
– በወጪ እና ገቢ ንግዱ ላይ ያሉ ብልሹ አሠራሮች በጥናት ተለይተዋል
አዲስ አበባ:- የንግድ እና ቀጣናዊ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሙስናን ለመዋጋት ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር “የገቢና የወጪ ንግድ እና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር አፈፃፀም ለሙስና ብልሹ አሠራር ያለው ተጋላጭነት” ላይ ያተኮረ ጥናት መነሻ በማድረግ ከሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር ትናንት ውይይት ተደርጓል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በአሠራር ሥርዓት ላይ ለሙስና በር ከፋች የሆኑ ጉዳዮችን ላይ በማጤን መፍትሔ መስጠት ይገባል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በጥናቱ የተገኙ ብልሹ አሠራሮችን ለመዋጋት ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
በጥናቱ የተገኙ ግኝቶችን ተቀብለን ከሙስና ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ ነን። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ እጅ መንሻዎች በየስፍራው መስፋፋታቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል ብልሹ አሠራር ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የተጠሪና የቅርንጫፍ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ላይ ርምጃ በመውሰድ ቀዳሚ መሆኑንም ገልጸዋል።
“ሀገሬን አልሰርቅም” የሚል ትውልድ ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሥራት ይገባቸዋል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም በቀጣይ ጥራት ደረጃ አሰጣጥ ላይ ጥናት ቢያደርግ የአገልግሎት ጥራት አሰጣጣችንን ለማስተካከል ይረዳልም ብለዋል፡፡
የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከሙስና ጋር በተያያዘ የማስተማር፣ የመከላከልና ርምጃ መውሰድ ላይ አትኩሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማት የአሠራር ሥርዓት ላይ ጥናት በማድረግ የሙስና እና ብልሹ አሠራሮች ሲኖሩ ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የሕግ ርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
በእለቱም ኮሚሽኑ ያጠናው ጥናት የቀረበ ሲሆን የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው የዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋን መሠረት በማድረግ ወቅታዊ የዋጋ ማስተካከያ በየጊዜው የሚደረግ አለመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ለማፋጠን ጉቦ መጠየቅ፣ የውጭ ምንዛሪን በመንግሥት ክልከላ ወይም እገዳ በተደረገባቸው ምርቶች ላይ ወጪ ማድረግና ድንበር ላይ ለሚገኙ ሀገራት ምርት በመሸጥ ምንዛሪ ማግኘት የሙስና ተጋላጭነትን መጨመራቸው ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም እሴት በማይጨመሩ ምርቶች ኢምፖርት ለማድረግ ምንዛሪ ማውጣት፣ በድንበር ላይ ሕገ ወጥ ምርቶችን በሕገወጥ መንገድ መሸመት፣ በመተማ፣ ቋራ እና ሌሎች አካባቢዎች ሰሊጥን በሕገ ወጥ መንገድ የማሻገር ችግሮችን ተከታትሎ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲገቡ የማድረግ አካሄድ ማነስ፣ ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት በቅንጅት የመሥራት ችግር፣ የሕግ ጥሰቶችን ለማረም የሚወስደው የቅጣት መጠን ተመጣጣኝ አለመሆኑ እና ሠራተኞች ተገቢውን መረጃ በተገቢው ጊዜ አለመስጠት እንዳለ ተነግሯል።
በጥናቱም በምክረ ሃሳብነት የቀረበው የዓለም ገበያን ዋጋ መሠረት በማድረግ ተመንን በወቅቱ ማስተካከል፣ የውጪ ንግድ ምርቶች የሚፈቀደው ብድር ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ፣ ኮንትራት ፋርሚንግ ሊሰጥ የሚገባውን ጠቀሜታ እንዲሰጥ ለማድረግ በትብብር መሥራት፣ በየጊዜው የሚፈጸሙ የሕግ ጥሰቶችን ለማረም በቅንጅት መሥራት፣ የውጭ ምንዛሪ አሠራርን ማጠናከር፣ ዋጋ ሳይለጥፉ የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ እና ቁርጠኝነት ያለው የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ተመላክቷል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም