በልምድ ለተገኙ ክህሎቶች እውቅና መስጠት የዜጎችን አቅም በቀጣይነት ለማሳደግ ያግዛል

አዲስ አበባ:- በልምድ ለሚገኙ ክህሎቶች እውቅና መስጠት የዜጎችን ክህሎት በቀጣይነት ለማሳደግና ሀገሪቷ የሰው ኃይሏን እንድታደራጅ የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር አካል የሆነው የፓናል ውይይት “በልምድ የተገኘ ክህሎትን እውቅና መስጠት” በሚል ርዕስ ትናንት ሲካሄድ፤ ሚኒስቴሩ በልምድ የተገኙ እውቀቶችና ክህሎቶችን እውቅና በመስጠት የዜጎችን ክህሎት በቀጣይነት ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል። ዜጎች በልምድ ያዳበሯቸው በርካታ እውቀቶች ቢኖሩም ለእነዚህ እውቀቶች እውቅና ባለመሰጠቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው እንዳይሠሩ ማድረጉን ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም ሚኒስቴር መሠሪያ ቤቱ አንድ ዜጋ ቢያንስ የአንድ ሙያ ባለቤት መሆን አለበት የሚል ኢንሼቲቭ በመቅረጽ ወደ ሥራ መግባቱንና ለ30ሺህ ዜጎች ምዘና መደረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም ይህን ቁጥር ወደ ሚሊዮኖች ለማሳደግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው እውቀትና ክህሎት በመደበኛም ሆነ በኢ-መደበኛው መንገድ ሊያገኝ ቢችልም በኢ-መደበኛ የተገኘው ክህሎት እውቅና አግኝቶ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። አሁን ላይ ግን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በልምድ የተገኙ ክህሎቶች የሚመዘኑበት አሠራር መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም አንዳንድ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን የማሠልጠንና እንዲመዘኑ የማድረግ ሂደት መጀመራቸውንና ከተቋማቱ ባለፈም ግለሰቦች አመልክተው የሚመዘኑበት ዕድል መመቻቸቱን ጠቁመዋል። ይህም ሀገሪቷ የሰው ኃይሏን እንድታደራጅና ለበርካቶችም የሥራ ዕድል እንድትፈጥር የሚያስችል መሆኑ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ጊዜም ሙያዎችን የመለየት፣ የመመዘንና ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪና የፓናል ወይይቱ አቅራቢ ተሾመ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በልምድ ለተገኘ ክህሎት እውቅና በመስጠት አንጻር በትኩረት እየሠራች መሆኑ ተናግረዋል።

በርካታ ሀገራት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ጀምሮ በልምድ ለተገኘ ክህሎት እውቅና መስጠት የጀመሩ መሆናቸውን አንስተው፤ ኢትዮጵያም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የአርሶ አደር ምዘና በሚል አርሶ አደሮችንና የልማት ባለሙያዎችን መመዘን ጀምራለች ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በልምድ ለሚገኝ ክህሎት እውቅና መስጠት የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱን አመልክተው፤ በልምድ ለሚገኘው ክህሎት እውቅና መስጠትም ወደ ሥራ የመሰማራት ዕድልን የማሳደግ፣ የሥራን ገበያ የማሻሻልና ኢኮኖሚያዊ እድገትና ፍትሐዊነት የማረጋገጥ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩትም ገልጸዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You