ኢትዮ ኤሌክትሪክ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና አሸናፊ ሆነ

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከሚያዝያ 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ሻምፒዮና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት፣ በዚህ ውድድር በሁለቱም ፆታ በቀጣይ ኢትዮጵያ የምትወዳደርባቸውን አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ብሔራዊ ቡድንን የሚወክሉ አዋቂና ታዳጊ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ሂደት ጠንካራ ስፖርተኞችን ማፍራት ተችሏል። ለዚህም ውድድር ስኬት አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት በተለይ በተጋባዥ እንግድነት ለተገኘው ትግራይ ክልል ጠረጴዛ ቴኒስ ቡድንና በእንግድነት እንዲገኙ ጥሪ ላደረጉት አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ቡድንን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ክለቦች በየጊዜ በሚያስመዘግቡት ውጤት (በደረጃ) ይመረጣሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ከዚህ በፊት የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን ከመቅረፍ ባሻገር በክለቦች መካከል ጤናማ ውድድር በመፍጠር የውድድሩን መርሐ ግብርን ያነቃቃል፤ ፍትሐዊነቱንም ይጨምራል ብለዋል።

ውድድሩ በሁለቱም ፆታ በታዳጊ ከ18 ዓመት በታች፣ ከ18-24 ዓመትና በአዋቂ ከ24-40 ዓመት ሲፎካከሩ የቆየ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የአጠቃላይ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

በማጠቃለያው መርሐ-ግብር ውድድሩን ለመሩት ዳኞች፣ ለተሳታፊ ክለቦችና ቡድኖች፣ ለኮከብ አሠልጣኞች፣ ለኮከብ ስፖርተኞች እና ምስጉን ዳኛ የምስክር ወረቀትና የብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በውድድሩ ለአሸናፊ ተወዳዳሪዎችና ክለቦች የሜዳሊያ እና ለውድድሩ አሸናፊ ስፖርተኞችና ክለቦች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ የትግራይ ክልል ስፖርት ክለብ ለወደፊቱም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀርብ እና በክልሉ ስፖርቱ እንዲነቃቃ በልዩ ሁኔታ ልዩ ልዩ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጎላቸዋል።

ሻምፒዮናውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በውድድሩ ሦስት ዋንጫ፣ ሦስት የወርቅ፣ አንድ የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሻምፒዮናው የታዳጊዎች ምድብ በበላይነት አጠናቋል።

አካዳሚው በሻምፒዮናው 5 ወንድ እና 5 ሴት በድምሩ 10 የጠረጴዛ ቴኒስ ሠልጣኞችን በታዳጊዎች ምድብ በማሳተፍ በሴቶች ከ18 ዓመት በታች የቡድን የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን፣ በወንዶች ከ18 ዓመት በታች በተመሳሳይ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

ሌላው በወንዶች ነጠላ ውድድር ደግሞ ዳንኤል ፋንታዬ 1ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የጨዋታው ኮኮብ ሆኖ በመመረጥ የገንዘብ፣ የዋንጫ እና ወርቅ ተሸላሚ ሲሆን፣ ቶማስ አስማማው ብር እና ለይኩን ኤፍሬም ነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በነጠላ ሴቶች ደግሞ ታሪኳ አገኘው የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን የቻለች የአካዳሚው ሠልጣኝ ነች።

በሻምፒዮናው በታዳጊዎች ምድብ አሸናፊ የሚሆኑ ስፖርተኞች በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም በናይጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ የታዳጊዎች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ብሔራዊ ቡድን አባላት እንደሚመረጡ በውድድሩ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሲሳይ ዮሐንስ መናገራቸው ይታወሳል።

ከሻምፒዮናው መጠናቀቅ በኋላ የአካዳሚው ጠረጴዛ ቴኒስ አሰልጣኝ ኤደን ተስፋዬ በሰጡን አስተያየት፣ ሠልጣኞቹ በውድድሩ መሳተፍቸው ለብሔራዊ ቡድን እንዲመረጡ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላቸዋል ያሉ ሲሆን፣ አካዳሚው ሁልጊዜ የታዳጊዎች ምድብን በበላይነት በማጠናቀቅ ተተኪዎችን በብዛትና በጥራት እያፈራ መሆኑን አስታውሰዋል። በአዋቂዎችም ምድብ አብዛኞቹ አሸናፊዎች የአካዳሚው ፍሬዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል። በመጨረሻም አሠልጣኙ ምንም እንኳን አካዳሚው በሥልጠናና ውድድር ውጤታማ ቢሆንም ከፍተኛ የማሠልጠኛ ቁሳቁስ ችግር እንዳለባቸው በመግለፅ ሥልጠናውን ለማስቀጠል ግን ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው አበክረው አሳስበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You