
አዲስ አበባ፡– ጂኦ ፓርኮችን ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያዎች አስተዋፅኦ እና የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ገለፁ።
ጂኦሎጂስት እና በቦትስዋና እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አስፋወሰን አስራት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ የጂኦፓርክ ዋና ዓላማ ለዓለም ማስተማሪያ የሚሆኑትን ቦታዎች ጠብቆ ማቆየት ነው ፤ ከመጠበቅ ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ከሀብቱ መጠቀም እንዲችል አድርጎ ማቋቋም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም ላይ በሥነ ምድር ሀብት እጅግ ከሚታወቁት ሀገራት መካከል አንዷ ናት ያሉት ፕሮፌሰር አስፋው፤ ስምጥ ሸለቆው ሰንጥቋት የሚያልፍበት እና የመሬትን አፈጣጠር ብዙ ሳንርቅ የምናይበት ቦታ አላት ብለዋል።
የሶፍዑመር ዋሻ፣ የገረዓልታ ተራሮች ፣ ወንጪ፣ ዓፋር እና ደንክል እስከ ኦሞ ድረስ እና ሌሎች የስምጥ ሸለቆ ቦታዎች ሁሉም የጂኦፓርክ መሆን የሚችሉ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የቱሪዝም ሚንስቴር እና በዙሪያው የሚሠሩ ምሁራን እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ መጠቀም እንዲችል የማስተዋወቅ ሥራ እና የቱሪስቱ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም በተደራጀ መልኩ ምቹ የሆነ ማቆያ እንዲኖር ማስቻል የግድ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ሀገራችን ውስጥ ያሉት ጂኦፓርኮች ዓለም አቀፍ እይታ የሚያገኙ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ሆኖም ግን ታች ድረስ ከማህበረሰቡ ጋር መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል። የቱሪዝም ሚንስቴር እና የማህበረሰቡ ውህደት ከባለሙያው ጋር ሲጣመር ጥሩ ውጤት ያመጣል ሲሉም ተናግረዋል።
የጉዞ እና ጉብኝት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ ያላት የጂኦፓርክ አቅም በአዋጅ እንዲቋቋም በማድረግ መሠረት ያለው ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤ ብዙዎቹ የጂኦቱሪዝም ቦታዎቻችን የመሠረተ ልማት ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፤ በመሆኑም ይህን በመፍታት የምስራቅ አፍሪካ ጂኦፓርክን ለማስተሳሰር የባለሙያው አብሮ መምከር የሚያመጣው ውጤት ይኖራል ሲል ገልጿል።
በሀገራችን የጂኦ ቱሪዝም ሀብት እጅግ በርካታ ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዓለም የአፍሪካ ከፍተኛ ተራሮች የሚገኙባት እና እስከ ከፍተኛው ዝቅተኛ ቦታ ድረስ በውስጥዋ ያላት ሀገር ናት ያለው ጋዜጠኛ ሄኖክ ፤ እስከ አሁን ስንዘፍን እና ስንቀኝ የነበረው ‹‹ሀገሬ ኢትዮጵያ መልክአ ምድርሽ ተራራሽ እያልን ነው ›› ይህ ማለት ስለጂኦቱሪዝም እያወራን እና ያለንን እያደነቅን ነው፤ ነገር ግን ነገሩ ጉዳይ ሳይሆን ቆይቷል፤ በኤርታሌ ዳሉል በምንለው አካባቢ ያለው አቅም መጠቀም ከጀመርን በጣም ጥቂት ጊዜ ነው ሲል ተናግሯል።
በዚህ ዙሪያ ብዙ የደከሙ ሰዎች መኖራቸውን በመጠቆም፤ እንደ ጂኦቱሪዝም ባለሙያዎች እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉት የጂኦሎጂ ምሁራን ያሉንን ሀብቶች በማውጣት ተራሮች እና የስምጥ ሸለቆዎች ትርጉም ያላቸው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ በሳይንሳዊ ጥናት ያገዙንን በርካቶችን ሳናመሰግን አናልፍም ብሏል።
ባሌ እና ሰሜን ተራሮች ያላቸውን ያክል አቅም ብዙ እንግዳ እያስተናገዱ አይደለም ያለ ሲሆን፤ በተለይ የአፍሪካ ጎረቤቶቻችን ካላቸው የውድድር አቅም አኳያ ያለን ነገር እና የመጣንበት መንገድ የሚመጣጠን ባለመሆኑ የሚያስቆጭ ነው ብሏል።
የጉዞ ጋዜጠኛ ሄኖክ ፤ ከዩኔስኮ እና ልምዱ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት የሚደረገው ውይይት እንዲሁም የእኛ የቱሪዝም ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች አብሮ ለመሥራት የሚተልሙት ትልም ወደፊት ትልቅ ዕድል ይዞ ይመጣል ይላል። ይህን ለማፋጠን እና ውጤታማ ለማድረግ በተለይ በክልሎች ባሉ መዳረሻዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አደረጃጀት መዘርጋት ያስፈልጋል ሲል አስረድቷል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም