ጨዋታ ቀያሪው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤

እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና የበኩር ልጁ ባዛሩ ወይም ኤክስፖው እጅና ጓንት ሆነው ተንሰላስለው የኢንዱስትሪ ዘርፉን መልክ እየቀየሩት ይገኛል ብል ማጋነን አይሆንም። ምን አለፋችሁ ጨዋታ ቀይረዋል። ለዚህ ነው ይሄን ንቅናቄና የማስፈጸሚያ ፕሮጀክቱን ከሜጋ ፕሮጀክቶቻችን አሳንሼ የማላየው። አዎ ደፋር ባትሉኝ በራሱ መንገድ ከአረንጓዴ አሻራና ከየኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር ላወዳድረው የሚዳዳኝ።

በውል ለተረዳቸውና ለተነተናቸው ደግሞ ሶስቱም ተመጋጋቢ ናቸው።አንድም ሶስትም ናቸው። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከአረንጓዴ አሻራም ሆነ ከሕዳሴው የሚገኘውን ሲሳይና በረከት አሟጦ ለመጠቀም አበክሮ መደላድል እየፈጠረ ያለ ራሱ ሜጋ ፕሮጀክታችን ነው ማለት ይቻላል።

ይሄን የምለው ልብ ለማሞቅ አይደለም። 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ በአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተገኝቼ ጎብኝቼ የተፈጠረብኝን ስሜት ምን ይሉኝን ትቼ እንደ ወረደ ነው የገለጽኩት። የዘንድሮው ባዛር ደግሞ ከአምናውም ሆነ ከካች አምናው ከፍ ብሏል ብቻ ሳይሆን ልህቀት ጨምሯል። ደረጃውም አድጓል። የባዛር ክላስ ፈጥሯል። ማዕከሉ ደግሞ በልኩ የተሰፋ ይመስል ሄዶ ልክክ ነው ያለው።

በሀገራችን የባዛሮችንና ኤክስፖዎችን ደረጃ የሚያወጣ ሬት የሚያደርግ ተቋም የለም እንጂ ቢኖር ከበጀት ዓመቱ ይህ ባዛርና የኢትዮጵያ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር በዚያ ሰሞን በሚሊኒየም አዳራሽ ያዘጋጀው የሆርቲፍሎራ ኤክስፖ ደረጃውን ሰቅሎታል። የባዛሩን ዘርፍ ማለቴ ነው። ወደ ሰሞነኛው ኢትዮጵያ ታምርት ባዛር ስመጣ በተሳታፊ ኢንዱስትሪዎች እና ፋብሪካዎች ብዛት፣ ስብጥር፣ ጥራት፣ ይዘዋቸው በቀረቡ ምርቶች እና በሌሎች መመዘኛዎች ከቀደሙት ከሁለቱ ጋር ብናነጻጽረው የዘንድሮው የትና የት። አንድ ነገር ግን የበለጠ ትኩረት የሚሻ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እሱም ንቅናቄውን 24/7 በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያ የመደገፍ ጉዳይ ይበልጥ ልዩ ትኩረት ይሻል። ከሩጫውና ከባዛሩ ባልተናነሰ ከዜና የተሻገረ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ማግኘት አለበት። ያለበለዚያ ንቅናቄው ምሉዕ አይሆንም።

በሀገሩ ምርት የሚኮራ ሸማች ለማፍራት፣ የዘርፉን የማኑፋክቸሪንጉንም ሆነ የኢንዱስትሪው ምርታማነት ለማሳደግና የሠራተኛውን የሥራ ባህል ለመቀየር ከኩነት ዝግጅት የተሻገረ እና ዓመቱን ሙሉ የሚካሄድ የሚዲያ ሥራ ይጠይቃል። ይሄ ዘርፍ ሀገርን እና ዜጋን ይዞ የመነሳት አቅም ያለው ዘርፍ ስለሆነ ከሚዲያው ጋር ለአፍታ እንኳ መለያየት የለበትም።

የዛሬዋ ዓለም እኮ የኢንዱስትሪ አብዮት የእጅ ሥራ ናት። በፋሪድ ዘካሪያ ድንቅ መጽሐፍ፣” Age of Revolutions”ላይ እንደተመለከተው እንግሊዝ ከኔዘርላንድ ወይም ሆላንድ ሪፐብሊክ ለሀገሯ እንዲሆን አድርጋ በኮረጀችው ዕድገትና ብልፅግና የኢንዱስትሪ አብዮትን ችቦ አቀጣጥላ ለዓለም አቀብላለች። አውሮፓን አዳርሶ አትላንቲክን ተሻግሮ አሜሪካን አካሎ ወደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና ያቀናው የኢንዱስትሪ አብዮት ነው በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከድህነት አረንቋ ያወጣው። ሀገራቱን ያበለፀገው። ቻይናንም ባለ ግዙፍ የዓለማችን ኢኮኖሚ ያደረገው ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ነው። በአቋራጭ ከማያልፏቸው የዕድገት እና የብልፅግና መንገዶች ንግድና ኢንዱስትራላይዜሽን ዋናኛዎቹ ናቸውና።

ሌላው ነጮች እንደ ሚሉት White Elephant in the Salon በሳሎን ውስጥ ያለውን ነጩን ዝሆን ወይም ወሳኙን ወቅታዊ ጉዳይ ባላየና ባልሰማ አልፈን ስለ ኢትዮጵያ ታምርት ልናወራ ስለማንችል፤ ባላየና ባልሰማ እንለፈው ብንል እንኳ ራስን ከማጃጃል ባሻገር እውነታውን ስለማይቀይረው በኢትዮጵያ ሳሎን ካሉ ነጫጭ ዝሆኖች ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መሳ ለመሳ ልዩ ትኩረት ይሻሉ። ስለሆነም ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት ላይ ያሉብንን የቤት ሥራዎች በጊዜ የለም መንፈስ ልንሠራ ይገባል። በአንድነት ያልቆመ ሀገርም ሆነ ዜጋ በዘላቂነትና ቀጣይነት ሊበለፅግ አይችልምና። ለመንደርደሪያ ያህል ይቺን ካልሁ ወደ ገደለው።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መጎልበት ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማሳለጥ የሀገርን ብልፅግና እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ በመደገፍ የተረጋጋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓትን ለመፍጥር እገዛ ያደርጋል።

ይህ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በኢትዮጵያ ያለውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዕምቅ አቅም በማሳየት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ዕድገት ለማስተዋወቅ፣ ለፖሊሲና አሠራር ማሻሻያነት እንደ ግብዓት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ የሚጠቅሙ የውይይት መድረኮችን ለመፍጠር እና በሀገር ውስጥ ምርት የሚኮራን ሸማችና አምራቾችን በማስተዋወቅ ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ኢንዱስትሪዎችን ከዚህ በላይ ለማስፋፋት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ወደ ትግበራ በተሸጋገረ ማግስት በርካታ ለዘርፉ እድገት ቁልፍ የሆኑ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እነዚህን በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶች ከፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ከማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተኪ ምርትን ምርታማነት ከማሳደግ አንጻር የተገኙ አበረታች ውጤቶች ናቸው፡፡

በአብነት የኃይል አጠቃቀም ዕድገትን እንመልከት። ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታ እየጨመረ እንደመጣ መረጃዎች ያመላክታሉ። አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ኃይል ፍጆታ በ2014 ከነበረበት 2.61 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት በ2015 ወደ 2.62 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት ያደገ ሲሆን በ2016 ወደ 3.39 ከፍ ብሏል። በ2017 የመጀመሪያዎቹ 9 ወራት ውስጥም ወደ 2.58 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተጠቀሙ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከኤሌክትሪክ ፍጆታው አንጻር የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በአማካኝ የ9.57 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማሳየት አጠቃላይ የ31.8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።

ይሁንና ኢንዱስትሪው አንድ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርትን ለማምረት የሚጠቀመው ኤሌክትሪክ ኃይል (የኢነርጂ ኢንተንሲቴ) ሲሰላ በ2014 ከነበረበት 0.52 kWh/US ዶላር ወደ 0.31 kWh/US ዶላር በ2017 ቀንሷል፣ ይህም የኢነርጂ አጠቃቀም ውጤታማነት በ40 ከመቶ መሻሻሉን ያሳያል። የኢትዮጵያ አማካይ የአምራች ኢንዱስትሪው የኃይል አጠቃቀም ጥንካሬ በአንድ የአሜሪካ ዶላር የማኑፋክቸሪንግ የተጨመረ እሴት (MVA) 0.4 የኪሎዋት ሰዓት ሲሆን ይህም ከዓለም አቀፍ አማካኝ (ከ0.3 እስከ 0.4 ኪሎዋት ሰዓት) እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ላይ ከደረሱ እና ኢንዱስትሪያላይዜሽን በፍጥነት እየተመነደገባቸው ካሉ ሀገራት ተርታ ያሰልፈናል።

ወደ ማምረት የገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎችና የተፈጠረ የሥራ እድልን ስንመለከት ደግሞ፣ በ2014 በጀት ዓመት 26 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ የተደረገ ሲሆን በ2015 ደግሞ 86 ኢንዱስትሪዎችን፣ በ2016 ደግሞ ወደ 131 ወደ ምርት ተሸጋግሯል። የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀምም ሲታይ 83 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል። በተጨማሪም ከ2014 እስከ 2017 ዘጠኝ ወራት ውስጥ በድምሩ ከ13830 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲቋቋሙና እንዲስፋፉ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን በአማካይ በየዓመቱ ከ3457 በላይ አነስተኛና መካከለና እንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ተችሏል።

በኢትዮጵያ ታምርት የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሠራር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች ማለትም የውጭ ምንዛሬ፣ የብድር፣ የፋይናንስና የኃይል አቅርቦት ሌሎች ችግሮችን በመፍታትና ወደ ሥራ በማስገባት እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገሩ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከ2014 እስከ 2017 ዘጠኝ ወራት ድረስ በድምሩ 910 ሺህ ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል። በአማካይ በየዓመቱ 228 ሺህ አዳዲስ የሥራ እድል ተፈጥሯል።

በየዓመቱ ወደ ምርት እየገቡ ያሉ የፈጠራ ሥራዎችን ስንቃኝ፣ከ2014 እስከ 2017 የመጀመሪያው ዘጠኝ ወራት ጠቅላላ 91 ምርቶችንና 35 ቴክኖሎጂዎችን ማልማት ተችሏል። ይህም በእነዚህ ዓመታት አዳዲስ ምርቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን አልምቶ ወደ ገበያ ማስገባት አማካይ እድገት ከ18 በመቶ በላይ ሲሆን ይህም በየዓመቱ በአማካይ 31 የለሙ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ገበያ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ተችሏል። በ2016 ዓመት በተካሄደው ኤክስፖ ከ5 በላይ የፈጠራ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ በኤክስፖው በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በብዛት ወደ ምርት በማስገባት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችለዋል።

ሌላውና ወሳኙ የንቅናቄው ትኩረት ገቢ ምርቶችን መተካት እና የንግድ ሚዛን ክፍተትን ማጥበብ ነው።በተኪ ምርት የዳነው የውጭ ምንዛሬ በ2014 በጀት ዓመት ከ0.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያልነበረው በ2015 ወደ 2.1 ቢሊዮን እያደገ የመጣ ሲሆን በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ ተኪ ምርቶች በማምረት ከ2.84 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል። የዚህን በጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሲታይ የተጣራ 3.1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል።

ከ2014 እስከ 2017 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ድረስ ተኪ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት አጠቃላይ 8.34 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ በማዳን አማካይ አመታዊ እድገቱም ከ14 በመቶ በላይ እና በአማካይ በየዓመቱም የተጣራ 2.1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማዳን ተችሏል።በዚህም በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ ተኪ ምርት አፈፃፀም ዙሪያ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ በመደረጉ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻን በ2014 ከነበረበት 30 በመቶ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 41.4 በመቶ ማድረስ ተችሏል።በሌላ መልኩ አምራች ዘርፉ ተኪ ምርቶችን በማምረት በጥራትና በተወዳዳሪነት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በስፋት በማቅረብ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በ2014 ከነበረበት 12.8 ቢሊዮን ዶላር በ2016 መጨረሻ ወደ 11.5 ቢሊዮን ዶላር ማጥበብ ተችሏል። ይህም በእነዚህ ዓአመታት ውስጥ የንግድ ሚዛን ጉደለቱን በ10.1 በመቶ ያህል እንዲሻሻል(እንዲጠብ) ተደርጓል።

የኢንጅነሪንግ ዘርፉ እንደ ሀገር የተጀመሩ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሥራዎችን ከማሳደግ አንጻር ያለው አስተዋፅኦ ደግሞ እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ መነሻውን ከባህላዊ የብረታ ብረት ሥራ ያደረገው የሀገራችን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ እራሱን ለማዘመን በፈጣን የሽግግር ሂደት ላይ ይገኛል።የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከውጭ ተገዝተው ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ የግብርና ማሽኖች በሀገር ውስጥ በመመረታቸው ወደ 120 ሚሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ማዳን ተችሏል።

በዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ሊያስገቡ የሚችሉትን ማሽኖች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ የውጭ ምንዛሬን ማዳን የተቻለ ሲሆን ለአብነትም 55 የወርቅ ማውጫ ማሽኖች፣27 መኖ ማቀነባበሪያ፣10 የስንዴ መውቂያ፣5 ፕላዝማ ኮቲንግ ማሽኖች እንዲያመርቱ በማድረግ ለገበያ እንዲውሉ ተደርጓል። በአጠቃላይ ማሽን ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ መስፋፋትና እድገት ለገጠር ኢንዱስትሪላይዜሽን የውጭ ምንዛሬ ቁጠባ፣የምርታማነት ጭማሪ እና የሥራ እድሎች መፍጠር፣ ለአካባቢ ፍላጎት ተስማሚ የሆኑ የማሽነሪ ዲዛይኖች ማዘጋጀት፣የሰው ኃይል ልማትና ክህሎት ማሳደግ እና ሙያዊ አቅም መገንባት፣ባህላዊ እውቀትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውህደት በማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም ማሻሻል፣በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈጠረው መነሳሳትና የተቀናጀ አሠራር መሰረት የአምራች ኢንዱስትሪውን መሰረታዊና መዋቅራዊ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም በ2014 ከነበረበት 46 በመቶ በ2015 ወደ 53 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ወደ 59 በመቶ ክፍ በማድረግ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።በ2017 ስድስት ወራትም ወደ 61.2 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በአጠቃላይ አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀምም በየዓመቱ በአማካይ ከ5 በመቶ በላይ ማደግ ችሏል።

በሀገራችን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በተደረጉ የመንግሥት ትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ባለፉት ሶሰት ዓመታት የማምረት አቅም አጠቃቀምንና ምርታማነትን በማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አመታዊ እድገት በ2014 ከነበረበት 4.8 በመቶ ዓመታዊ እድገት በ2015 በጀት ዓመት በ7.2 በመቶ ማደግ ችሏል። በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ በ10.1መቶ እድገት አስመዝግቧል። በዚህ በጀት ዓመትም በ12.9 በመቶ ማደግ እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ።

የማኑፋክቸሪንግ የምርት መጠን ደግሞ በ2014 ከነበረበት 151.6 ቢሊዮን ብር በ2015 ወደ 162.1 ቢሊዮን ብር የጨመረ ሲሆን በ2016 በጀት ዓመትም 178.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል።የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ እሴት ጭማሪ በከፍተኛ እድገት አሳይቷል፤ይህም የማኑፋክቸሪንግ እሴት የተጨመረበት ምርት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በ2016 ወደ 8.3 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ይህ ከፍተኛ የሆነ የእሴት ጭማሪ ከላይ የተጠቀሰውን ትክክለኛ የምርት ዕድገት የሚያንፀባርቅ ነው።

ያለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረኮችን ደግሞ በወፍ በረር ስንቃኝ፣ባዛሮች እና ኤክስፖዎች ውጤቶችና ከዚህ ዓመት ኤክስፖ የሚጠበቁ ውጤቶች፣ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በየደረጃው የተካሄዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረኮችና ባዛሮች በአጠቃላይ 244 የንቅናቄ መድረኮች እና 116 ባዛሮችን ማለትም በየደረጃው የተካሄዱ በአማካይ በየዓመቱ ከ37ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ከ80 በላይ የንቅናቄ መድረኮች እና ከ38 በላይ ባዛሮችን ማካሄድ ተችሏል።

የዘርፉን ማነቆ በቅንጅት ለመፍታት የእንችላለን ስሜት የሚዳብርበት፣ አማራጭ ሃሳቦችን የሚሰባሰቡበት፣ ምርቶች የሚተዋወቁበትና ዘላቂ የንግድ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርት ያለውን አመኔታ ያሻሻለበትና ግንዛቤ የተፈጠረበት መድረኮች እንደነበሩ ማስታወስ ይቻላል።

እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ሁለት ታላላቅ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖዎች 334 አምራች ኢንዱስትሪዎችን( 171 ከፍተኛ እና 163 አነስተኛ መካከለኛ አንዱስትሪዎች) በማሳተፍ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ ፈጥረውላቸዋል፡፡በዚህም ኤክስፖ ከ153ሺህ በላይ ሰዎች የጎበኙት ሲሆን በዚህም ከ5133 በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የግብይት ግንኙነት መፍጠር ተችሏል።

በአጠቃላይ በሰሞነኛውና 3ኛው ኤክስፖ ከሰባት ክልሎችና ከ2 ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሰባት ንኡስ ዘርፎች የተውጣጡ ከ282 በላይ ኢንዱስትሪዎች ላይ ምርቶቻቸውን እና ልምዶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን 161 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፣ 100 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣17 የፈጠራ ሥራዎች የሚያሳዩ ኢንዱስትሪዎች እና አራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ጥበቃ እና የተቀናጀ ምርታማነት ማሻሻያ ተሞክሮ የሚያቀርቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል።በዚህ ኤክስፖ ከ120ሺህ በላይ ጎብኝዎች የሚሳተፉበት እና ከ6000 በላይ የገበያ ትስስሮችን እንዲካሄዱ በማመቻቸት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የግብይት ትስስር ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም በዚህ ዓመት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ላይም ከ16 በላይ የፈጠራና ማሻሻያ ውድድር ተሳታፊዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበትና ልዩ የፈጠራ ውጤቶች የሚቀርቡበት ታላቅ ኤክስፖ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት 2017 ኤክስፖ ልዩ ገጽታዎች አሉት።ተሳታፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከለፈው ዓመት ኤክስፖ በ66 እንዱስትሪዎች ብልጫ ያለው መሆኑ፣የክልል ስብጥር በእጅጉ የተሻለ ማለትም ባለፈው ዓመት የተሳተፉት ኢንዱስትሪዎች ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ የተውጣጡ ሲሆን በዚህ ዓመት በሚካሄደው ኤክስፖ ከዘጠኝ ክልሎች የተውጣጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ መደረጉ እና የአንዱስትሪዎች ንኡስ ዘርፍ ስብጥር ሲታይ ባለፈው ዓመት ከስድስት ንኡስ ዘርፎች የተውጣጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን አምና ላይ ያልነበረ ሁለት ንኡስ ዘርፎች ማለትም ስጋና ወተት እና ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎች መጨመሩ፣ከኩነቶች ብዛት አኳያ ሲታይ ባለፈው ዓመት ሰባት ኩነቶች የነበሩ ሲሆኑ በዚህ ዓመት ደግሞ ዘጠኝ ኩነቶች የሚካሄዱበት መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ የዚህ ዓመት ኤክስፖ ካለፉት ዓመታት በእጅጉ የተለየ መሆንን መረዳት ይቻላል።

ቀጣይ አቅጣጫዎች ደግሞ፦

1ኛ. የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ወደ ተሟላ የትግበራ ምዕራፍ ማሸጋገር፣

2ኛ. በተለይ በዚህ ዓመት ወደ ሥራ የገባው የአምራች ኢንዱስትሪ ብሄራዊ ካዎንስል እንዲሁም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ በማስቀጠል ከፌዴራል እስከ ክልልና የከተማ አስተዳደር ድረስ በማውረድ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችንና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር የአምራች ኢንዱስተሪዎችን ማነቆዎች መፍታት፣

3ኛ. በምርታማ የሥራ ባህል የሚገለጽ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ከመገንባት አኳያ ሰፊ የግንዛቤና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን የአመለካከትና የሥራ ባህል ለውጦች እንዲመጡ በአንክሮ መሥራት፤

4ኛ. የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማስፋፋት ህብረተሰቡ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ያለው አመለካከት ላይ በመሥራት የምርቶቹን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ከማሳደግ አኳያ ሥራዎችን መሥራት፤

5ኛ. የአካባቢያዊ ጸጋን ማዕከል ያደረጉ እና እርስ በርስ እንዲሁም ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተመጋጋቢ የሆኑ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን የማስፋፋት ሥራ ማከናወን፡፡

6ኛ. በዋናነት በዘርፉ እንደ ሀገር የሚስተዋሉ የቴክኖሎጂ፣ የዕውቀት፣ የክህሎት እና ካፒታል ጉድለቶችን ሊሞሉ የሚያስችሉ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ፤ እንዲሁም በዘርፉ ያሉና አዲስ ለሚቀላቀሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ምቹ የቢዝነስ ከባቢን መፍጠር ናቸው።

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You