በክልሉ በዘጠኝ ወራት፡- 138 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል

-33 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት 138 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 33 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ማጎልበት በመቻሉም በርካታ የክልሉ ሕዝቦች ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን አመልክቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የእርሻ ሆርቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለም ይርጋ ወልደሥላሴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ 146 ሺህ ሄክታር በመስኖ በማልማት 35 ነጥብ 5 ሚሊዮን ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገው ርብርብም 138 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የተቻለ ሲሆን ከዚህም 33 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።

አጠቃላይ ከለማው መሬት ውስጥም 40 በመቶ የሚሆነው በኩታ ገጠም (በክላስተር) የለማ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በዋና ዋና ምርት የለሙ የመስኖ ምርቶች መካከልም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የአትክልት ልማት መሆኑንም አስታውቀዋል።

እንዲሁም ስራስር፣ ፍራፍሬና ስንዴ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ጠቁመው፤ ለውጤቱ መገኘትም በተለይም ክልል አቀፍ የውይይትና የንቅናቄ መድረኮች መዘጋጀታቸውና ፈፃሚውን የክህሎት ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራዎችን መሠራታቸው ነው›› ብለዋል።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም በክልላችን የማዳበሪያ አቅርቦት ከፍተኛ የሆነ ችግር የሚታይበት ነው። በዚህ ምክንያት የቀረበውም ማዳበሪያ በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ስለሆነ አርሶ አደሩ በተገቢ ሁኔታ አያገኝም ነበር። በዚህ ዓመት ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደሀገር በተሠራው ሥራ የሚያበረታታ ውጤት መምጣት ችሏል። መሠረታዊ በሚባል መልኩ በአቅርቦቱና በስርጭት ላይ በተሠራው ሥራ አሁን ላይ የማዳበሪያ ጥያቄ እጥረት ሆኖ የሚነሳበት አንድም አካባቢ የለም ነው ያሉት።

በተለይም በማዳበሪያና የዘር አቅርቦት ረገድ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል። ‹‹በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመስኖ፤ ለበልግና ለመኸር እንዲቀርብልን ጠይቀን ተፈቅዶልናል፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች ቀርቦ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል›› ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ለመስኖ ልማት የዋለው ከ180 ሺህ ኩንታል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዘንድሮ የመስኖ ልማት ሥራ 460 ሺህ የሚደርሱ የክልሉ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውንና መካናይዜሽን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል። ምርቱን ከማምረት ጎን ለጎን የክልሉ መንግሥት ለገበያ ትስስርና ሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የተመረተው ምርት የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት መደረጉን አስገንዝበዋል።

በክልሉ በስፋት የሚመረተው አትክልትና ፍራፍሬ እንደመሆኑ የማቆያና የገበያ ሰንሰለት በመዘርጋት የተመረተ ሰብል ሳይበላሽ ወደ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ መፈጠሩንም አስረድተዋል። ‹‹በተለይ ከፌዴራል ባገኘናቸው ድጋፎች በስፋት የመስኖ ምርት የሚመረትባቸው አካባቢዎች ብልሽትን ለማስቀረት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ሞዴል የማቀዝቀዣ መጋዘኖችን ለመገንባት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ለክልሉ የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ውጤታማነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹በክልላችን ከታህሳስ ወር ጀምሮ የተግባቦት መድረክ አዘጋጅተን፤ የበልግ የንቅናቄ መድረኮች በማካሄድ በቀጥታ ወደ ሥራ ገብተናል›› ብለዋል።

በዚህም ዓመታዊ ሰብሎች አዝዕርትና አትክልት ብቻ 363 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈኑን፤ የቋሚ ሰብሎችን ጨምሮ እስከ አሁን ባለው እንቅስቃሴ በዓመታዊ ሰብሎች 378 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱንና 341 ሺህ 436 ሄክታር መሬት ወይም የእቅዱን 66 በመቶ በዘር መሸፈን መቻሉን አብራርተዋል።

በክልሉ የበልግ ወቅት ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መድረሱን አቶ ዓለምይርጋ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ በተለይ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በማጎልበት ‘’ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር’’ በሚል በተጀመረው ንቅናቄም በርካታ አርሶ አደሮች ከርዳታ መውጣትና ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል።

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግና ከተረጂነት ለማላቀቅ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል። ‹‹በተለይ በስራ ስር ሰብሎች፣ በአትክልት ሰብሎች፣ በአዝዕርት ሰብሎች እንዲሳተፍ ለይተን እየደገፍን በመምጣታችን በርካታ አካባቢዎች ላይ ተጨባጭ የሚባሉ ለውጦች እየመጡ ነው” ብለዋል። በዚህም አርሶ አደሯችንም በዘርፍ መጠቀም የጀመረበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You