። ልማቱ ከተሞችን ከእርጅና ከመታደግ ባለፈ፤ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እያሳደገ ነው።

አሁን ላይ በቡታጅራ ከተማ የኮሪዶር ልማት ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ያስታወቁት ከንቲባው፤ የልማት ሥራው ከመጀመሩ በፊት ከማህበረሰቡ ጋር ምክክር መደረጉን፤ በእዚህም ከተማዋን ለንግድ፣ ለኑሮ እና ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ማድረግ ላይ መግባባት መፈጠሩን አስታውቀዋል። ይህም ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገው ገልጸዋል።

በከተማዋ የኮሪዶር ልማት የተጀመረው በሁለት ነጥብ ሁለት ኪ.ሜ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብዱ፤ ልማቱ አሁን ላይ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ወደ 25 ኪሎ ሜትር ማደጉን አስታውቀዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ 17 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን የገለጹት አቶ አብዱ፤ በእዚህም የቡታጅራ ከተማን ኢኮኖሚ፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን በተሟላ መልኩ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኮሊዶር ልማቱ ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኮሪዶር ልማቱ የሚሆነውን ቦታ ከመልቀቅ ባለፈ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህም ለሌሎች ፕሮጀክቶች መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ አመልክተዋል።

የቡታጅራ ኮሪዶር ልማት የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ፣ አረንጓዴ ሥፍራ፣ ፓርክ፣ ፋውንቴን፣ ፕላዛ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቦታዎች እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች በውስጡ ያካተተ እንደሆነም አስታውቀዋል፤ አሁን ላይ ከኮሪዶር ልማቱ ስምንት ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትሩ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጠናቀቁ ሥራዎች በተያዘው ወር መጨረሻ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን እና ሌሎቹንም ደረጃ በደረጃ ለአገልግሎት ክፍት የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው፤ በሁለት ዓመት የሚጠናቀቅ እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እየተገነባ የሚገኝ ሁለት ነጥብ ስምንት ኪ.ሜ ርዝመት ያለው መንገድ እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡ የኮሪዶር ልማት እንዲሳካ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ እውቅና የሚሰጠው መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You