የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከማክሰኞ ጀምሮ ይካሄዳል

54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል። ቻምፒዮናውን ደማቅና ስኬታማ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከሚያዝያ 28-ግንቦት 03/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ በርካታ ታዋቂና አዳዲስ ወጣት አትሌቶች ይፎካከራሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሚኒኬሽን ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ ፣ የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በጋራ በመሆን በቻምፒዮናው ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ

“የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ፣ በዓለም አቀፍ እና በኦሊምፒክ የውድድር መድረኮች በመሳተፍ ድል የተቀዳጁ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶች ተሳትፎ ያለፉበት እና የሚሳተፋበት አንጋፋ ቻምፒዮና” መሆኑን አስታውሰዋል።

የሻምፒዮናው ዓላማ እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 13-21/2025 በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲመዝኑ ፣ ለአትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር ፣ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በሽልማት ለማበረታታት መሆኑን በመግለጫው ተመላክቷል።

በተጨማሪም በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ኮርስ የወሰዱ 80 ዳኞች ውድድሩን የሚመሩ ሲሆን ለሻምፒዮናው በቂ በጀት መመደቡን ተጠቁሟል ።

በሻምፒዮናው 536 ሴት 843 ወንድ በአጠቃላይ 1379 አትሌቶች ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፣31 ክለቦችና ተቋማት እና ብዙ ታዋቂ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የሻምፒዮናው የመክፈቻ እና የመዝጊያ መርሀግብር በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቀጥታ የሚተላለፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘ ጋጃቸው ውድድሮች መካከል ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ1963 ዓ∙ም ነበር የተጀመረው። ውድድሩ ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል የቻሉ አትሌቶችን ማፍራት ዋነኛ ዓላማው ሲሆን፤ አንጋፋዎቹን አትሌቶች እነ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠርን ጨምሮ አሁን በውድድር ላይ እስካሉት ወጣት አትሌቶች ድረስ በርካቶችን አፍርቷል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You