በኮሌጁ የሚቀርቡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉት ነው

አዲስ አበባ፡– ኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የሚገኘው አጋርፋ ኮሌጅ ለአካባቢው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየሰጠ ባለው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚነታቸው ከፍ እንዲል ማስቻሉን አስታወቀ፡፡

በአጋርፋ ግብርና ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን አቶ መሐመድኑር ቱጂ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሌጁ የማህበረሰብና የምርምር ቢሮ በማደራጀት ለአካባቢው አርሶ አደሮች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና በሴፍቲኔት ለተደራጁ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በማቅረብ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ካሉት በተለይም በሴፍቲኔት የተደራጁ የማህበረሰብ ክፍሎችና አርብቶ አደሮች ወደ ግብርና ሥራ ገብተው አምራች እንዲሆኑ በማድረግ ያከናወነው ተግባር ለአብነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል፡፡

ኮሌጁ፤ አካባቢው ላይ ሊመረቱ የሚችሉ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በተመጣጣኝ ዋጋና በነፃ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መሐመድኑር፤ ምርጥ ዘር ከማቅረብ በተጨማሪ በመስኖ፣ በእጽዋትና በእንስሳት ሳይንስና ተያያዥ መስኮች የክህሎት ሥልጠና እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

ለማህበረሰቡ የእየቀረቡ ካሉት የተሻሻሉ ዝርያዎች መካከልም ገብስና ስንዴ፣ ጎመንዘርና የአቮካዶ ዘሮች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

የተሻሻለው የአቮካዶ ዘር የአየር ፀባዩ ደጋ በሆነ አካባቢ አይበቅልም የሚለውን እሳቤ ያስቀረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መሐመድኑር፤ ሁለት አይነት የአቮካዶ ዝርያዎችን በማዳቀል ዘዴ የተሻሻለ ዝርያ ማግኘት መቻሉንና ውጤቱም ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ ተሻሽሎ እየወጣ ያለው የገብስ ዝርያ ለቢራ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውል መሆኑን ጠቅሰው፤ ገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ የተለያዩ የተሻሻሉ የቢራ ገብስ ዝርያዎችን በቴክኖሎጂ በማፍለቅ ከውጭ የሚገባውን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉንና ይህም የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተሻሽሎ የቀረበው የስንዴ ዝርያም በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ እንደሆነና ይሄም ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስንዴው ለዳቦ፣ ለጣፋጭ ምግቦችና ለፓስታ የሚውል መሆኑን ጠቁመው፤ ጎመን ዘር ዝርያም ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ ያልተለመደ ወደ ቢጫ ቀለም ያደላ አዲስ ዝርያ መሆኑንና ለምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደሚውል ገልፀዋል፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውልም በሙከራ ደረጃ ቨርብ ኮምፖስት በማዘጋጀት ኮሌጁ ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድኑር፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያው በጠጣርና በፈሳሽ ተዘጋጅቶ ወደ ተጠቃሚ በማድረስ አምራቹ እንዲለማመድ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኮሌጁ የሚያፈልቃቸው የተለያዩ የተሻሻሉ ዝርያዎች በማህበረሰቡ ያላቸውን ተቀባይነት በተመለከተ አቶ መሐመድኑር ፤ በዚህ ሰሞን ብቻ ወደ 50 ኩንታል አዶሺያ የተባለ የቢራ ገብስ ዝርያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ገልፀው፤ አርሶ አደሩ አምርቶ አንድ ኩንታል የቢራ ገብስ እስከ 11ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ በመሆኑ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ኮሌጁ አሰላ ብቅል ፋብሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የግል አምራች ኢንዱስትሪዎችና የኢትዮጵያ ምርጥ ድርጅት ጋር የሚሠራ መሆኑም የተሻለ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡ ዘሩን ማዳረስ ብቻ ሳይሆን፣ ምርታማነቱን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

አጋርፋ ኮሌጅ መማር ማስተማር፣ በመካከለኛ ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ቴክኖሎጂን ማፍለቅና ማሸጋገር እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን መሥራት ዋና ተግባራቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡

ኮሌጁ የሚገኝበት አካባቢ ለሰብል፣ ለእንስሳት ርባታ፣ ለወተት ልማት፣ ለንብ ማነብ ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ ወንዞችና የተለያዩ የውሃ ምንጮች ይገኛሉ፡፡ ባለው ሰፊ የውሃ ሀብት በመጠቀም በመስኖ ጭምር ሰፊ ልማት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ አጋርፋ ኮሌጅ 1975 ዓ.ም የተመሠረተ አንጋፋ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

በለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You