ሐምሌ 22፣ 2011 ዓ.ም በመጪው የኢትዮጵያ ትውልድ ውስጥ ለዘመናት የሚዘልቅ አዲስ ሀገራዊ ታሪክ ተመዝግቧል። አረንጓዴው አሻራ።ጥንት በግዙፍ ደኖች የተሸፈነች ብዙ ብርቅዬ የዱር አራዊቶች፤ ምንጭና ፏፏቴዎቿ የነበሯት፤ እጅግ ውብ ሀገር እንደነበረች የጎበኟት የአውሮፓና የአረብ ጸሐፍት በተለያየ ዘመን ከትበዋል።የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የመጀመሪያውም የሰው ዘር መገኛ ነን።
ደኖቻችንን ያጠፋን ያወደምን፤ አራዊቶቻችን መኖሪያ አጥተው እንዲሰደዱ ያደረግን እኛው ነን። መሬታችንን አራቁተን ደን አልባ እንዲሆን፤ በጎርፍ እንዲታጠብ ያበቃነው፤ ለድርቅ ለረሀብ አደጋ ለልመና የተጋለጥነው እኛው ነን። ድንቅና በተፈጥሮ የታደለች ሀገር ይዘን የተራብነው የታረዝነው እኛው ነን።ተፈጥሮ የሰጠችንን ጸጋ ገፈን ከዳቦ ቅርጫትነት ወጥተን፤ ክብራችን ተዋርዶ ወደተረጂነት፤ ራሳችንን በምግብ መቻል ተስኖን ወደተመጽዋችነት የተሻገርነውም እኛው ነን።
ጥያቄው ከዚህ እንዴት እንውጣ ነው።ይሄ መደፈርና ውርደት ተሰምቶት በሁሉም መስክ ሀገርን ለመለወጥ የማይነሳ የማይሰማው ዜጋ ካለ ሕያው ሳይሆን በድን ብቻ ነው የሚሆነው። ዓለምን የሞላነው የሰውን ሀገር ያጣበብነው እኛ ሆነን ሳለን እዚህ ሀገራችን ውስጥ በሰላም መኖር ተስኖን እንባላለን። ድንቁርናችን ከጣሪያ አልፎ እንጠፋፋለን፤ እንገዳደላለን።
ከመንደሬ ውጣ ልቀቅ የምንል የዘቀጥን መንደርተኞች ሆነናል። ከመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ቢባል የሌለንበት የዓለም ሀገር የለም።በሰው ሀገር እንደልብ እየተኖረ እዚህ በጎጥና በጎሳ መባላት ማለት ምንኛ የረከሰ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ከእኛም አልፎ ለሌሎች ትበቃለች። ያነሰን መልካምነትና በጎነት እንጂ መሬት አልጠበበንም።የሚበጀን ሀገራችንን እያለማን በፍቅር በሰላም ተቻችለን ተከባብረን መኖር ብቻ ነው። ሌላውም ዓለም እንዲሁ ነውና፡፡
ይሄን ሁሉ የገዘፈ ችግር አዝለን በደነቆረ ኋላቀር የጎጥ ፖለቲካ መናቆርና መባላታችን ለመጠፋፋት እያቅራራን መገኘታችን በዓለም ፊት አሳፋሪና አዋራጅ ሆኖ እየታየ ነው። ሀገርን ማልማት ማሳደግ ሰላሟን መጠበቅ ወደቀደመው የተፈጥሮ ልምላሜና ጸጋዋ ወደ ታላቅነቷ ለመመለስ ሁሉም ዜጋ በጋራ መቆም አለበት።
ከቀደሙት ዓመታት ልቆ በገዘፈ መልኩ የተከወነው የአረንጓዴው አሻራ ብሔራዊ ዘመቻ በአንድ ጀምበር መላው ኢትዮጵያዊ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወጥቶ ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሉ የኢትዮጵያውያንን ታላቅ አንድነትና ሕብረት ማሳያና ማረጋገጫ ነው። ድፍን ዓለምንም አስደምሟል። ታላላቅ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃንም ይሄንኑ እውነት አስተጋብተዋል።
ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሰኞ ችግኞችን ተከለች፤ የመንግሥት ባለስልጣናት የዓለምን ሪከርድ ይሰብራል ማለታቸውን ዘግቧል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ግዙፍ ተነሳሽነት ዒላማ ያደረገው የሀገሪቱ መልክአ ምድር እንዲያገግም ሲሆን ኤክስፐርቶች መሬቱ በደኖች መመናመንና በአየር ንብረት ለውጥ በፈጣን ሁኔታ እየተሸረሸረ መሆኑን ይናገራሉ ብሏል ዘገባው፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ ዘመቻው ሰኞ ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ትዊት እንዳደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በደቡብ ክልል ችግኝ ይተክላሉ ማለቱን ዋሽንግት ፖስት አስነብቧል።
ኢትዮጵያ በዚሁ ፕሮግራም ከግንቦት እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳለች። የግብርና ባለስልጣናት በመላው ሀገሪቱ ከ2.6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን በመግለፃቸውን አስታውሶ ዘግቧል ዋሽንግተን ፖስት፡፡
ፋርም አፍሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ በደን ልማትና አስተዳደር ሥራ ተሰማርቶ የሚሠራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በደን የተሸፈነ መሬት አነስተኛ መሆኑን ገልፆ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ 30 በመቶ የነበረው ደን በከፋ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል ይላል ዋሽንግተን ፖስት። በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር የእርሻ ቦታ ጥያቄው እየጨመረ መምጣት፤ ደንን ያለአግባብ መጠቀም፤ የአየር ንብረት ለውጥ ለደኖች በፍጥነት እያሽቆለቆለ መሄድ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብሏል ዘገባው።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን፤የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የንግዱ ማሕበረሰብ በችግኝ ተከላው የተሳተፉ ሲሆን ሕንድ በ2017 (እኤአ) በአንድ ቀን 66 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የያዘችውን ሪከርድ ኢትዮጵያ ሰብራለች።የጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ የኢትዮጵያን ችግኝ ተከላ ይከታተለው እንደሆነ እስከአሁን አልታወቀም ሲል ዘግቧል ዋሽንግተን ፖስት።
የሲኤንኤን ዘጋቢ ሸሪፍ ፓጌትና ሄለን ሬገን ኢትዮጵያ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በ12 ሰዓታት ውስጥ ተክላለች፤ ባለስልጣናት የዓለምን ሪከርድ እንደያዘ ያምናሉ ብሏል በዘገባው። ይህ ግዙፍ የችግኝ ተከላ በብሔራዊ ደረጃ የተራቆተውን ደን በስፋት ለመተካት እንዲቻል ‹አረንጓዴ አሻራ› በሚል የተሰየመው ዘመቻ የሚመራው በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ግንባር ቀደምትነት ነው።በመላው ሀገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመቻ እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረጋቸው በስድስት ሰዓታት ውስጥ 150 ሚሊዮን ችግኞች መትከላቸውን በትዊታቸው ገልጸዋል።
ጠ/ሚሩ ከግባችን ግማሹን ደርሰናል በማለት አስታውቀው በቀሪዎቹ ሰዓታት ችግኝ ተከላውን እንዲቀጥሉ አበረታተዋል። በ12 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገና ወደ ትዊተር ገጻቸው ተመልሰው ኢትዮጵያ የጋራ የሆነውን አረንጓዴ አሻራ ግብ ማሳካት ብቻ ሳይሆን አልፋው ሄዳለች ማለታቸውን ሲኤንኤን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በአጠቃላይ 353,633,660 ችግኞች መተከላቸውን በትዊተር ገጻቸው መግለጻቸውን ያስታወቀው ሲኤንኤን በ2017 ሕንድ 1.5 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት በ12 ሰዓታት ውስጥ 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለምን ሪከርድ ይዛ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቧን ዘግቧል።
ባሕር በር አልባ የሆነችው ሀገር በአየር ንብረት ለውጥ ትሰቃያለች። የመሬቱ መጎዳት፤ የአፈር መሸርሸር፤ የደን መመናመን፤ ተደጋጋሚ ድርቅ፤ በእርሻ ላይ የሚከሰት ጎርፍ በተደጋጋሚ አጋጥሟታል ይላል የሲኤንኤን ዘገባ፡፡
የአፍሪካን ደን መልሶ ለመተካት እንዲቻል 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ደን ለማልበስ የተያዘውን ፕሮግራም ከ20 ሀገራት በላይ የፈረሙ ሲሆን ኢትዮጵያም ተቀላቅላለች። በቅርቡ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው የዓለምን የጠፉ ደኖች መልሶ እንዲተኩ ለማድረግ በሰዎች እንቅስቃሴ ምክንያት የተከሰተውን 2/3 ኛውን የዓለም ሙቀት መጠን ያስወግዳል።
ጥናቱ የተካሄደው በስዊስ ዩኒቨርሲቲ ዙሪክ ተመራማሪዎች ሲሆን በስሌቱ መሰረት በመላው ዓለም የጠፉ ደኖች እንዲተኩ ከተደረገ በአጠቃላይ 205 ቢሊዮን ቶን ካርቦንን ማስቀረት ይችላል።በዓለም ደረጃ ያለው የካርቦን ስርጭት መጠን በየዓመቱ 10 ቢሊዮን ቶን ይደርሳል ብሏል ሲኤንኤን።
ሜትሮ ኒውስ በበከሉ ኢትዮጵያ 350, ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ውስጥ በመትከል የዓለምን ሪከርድ ሰበረች ሲል ዘግቧል።ጀምስ ሆካደይ ኢትዮጵያ ሕንድ የያዘችውን ሪከርድ በብዙ እጥፍ እንደምታልፍ ይጠበቃል ብሎ ነበር።
አረንጓዴ አሻራ በሚል የተጀመረው ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አንድ ሺ ጣቢያዎች ይካሄዳል፤ በዕለቱ የመንግሥት ሠራተኛው በችግኝ ተከላው እንዲሳተፍ በማሰብ አንዳንድ የሕዝብ ቢሮዎች መዘጋታቸውን ሜትሮ ኒውስ አስታውሷል።ሰኞ ማለዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል።በእቅድ የተያዘው 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ሲሆን እስከ አሁን 2.6 ቢሊዮን ችግኞች በመላው ሀገሪቱ መተከላቸውን የችግኝ ተከላው አስተባባሪ ኮሚቴ መግለጹን ዘገባው አስፍሯል።
የእንግሊዙ ታዋቂ ጋዜጣ ዘ- ኢንዲፔንደንት ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ 350 ሚሊዮን ችግኞችን ተከለች ሲል ዘግቧል።ለምሳሌም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ20ኛው ክፍለዘመን ቀደም ብሎ 30 በመቶ ማሽቆልቆሉን በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ 4 በመቶ ደን ብቻ መኖሩን ገልጹዋል። ዘ ጋርድያን ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 353 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የዓለምን ሪከርድ ይዛለች ብሏል። በችግኝ ተከላው ከሕዝቡ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት፤የአፍሪካ ሕብረትና በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ኤምባሲዎች ሠራተኞች መሳተፋቸውን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2011
ወንድወሰን መኮንን