ፓኪስታን በኒውክሌር ጦር መሣሪያዋ ላይ የሚወስኑትን ባለሥልጣኖቿን ለስብሰባ ጠራች

ፓኪስታን በሕንድ የአየር መከላከያ ሥርዓት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካሳወቀች በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሯ የሀገሪቱን ከፍተኛውን ወታደራዊ ውሳኔ የሚያሳልፈውን ቡድን ለስብሰባ ጠሩ። ፓኪስታን ከሰዓታት በፊት እንዳስታወቀችው በተለያዩ የሕንድ ይዞታዎች ውስጥ የሚገኙ የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ እና የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በተጨማሪም የከባድ መሣሪያ መተኮሻዎች እና ማከማቻዎች መመታታቸውን የፓኪስታን ወታደራዊ ኃይል አስታውቋል።

ከቀናት በፊት ሕንድ በፓኪስታን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ሁለቱም ሀገራት የአጸፋ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃቶች እየፈጸሙ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ትናንት[ቅዳሜ] ማለዳ ሕንድ እና ፖኪስታን በሚዋሰኑበት የካሽሚር አካባቢዎች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘገባዎች ያመለከቱ ሲሆን፣ ዘጋቢዎች ሕንድ በምታስተዳድረው ካሽሚር ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን አረጋግጠዋል።

ሌሎች መገናኛ ብዙኃንም ፓኪስታን ጥቃት ፈጸምኩባቸው ያለቻቸው የሕንድ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በሚገኙባቸው የካሽሚር ክፍሎች ውስጥ ፍንዳታ መሰማታቸውን ዘግበዋል። የሕንድ ጦር ሠራዊትም ፓኪስታን ድሮኖችን እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀም በምዕራባዊ የሕንድ ድንበር አካባቢ ጥቃት መፈጸሟ “አደገኛ ሁኔታን የሚያስከትል ነው” ሲል አስጠንቅቋል።

የፓኪስታን ጦር በበኩሉ በሕንድ ይዞታዎች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ ሕንድ በአየር ኃይል ሰፈሮቹ ላይ ለፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት አጸፋ መሁኑን ቢገልጽም፤ ሕንድ ግን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ያለችው ነገር የለም። ለዘመናት በፍጥጫ ውስጥ የቆዩት ሕንድ እና ፓኪስታን ኒውክሌርን ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቁ ሠራዊቶች ያሏቸው ሲሆን፣ ግጭቱ ተባብሶ ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት ተፈጥሯል።

ትናንት ቅዳሜ ማለዳ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የፖኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በሀገሪቱ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጠውን ‘የብሔራዊ ዕዝ ባለሥልጣንን’ ለስብሰባ ጠርተዋል። ይህ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናትን ያካተተ ሲሆን ፓኪስታን ያሏትን የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች በተመለከተ እና በሌሎች ወሳኝ የሀገሪቱ የደህንነት ጉዳዮች ላይ በመምከር ለሠራዊቱ ትዕዛዝ የሚያስተላለፍ አካል ነው።

በሕንድ እና ፓኪስታን መካከል ያለው ውጥረት የተባባሰው ከሁለት ሳምንት በፊት ሕንድ በምትቆጣጠረው የካሽሚር ክፍል ውስጥ ከ20 በላይ ቱሪስቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ሕንድ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ የበቀል ጥቃት በፓኪስታን ይዞታዎች ላይ መውሰድ ስትጀምር ነው። ባለፉት ቀናት ሁለቱም ሀገራት አንዳቸው ሌላኛውን በድሮን እና በከባድ መሣሪያ ጥቃት በመፈጸም ሲከሱ የቆዩ ሲሆን እስካሁን ከሁለቱም ወገን ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው እየተዘገበ ነው።

በሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ ሀገራት መካከል ባለፉት ቀናት እየተባባሰ ያለው ግጭት እንዲረግብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ለፓኪስታን ጦር ሠራዊት እና ለሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስልክ በመደወል መወያየታቸውን እና ሀገራቱ ውጥረቱን እንዲያረግቡ መጠየቃቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ሩቢዮ በሀገራቱ መካከል ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይፈጸሙ የሚያስችል “ገንቢ ንግግር” እንዲያደርጉ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ እንደምትፈልግ አሳውቀዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You