
ሀገር የዜጎቿ መልክ ናት። በተለይ እንደ አርበኞቻችን ባሉ በሀገር ፍቅር ስሜት በተነኩ ነፍሶች በኩል ሲሆን ትርጓሜው ለየት ይላል። ከዚህ እውነት በመነሳት ኢትዮጵያና ጀግንነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት እንችላለን። ልክ እንደ እጅና ጓንት፣ ልክ እንደመዳፍና አይበሉባ ከዘመን ዘመን ከትውልድ ትውልድ ስማችን በኩራት ሲጠራ ቆይቷል። አርበኝነት ከታሪክነት ባለፈ በእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ የበቀለ የኢትዮጵያዊነት አለላ መልክ ነው። ብዙ ትናንትናዎችን የፈጠረ የዘመን ቀለማት።
ለዚህ ደግሞ በተለያየ ጊዜ በጠላት ላይ በወሰድነው የበላይነት ያስመዘገብናቸው አኩሪ ብሄራዊ ድሎች ምስክር ናቸው። ከነዚህ እሙን የታሪክ ድርሳን ውስጥ አርበኞቻችን ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ። የትናንቷ ኢትዮጵያ የዛሬዋም መልካም ምድር በአርበኞቻችን እንባና ደም የተቀለመች ስለመሆና መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው። ሲነኳቸው በሚቆጡ፣ ሲደፍሯቸው በህብረት በሚነሱ ጥቁር ሕዝቦች የጸናች ናት።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ከተጻፉ ክቡር ስሞች ውስጥ አርበኛ የሚለው ቃል ቀዳሚው ቃል ነው። በዘመናት የጥቁሮች ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ ሆኖ ዛሬም ድረስ በክብር ይጠራል። ከአፍሪካ አልፎ በዘመናዊው የአውሮፓ ሥልጣኔ ውስጥ የሃያላኖቹ የእግር እሳት ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ። የቆምነው በዚህ ታላቅ እውነት ውስጥ ነው። ኢትዮጵያን ያቆማት ይሄ ስም ነው። የተከፈለልን የሀገር ፍቅር ስሜት እንደዋዛ የሚታይ ሳይሆን ሕይወት የተገበረበት በመሆኑን አስታውሰን አሁን ላለችው ሀገራችን በያገባኛል ልንቆም ይገባናል።
ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ፋና ወጊዎች ሆነን ቀደምት ስልጡን ሕዝቦች በመባል የምንጠራው በሀገራቸውና በርስታቸው ቀልድ በማያውቁት አባቶቻችን ደምና አጥንት ነው። ከትናንት እስከዛሬ ለሀገርና ሕዝብ ክብር ሲሉ ራሳቸውን እንደ ሻማ ያቀለጡ በርካታ አባቶች አሉን። ርስቴን አልሰጥም፣ የሀገሬን ዳር ድንበር አላስነካም ሲሉ የሞቱ፣ የተንገላቱ ብዙ የሀገር ባለውለታ አርበኞች በትናንትና በዛሬ ውስጥ ተፈጥረዋል።
እኔና እናተም የነዚህ ባለውለታ አርበኞቻችን የደም ፍሬ ነን። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዚህ ልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልታና ታፍራ እንድትታይ ያደረጉት እነሱ ናቸው። በዓድዋና በካራማራ፣ በኡጋዴንና በአንባላጌ ታላቅ ገድልን በመፈጸም የማይሞትና የማያረጅ ዘላለማዊ ክብርን ሲሰጡን በዝም ብሎ ሳይሆን ሀገርህን ጠብቅ ከሚል የአደራ መልዕክት ጋር ጭምር ነው። መልዕክቱ ለዚህ ትውልድ ዘመነኛ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ከሀገር የሚበልጥ የርስት ውርስ እንደሌለ ገብቶን በአንድነቷ የታፈረች ኢትዮጵያን እንድንፈጥር ጉልበት የሚሆነን ነው።
ሁላችንም የደም ፍሬ ነን። ክብራችን ሳይጎድል፣ ነጻነታችን ሳይነካ ዳር ድንበራችን ሳይደፈር በክብር የምንጠራው ነፍሳቸውን ለሀገር በሰጡ አባቶቻችን ሞት እንደሆነ ሀቅ ነው። ጀብድን ከጀግንነት ጋር ይዘው፣ እውነትን ከጽናት ጋር ሸክፈው የአደራ ሀገርን አስረክበውናል። አደራ በል እንዳንሆን ያስረከቡንን ሀገር በፍቅር አጽንተን ለመጪው ትውልድ የማስረከብ እዳ ተጥሎብናል። ኢትዮጵያን ተባብረው ከገነቧት ጽኑ ክንዶች ተቀብለን ቀጣይ እጣ ፈንታዋን ለመወሰን አደራ ተሰጥቶናል።
ከእውነት ሁሉ እውነት ሀገር ናት። ሀገር የሁላችን ክብር ናት። የደስታችን አጥቢያ የኀዘናችን መድረሻ እንዲህም ናት። ስለ ሀገር አባቶቻችን ያስተማሩን እውነት ይሄ ነው። ከታላላቆቻችን የሰማነው፣ ከፊተኞቻችን ያወቅነው ጥበብ ይህ ነን። በነፍሶቻችን ላይ የአባቶቻችን የአደራ ቃል አለ። ይሄን የአደራ ቃል ይዘን ነው የምንኖረው።
አርበኝነት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ፣ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደም ውስጥ የሚቀዳ የሉዓላዊነት ድንበር ነው። የእያንዳንዳችን ትናንት፣ የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ በአርበኞቻችን ሞት የተገኘ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ድርና ማግ ፈትለውና ሸምነው በትውልድ ልብ ውስጥ የቋጩ የዚህኛው የዚያኛውም ዓለም ጀብደኛ ነፍሶች ናቸው።
በእኚህ ነፍሶች ውስጥ መኖር ለሀገርና ሕዝብ የሚከፈል የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል። በነዚህ ነፍስ ውስጥ መኖር ራስን ለሌሎች ህልም ገምሶ እንደመስጠት እቆጥረዋለሁ። በአባቶቻችን ደጋግ ነፍሶች ዛሬ እኔና እናተ ወልደን ከብደን እድሜ ቆጥረናል። ብርቱ ሕዝብ፣ ሥልጡን ሀገር ተብለን በዓለም አደባባይ ተመስክሮልናል። ነገ ለሚፈጠረው አዲስ ትውልድ ደግሞ እኔና እናተ እናስፈልጋለን። በአባቶቻችን ሀቅ እንደኖርን ሁሉ በእኛም ሀቅ የሚኖር ትውልድ ይመጣልና ራሳችንን ለሃላፊነት ማዘጋጀት ይኖርብናል። አባቶቻችን በዚህ ልክ ባይኖሩ ኖሮ አሁን ላይ እኛ በዚህ ልክ አንገኝም ነበር። አባቶቻችን ለእኛ እንዳስፈለጉ ሁሉ እኛንም የሚፈልግ ትውልድ ይመጣልና አስፈላጊ ዜጋዎች ሆነን መቆም የዜግነት ግዴታችን ነው።
በአባቶቻችን መኖር ኖረናል። በተስፋቸው ለምልመናል፣ በእውነታቸው ደምቀናል አሁን ሌሎችን ለማኖር የእኛ ተራ ነው። ተነጋግሮ በመግባባት ለሌሎች የምናስፈልግበት፣ ለሌሎች የምትሆን ምቹ ሀገር ለመፍጠር የአርበኝነት ሥራ የምንሠራበት ሰዓት ላይ ነን። ዛሬ መልካም ነገር ለመሥራት ከቀኖች ሁሉ ትክክለኛው ቀን ነው።
በዚህ ቀን ላይ መልካም ሥራ በመሥራት በእኛ በኩል ለሚመጣው አዲስ ትውልድ ስንቅ ለመሆን መነሳት ይጠበቅብናል። የእኛ ዛሬ በአባቶቻችን የተፈጠረ ነው። የልጆቻችንም ነገ በእኛ መልካም ዛሬ የሚፈጠር ይሆናል። የሃሳባችን መልካም መሆን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉም በረከትና መልካምነት ነውና ሁሉን ነገር ከሃሳብ እንጀምር። ህልምና ራዕያችን ለሌሎች እንዲጠቅምና እንዲበጅ አድርገን እናዘጋጀው።
አባቶቻችን የኢትዮጵያ የትናንት ብሩህ መልኮች ነበሩ። አርበኞቻችን ለእያንዳንዳችን ደማቅ ዛሬ የሞት ዋጋ የከፈሉ የመልካም ልቦች ባለቤት ነበሩ። ሁላችንም ለሁላችን እናስፈልጋለን። አወቅንም ሳትንም አስፈላጊዎች ሆነን ነው ወደ ምድር የመጣነው። በአባቶቻችን የአርበኝነት ተጋድሎ ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተፈጥረዋል።
ነገ ደግሞ በእኔና በእናተ የአርበኝነት ተጋድሎ የሚፈጠር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይኖራል። ከእኛ በኋላም ያለው ትውልድ እርስ በርሱ የሚደጋገፍ ነው። ደምቀው የተጻፉ ብዙ ትናንትናዎች በእያንዳንዳችን ዛሬ ውስጥ አሉ። ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ሆነው አጠገባችን የቆሙ ሰዎች ነበሩ። ለመኖራችን ብርታት ሆነው በትናንትና በዛሬአችን ውስጥ የበቀሉ ደጋግ ነፍሶች ስለመኖራቸው አልጠራጠርም። ይሄን እውነት ወደ ሀገርና ሕዝብ ስናመጣው አርበኞቻችንን እናገኛቸዋለን። እውነታቸው ከእኛ አልፎ ወደ ልጅ ልጆቻችን እንዲሸጋገር በተራመዱበት የአንድነትና የወንድማማችነት መንገድ ላይ መቆም ያሻናል።
በዓለም አደባባይ ብዙዎች አንገታቸውን ቀና ማድረግ ተስኗቸው አቀርቅረው በሚኖሩበት በዚህ ዘመን ቀና ብለን እንድንራመድና ማነህ ስንባል ኢትዮጵያዊ ነን ብለን በኩራት እንድንናገር ያደረጉን እነሱ ናቸው። በጥቁርነት ውስጥ ዘለአለማዊ ክብርን፣ ዘለአለማዊ ነጻነትን ያጎናጸፉን በዛኛው ትውልድ ማህጸን ውስጥ የበቀሉ አርበኞቻችን ናቸው።
ዛሬ በሀገራችን ላይ ጀብድ ለመሥራት የእኔና የእናተ ተራ ነው። ዛሬ የእኔና የእናተ የድል የተስፋ ቀን ነው። ታሪክ ከማውራት ወጥተን ታሪክ የምንሠራበት ዘመናችን ነው። እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በብዙ ችግርና መከራ ውስጥ የምትገኝበት ሰዓት ላይ ናት።
ከትናንት በባሰ የእኛን አንድነት የእኛን አብሮነት የምትፈልግበት የችግር ጊዜ ላይ ናት። ከውስጥም ከውጪም ጠላቶች ተነስተውባታል። አንድነቷን ህብረቷን ለመሸርሸር የተንኮል ሴራዎችን የሚያሰሩ ግለሰቦች ቡድኖች ሀገሮች ሳይቀሩ የተነሱበት ጊዜ ነው። እንደ አባቶቻችን ትውልድ የማይረሳውን የጀግንነት ተግባር ፈጽመን ለማለፍ ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን።
ከእኔነት ወጥተን ለሀገራችን ምርጡን ለማድረግ በአንድነት የምንቆምበት የተጋድሎ ጊዜ ላይ ነን። ስለኢትዮጵያ የተቀበልነው የአደራ ቃል ተፈጽሞ ለሁላችን የምትበቃ የጋራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የምንተጋበት ሰሞን ላይ እንገኛለን። ነገ ለሚፈጠረው አዲሱ ትውልድ መንገድ ጠራጊ በመሆን የአርበኝነት ድርሻ አለብን። እንደ አባቶቻችን የምኩራቦቻችን ደማቅ ቀለሞች ሆነን ስማችንን ከትውልድ አብራክ ውስጥ እንጽፍ ዘንድ ዛሬ የእኛ ቀን ነው።
ዘረኝነት አድማሱን አስፍቶ አብሮነታችንን እየተፈታተነን ባለ ጊዜ ላይ ነን። ከአባቶቻችን የተቀበልነው እና ለሚመጣው የምናወርሰው የወንድማማችነት አርበኝነት ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል። በፖለቲካው በኢኮኖሚው በማህበራዊው ሕይወታችን ውስጥ ሀገራችን የእኛን አርበኝነት የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። አሁን ለሀገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ምርጡን የምንሠራበት ከሁሉ ምርጥ ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያን እወዳለው የሚል ሁሉ ከወሬነት ባለፈ በተግባር የሚፈተንበት ጊዜ ላይ ነን።
አብዛኞቹ ችግሮቻችን አንድነትን ሕዝባዊነትን የሚሹ ናቸው። አብዛኞቹ መፍትሄዎች ደግሞ በእኔና በእናተ እጅ ውስጥ ናቸው። እኔና እናተ በአንድነት ከቆምን ችግሮቻችን ሁሉ እሳት እንዳየው ቅቤ ቀልጠው እንደሚጠፉ ጥርጥር የለኝም። የእስካሁኑ ችግሮቻችን በአንድነት ማጣት በመለያየት የመጡ ናቸው።
ባለመነጋገር፣ ባለመደማመጥ የተፈጠሩ ናቸው። መለያየታችን የፈጠራቸው ችግሮቻችን ናቸው ዛሬ ላይ በየቦታው መከራ ሆነው የሚያሰቃዩን። አርበኛ ለመባል የግድ ጦር ሜዳ ሄደን መዋጋት አይጠበቅብንም። አርበኛ ለመባል ጦርና ጎራዴ ወይም ደግሞ መሣሪያ መታጠቅ አይኖርብንም። በብዕራችን መልካም ነገር በመጻፍ አርበኛ መሆን እንችላለን። በተግባራችን አስፈላጊዎች በመሆን ታሪክ መሥራት እንችላለን። በእያንዳንዱ ሀገራዊ ችግር ላይ በነቃ ተሳትፎ መፍትሄ በማምጣት የዚህኛው ትውልድ አርበኛ መሆን እንችላለን።
እንደ ሀገር ለሚነሱብን ችግሮች ጦር ሳንማዘዝ በሰላም ከፈታን አርበኛ ነን። በጥላቻ እና በዘረኝነት ሳንሸነፍ አብሮነትን ለማስቀጠል የድርሻችንን ከተወጣን ሳንገል እና ሳንሞት አርበኛ ነን። በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠቅም አመርቂ ውጤት በማምጣት አርበኛ መሆን እንችላለን። ጥሩ ነገር በመሥራት፣ መልካም ነገር በማሰብ በዙሪያችን ላሉ አስፈላጊዎች ሆነን በመቆም በዚህም አርበኛ መሆን ይቻላል።
መልካም ሥራ ለመሥራት ከተዘጋጀን ጀብድ ልንሠራባቸው የምንችልባቸው በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። ችግሩ ግን ካበደው ጋር ማበድ፣ ድንጋይ ካነሳው ጋር ድንጋይ ማንሳታችን ነው። ሀገራችን በአስተሳሰባችን ውስጥ ናት። ከነውረኛ አስተሳሰብ ወጥተን ወደሚደነቅ ብርሃናዊ እውነት መምጣት የአባቶቻችንን አደራ ከምንወጣበት መንገድ አንዱ ነው።
አብዛኞቻችን ታሪክ ከመሥራት ይልቅ ታሪክ በማውራት የምንኖር ነን። ዛሬ ላይ ታላቅ ነገር ለመሥራት ከመሞከር ይልቅ በአክሱምና ላሊበላ እየተደነቅን ሥራ ፈተን የምንቀመጥ ብዙዎች ነን። ትልቅ ለመሆን ከመጣር ይልቅ ትልቅ ነበርን ብለን ያለፈን በማውራት ጊዜ የምናጠፋ እንበዛለን። የዚህ ትውልድ አርበኝነት በመነጋገር እና በሰላማዊነት የሚገለጽ ነው። የወንድማማችነት ችቦን በመለኮስ የብቻ ኑረትን በመሻር የምናደርገው ሀገር ግንባታ ጀብደኝነት ነው።
ትልቅ ነገር ለመፍጠር ከተዘጋጀን ይቻለናል። አባቶቻችን ባልዘመነና ባልሠለጠነ ዘመን ነው ዓለምን ጉድ ያስባለ ታሪክ የሠሩት። እኛም የዛሬዎቹ ትውልድ በብዙ ነገሩ ምቹና ስልጡን በሆነ ዘመን ላይ ነን ለሕዝባችንም ሆነ ለሀገራችን ታሪክ ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ዘመን ላይ ነን። የአባቶቻችንን ወኔ ለብሰን ላሉብን ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ በማምጣት የዜግነታችንን እንድንወጣ በማሳሰብ ላብቃ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም