የማሠልጠኛዎቹ በጀት አነስተኛ መሆኑ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ተግዳሮት ሆኗል

አዲስ አበባ፡– ለቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛዎች የሚበጀተው በጀት አነስተኛ መሆን በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ተግዳሮት መሆኑን በኢፌዴሪ ቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በኢፌዴሪ ቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አንመው ታደሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ለሌሎች የትምህርት ተቋማት ከሚመደበው በጀት አንጻር ለቴክኒክ እና ሙያ ዘርፉ የሚመደበው በጀት አነስተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም ለዘርፉ አምስት በመቶ ብቻ የበጀት ድጋፍ ይደረግለታል። በዚህ በጀት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ተግዳሮት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠናዎች በተግባር የተደገፉ በመሆናቸው ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት 30 ዓመታት የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠናዎችን አቅርቦትን ከማስፋፋት እና ፍትሃዊነትን ከማዳረስ አንጻር የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ጥራት ያለው እና ብቃት ባለው ደረጃ ተሠርቷል ለማለት ግን አያስደፍርም ብለዋል፡፡

ዓለም ላይ ያለው ቴክኖሎጂ በየጊዜው የሚቀያየር ቢሆንም ማሠልጠኛዎቹ እራሳቸውን በየጊዜው ከጊዜው ጋር የማሻሻል ውስንነት መኖሩም ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ፤ የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ከብዙ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚገናኝ ቢሆንም ፖሊሲዎችን አናቦ እና አቀናጅቶ በመሥራት ረገድ ክፍተት አለ፡፡ የግሉም ዘርፍ ተማሪዎችን መቅጠር ብቻ ሳይሆን የማሠልጠን እና የመመዘን ሃላፊነት ቢኖርበትም ያንን እያደረገ አይደለም፡፡ በእነዚህም ምክንያቶች በዘርፉ ላይ የጥራት እና የብቃት ውስንነቶች እንዲከሰት ሆኗል፡፡

ዘርፉ ላይ ያሉ የሥልጠና ጥራት ችግሮችን በመፍታት በፖሊሲው እንደተቀመጠው 70 በመቶ የተግባር ሥልጠና መሰጠት እንዳለበት አመልክተው፤ ይህንን ማድረግ የሚያስችሉ ወርክሾፖች በየኮሌጆቹ ሊገነቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

አንዳንድ በሀገር ውስጥ የማይገኙ መሣሪያዎች ሲኖሩም በበይነ መረብ በመታገዝ ትምህርት መሰጠት እንደሚኖርበት ጠቁመው፤ ኢንዱስትሪዎች እና የትምህርት ተቋማቱ በጋራ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ አንድ ሺህ 700 በሚሆኑ የግል እና የመንግሥት ተቋማት መምህራንን እና አመራሮችን የማፍራት አቅሙ ውስን በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የሆኑ መምህራንን የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋሞች እንደሚቀጥሩ ገልጸው፤ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የትምህርት አሰጣጥ 80 በመቶ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት በመሆኑ የተግባር ልምድ የሌላቸው መምህራን ተማሪዎች በብቃት ማሠልጠን አይችሉም ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን ያለውን የተግባር ልምድ ማነስ በሥልጠና መሙላት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በተቋሙም በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ገበያው የሚፈልጋቸውን የትምህርት ዘርፎችን ለመክፈት እና ከገበያ ውጭ የሆኑትን በመዝጋት ወይም ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች ጋር በማዋሃድ እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አብራርተዋል። ከኢንዱስትሪው ጋር በቅርበት በመሥራት ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግም እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You