‹‹“ከዘመን ጋር ካልተጓዙ መቅደም ብቻውን መብለጥን አያመጣም̋”›› – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ:- የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዛሬ ሰባ ዓመት በጥሩ መሠረት ላይ ነው የተገነባው፤ ግን ከዘመን ጋር ካልተጓዙ መቅደም ብቻውን መብለጥን አያመጣም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሪፎርም እንዴት እንደሚሠራ ቋሚ ዓውደ ርዕይ የሚሆን ውጤት በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ተመልክተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዛሬ ሰባ ዓመት በጥሩ መሠረት ላይ ነው የተገነባው፤ ይሁን እንጂ ከዘመን ጋር ካልተጓዙ መቅደም ብቻውን መብለጥን አያመጣም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀድሞ የበቀለን ጆሮ በኋላ የመጣ ቀንድ ሊቀድመው ይችላል ብለዋል። እየፈጠኑና እየፈጠሩ ዘመኑን ካልቀደሙትም፤ ጊዜው ራሱ ይቀድማል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዛሬ ሦስት ዓመት ለሠራተኞቹ  ደመወዝ መክፈል ተስኖት እንደነበር አስታውሰው፤ ዕዳ እንደ መርግ ተጭኖት ነበር። በመሆኑም በተሠራው የሪፎርም ሥራ በቀን ያመርተው ከነበረው አንድ ሺህ 500 ኩንታል ዛሬ ወደ ሰባት ሺህ ኩንታል አድጓል ነው ያሉት።

ከዚህ ባሻገርም ለ14 ዓመታት ከሥራ ውጭ የነበረው የብዙዎች ትዝታ ደስታ ከረሜላ እንደገና መመረት ጀምሯል ሲሉ አስታውቀዋል። በሌማት ትሩፋት ዘርፍም በቀን 3 ሺህ ሊትር ወትት እና 20 ሺህ ዕንቁላል ማምረት የሚችል ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ ግቢው እና መስኩ ለዓይን እንደሚማርክ አመላክተዋል።

ወንጂ ዘንድሮ የፈተናውን ዘመን አልፎ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገብቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ይህ ጠንካራ የሪፎርም ውጤት በሌሎቹ ፋብሪካዎች እንደሚደገም ይጠበቃል፤ ከሠራን ነገን እንቀድመዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You