
አዲስ አበባ፡- ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ከፖለቲካ ፓርቲነት መሠረዙን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ከፖለቲካ ፓርቲነት መሠረዙን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከዚህ ቀደም ህ.ወ.ሓ.ት በዐመጻ ድርጊት በመሣተፉ ምክንያት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሠረዙ የሚታወስ ነው። ይሁንና የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተደረገ በኋላ የህ.ወ.ሓ.ት ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ የተላለፈው ውሣኔ እንዲነሣ ቦርዱን ሚያዝያ 13 እና ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም መጠየቁን መግለጫው አትቷል።
ሆኖም ቦርዱ በዐመጻ ድርጊት በመሣተፍ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሠረዘ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነቱ ከተሠረዘ በኋላ ሕጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ የሚያስችል ሕግ ስለሌለ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/1155 በተጻፈ ደብዳቤ መልስ መስጠቱን በመግለጫው አስታውሷል።
የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መታወጁን ተከትሎ ህ.ወ.ሓ.ት በአዋጁ መሠረት “በልዩ ሁኔታ” ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ መቅረብ የሚገባቸውን ሠነዶች በማያያዝ ባቀረበው ጥያቄ እንዲሁም ህ.ወ.ሓ.ትን አስመልክቶ የፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር ፍሚ 1/1345 በጻፈው ደብዳቤ |መነሻ ህ.ወ.ሓ.ት ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበትን ሕግ መሠረት በማድረግ ቦርዱ በማሻሻያ አዋጁ መሠረት ፓርቲውን “በልዩ ሁኔታ” መዝግቦ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰጥቷል ነው ያለው።
ሆኖም ህ.ወ.ሓ.ት ምዝገባውን ተከትሎ እንዲፈጽም የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ማሳሰቢያ ቢሰጥም ፓርቲው ግን በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አልፈጸም ያለው የቦርዱ መግለጫ፤ ከዚህም በላይ በአዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት የፓርቲውን ሕጋዊነት የሚያረጋግጠውንና በወቅቱ አምኖበትና ተስማምቶ ከቦርዱ የተቀበለውን የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ አላውቅም፤ ሕጋዊ ሰውነቴ በዚህ ሠነድ አይረጋገጥም በማለት ሕግንና መመሪያን ባለማክበርና ለማክበርም ፈቃደኛ ባለመሆን ሲገልጽ ቆይቷል ብሏል።
ቦርዱ በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትና ፓርቲው ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታ እንዲወጣ ለማድረግ በተለያየ ወቅት በጽሑፍ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ቢቆይም፤ ፓርቲው ግዴታውን ባለመወጣቱ ቦርዱ “የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1332/2016 እና አዋጁን ተከትሎ በወጣው መመሪያ ቁጥር 25/2016 መሠረት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይጠብቅ ፓርቲውን መሠረዝ የሚያስችል የሕግ መሠረት ቢኖረውም፤ ፓርቲው ግዴታውን እንዲወጣ ዕድል ለመስጠት ቦርዱ ፓርቲውን ለሦስት ወራት ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ በማገድ ፓርቲው የዕርምት እርምጃ በመውሰድ በሕጉ መሠረት ግዴታውን እንዲፈጽም ቦርዱ ጥረት ቢያደርግም ፓርቲው ተጣለበትን የሕግ ግዴታ ለመወጣት ፈቃደኛ አልሆነም ሲል ገልጿል።
በመሆኑም ቦርዱ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በቁጥር አ1162/11/15421 በተጻፈ ደብዳቤ ተራ ቁጥር 3 ላይ በተጠቀሰው የቦርዱ ውሣኔ ላይ ፓርቲው በሦስት ወር እግድ ጊዜ የእርምት እርምጃ ሳይወስድ ቢቀር በአዋጅ ቁጥር 1332/16 አንቀጽ 3(11) (ሐ) እና በመመሪያ ቁጥር 25 /2016 አንቀጽ 19(1)(ሐ) መሠረት ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲውን ምዝገባ እንዲሠረዝ ቦርዱ በወሠነው መሠረት ፓርቲው የዕርምት እርምጃ ባለመውሰዱ ቦርዱ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ፓርቲው ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሠረዘ መሆኑን ወስኗል ብሏል።
ሄርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም