መሶቦች ይበራከቱ!

ሕዝብ ከሚማረርባቸው ዘርፎ አንዱ እና ዋነኛው በየተቋማቱ ያለው የተንዛዛ አገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። ሕዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ ተቋማት ዋነኛ ተልዕኳቸው ረስተው ሕዝቡን ሲያንገላቱ እና ሲያማርሩ መታየት የተለመደ ነው። በዚሁ ምክንያት ቀልጣፋ መስተንግዶ እና አገልግሎት ማግኘት ብርቅ እስከ መሆን ደርሷል።

አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ለደንበኛ አገልግሎት ክብር ስለሌላቸው ሲስተም የለም በሚል ሰበብ ተገልጋይን ከፊት ማራቅን እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነው። ለተቸገረ ደንበኛ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ችግር እየፈጠሩ ከቢሮ እንዲርቅ የማድረግ ስልትን ይጠቀማሉ።

ተገልጋይ ክቡር ነው ከሚለው ዓለም አቀፋዊ መርህ በተቃራኒ ደንበኛን ማመናጨቅና ማጉላላት እንደ አዋቂነት የተወሰደ ይመስል። ለጉዳይ የመጣን ሰው ከፍ ዝቅ አድርጎ መመልከት የበርካታ ተቋማት መገለጫ እየሆነ ነው። ‹‹አይሆንም፤ አይቻልም›› የሚሉ ሃሳቦችን በመደርደር ደንበኛን ከፊት የማራቅና አልፎ ተርፎም በመንግሥት አገልግሎት ላይ እንዲማረር የማድረግ ስልት እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ መጥቷል።

አብዛኛዎቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አርፍዶ በመግባትና ቶሎ በመውጣት፤ ሕዝብን በማጉላላት፤ ምልጃ በመጠየቅ፤ በትውውቅና ዘመድ አዝማድ መሥራት፤ በማመናጨቅ ጭምር የተገልጋይን ቆሽት የሚያደብኑ መሆኑን የደረሰበት ያውቀዋል። ብዙዎችም ‹‹ሰው ጤፉ›› የሚባሉ ዓይነት ናቸው።

አገልግሎት አሰጣጥ ሳይንስ ነው፤ ጥበብ ነው አልፎ ተርፎም ተሰጥኦንም የሚጠይቅ ሙያ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ቅንነትን ይፈልጋል። የደከሙ እናቶችን፤ አካል ጉዳተኞችን፤ እርጉዞችን እየተመለከተ ግድ የማይሰጠው ሠራተኛ ወይም ኃላፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥበብ ገብቶታል ማለት አይቻለም። ወይም ደግሞ አገልጋይ ነኝ ብሎ ራሱን መቁጠር አይችልም።

ይህ ሰው ሳይንሳዊ እውቀቱ ቢኖረውም ቅንነት ካልታከለበት በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ የቀሰመው ዕውቀት የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን አያልፍም። ከራሱ ተርፎ ለማኅበረሰቡ ጠብ የሚል ነገር የለውም።

በርካታ ተቋማት የሥነ ምግባር መርሆች ብለው መግቢያ በራቸው ላይ ዝርዝር ነጥቦችን በማስታወቂያ መልኩ ይለጥፋሉ። 12 ሥነ ምግባር መርሆች ተብለውም ይታወቃሉ። ከእነዚህ ሥነ ምግባር መርሆች ውስጥ በተራ ቁጥር አንድ የሚቀመጠው ቅንነት ነው። ቅንነት የሁሉም ነገር መሠረትና መነሻ በመሆኑ ቅድሚያ መሰጠቱ አግባብ ቢሆንም አተገባበሩ እና ክትትሉ ላይ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

ቅንነት ተራ ቁጥር አንድ ሆኖ እንደ መቀመጡ የትኛው ሠራተኛ ነው በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በቅንነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆነው። እንደ ፋሽን በየቦታው የበዛው ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለው ምላሽስ ምን ያህል እውነተኛ ነው። ወይንስ ተገልጋይን ለማራቅና ለሙስና ለማመቻቸት ከቅንነት ውጭ እየተሠራ ያለ ሥራ ነው።

በየቦታው ተዘዋውሮ ለተመለከተው ኅብረተሰቡ ከተማረረባቸው ቃላት ውስጥ ‹‹ሲስተም የለም›› የሚለው ቀዳሚው ነው። ‹‹ኔት ወርክ የለም›› የሚለውን ቃል የሚሰማ ተገልጋይ ወሽመጡ ቁርጥ ይላል። ጉዳዩን ጨርሼ ቶሎ ወደ ሥራዬ እመለሳለሁ ብሎ ያሰበ ሁሉ ፊቱ በሀዘን ድባብ ይዋጣል። ሲስተም እስኪመጣ ድረስም ወዲህ እና ወዲያ እያሉ መጠበቅም ግድ ይሆንበታል። አብዛኛውም ተገልጋይ ሲስተም የለም የሚለው አባባል እውነት እየመሰለው ቀኑን ሙሉ ተገትሮ ሲውል ይታያል። ሆኖም የሙሰኞችን ኪስ እስካልሞሉ ድረስ ሲስተም መቼም እንደማይመጣ የሚረዱት ዘግይተው ነው።

ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለአገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ ማቅረብ ግዴታ ሲሆን ለተገልጋዩም መብት ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 እንደተደነገገው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12/2/ “ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠይቂ ይሆናል” በማለት ደንግጓል።

ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ የምንማረው አገልጋዩ ለተገልጋዩ መስጠት የሚገባውን አገልግሎት የሚሰጥበትን አሠራር ካልዘረጋ፣ በዘረጋው አሠራር መሠረት አገልግሎት ለመስጠት የገባውን ቃል ግልጽነትና ጥራት ባለው መንገድ ካልሰጠ እና የመንግሥት ሕጎችን፣ ደንቦችን መመሪያዎችንና አሠራሮችን ካልፈፀመ ወይም ካላስፈፀመ ተጠያቂ ይሆናል።

በዚህ መሠረት ሊሠጥ የሚገባው አገልግሎት ቃል ለተገባለት ሕዝብ/ዜጋ መድረስ አለመድረሱ ሲጋለጥ ቃሉን የጠበቀና ያሳካ የሚመሰገንበት፣ የሚበረታታበትና የሚሸለምበት አሠራር ሊኖር ይገባል። በአንጻሩ በገባው ቃል መሠረት ያልፈፀመ የሚመከርበትና የሚወቀስበት እንዲሁም ሆን ብሎ ያጠፋ ከሆነ ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የሚጠየቅበትና የሚቀጣበት ሥርዓት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።

የዚህ መርህ መሠረታዊ ቁም ነገር ዜጎች በቂ መረጃ ያላቸው ሆነው ተገቢውን አቋም መያዝ የሚያስችላቸው መሆኑ ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ መረጃ በማጣት ምክንያት ያለ አግባብ የሚፈጠር አለመግባባት፣ አለመተማመንና ጥርጣሬን ከማስወገዱም በላይ ስህተትን በቀላሉ ለማወቅና ለመፍታት የሚችልበት ሁኔታን መፍጠሩ ነው። አገልግሎትን ለተገልጋዩ ግልጽ ማድረጉ ሲስተም የለም እያሉ ለሚያጭበረብሩትም መፍትሔ ሳይሆን አይቀርም።

ግልጽነትን ከማስፈን በሻገር ቢያንስ የእያንዳንዱን ተቋም አሠራር መፈተሽ፤ መከታተልና መደገፍ የመንግሥት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል። ይህንኑ ችግር ለመፍታትም መንግሥት ተገልጋይ መስሎ (ምስለ ተገልጋይ )በተለያዩ ተቋማት እያደረገ ያለው ፍተሻ የሚበረታታ ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ሙሰኞችም ወደ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ሊጠናከር ይገባል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ግን በዋነኝነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ነፃ የሚሆኑበትን አሠራር መቀየስ ይገባል። በዚህ ረገድ ሰሞኑን ይፋ የሆነው የመሶብ አገልግሎት ተጠቃሽ ነው።

የመሶብ አገልግሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚሰጥበት አሠራር ነው። ይህ አሠራር ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ወይም ወደ ማዕከሉ በመምጣት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ሰዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር ነው። በዚህ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት የሰዎች ንክኪ ስለማይኖር አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ ከእንግልት እና ውጣ ውረድ ይድናል። ሙስናና እና ምልጃ ይቀራል። ግልምጫ እና ማመናጨቅ ተረት ሆኖ ይቀራል። ስለዚህም የመሶብ አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥ ለተማረረው ሕዝብ ፍትሁን መድኃኒት ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

መንግሥት ይህንን አገልግሎት ለዜጎች ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በርካታ ገንዘብ እና እውቀትም አፍስሷል። ሆኖም የዜጎችን እንግልት ከመቀነስ በላይ ትኩረት የሚሰጠው የተቀደሰ ተግባር የለምና መንግሥት የመሶብ አገልግሎትን ለዜጎቹ በገጸ በረከትነት አቅርቧል።

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተመረቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለዚህ ቁርጠኝነታችን አንዱ ማሳያ የሆነውን የመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከልን መርቀናል ብለዋል።

ይህን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የቆየ እና የተጎዳ ሕንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነ ውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደሆነ ሕንፃ መለወጡ አንዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አገልግሎቶችን ለመሰተር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍት ዌርም በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው ብለዋል።

12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን ይህም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት ያግዛል ነው ያሉት። እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉም አክለዋል።

መሶብን የመሳሰሉ ማዕከላት ወደ ሥራ መግባት ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን የሚያስቀር ነው። አገልግሎቶቹም ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ፋይዳ ዲጂታል የመታወቂያ ምዝገባ እና ሌሎችንም ያካተተ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

በአጠቃላይ በፓይለት ፕሮግራም በአንድ ስፍራ የ12 ተቋማት 41 አገልግሎቶች በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ተቋማቱም፦ የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት፤ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት፤ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፤ የገቢዎች ሚኒስቴር፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ኢትዮ ቴሌኮም፤ በቴክኖሎጂ አማካኝነት በትስስር አገልግሎት እየሰጡም ይገኛሉ።

መሶብን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረጉ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች ዜጎችን ርካታ ከመጨመሩም በላይ በተንዛዛ የአገልግሎት አሰጣጥ የሚባክነውን ጊዜ ለማዳን ያስችላል። የአገልግሎት አሰጣጥ መቀላጠፍ ወደ ኢኮኖሚው የሚገቡ ባለሀብቶችን ያበረታታል፤ ኢንቨስትመንትን ሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኢኮኖሚ መነቃቃቱ በሚፈጥረው ስሜትም ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት ያሳድራሉ፤ በዜጎች እና በመንግሥት መካከል መቀራረብን ይፈጥራል በአጠቃላይም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በር ይከፍታል። ይህ መሆኑ ደግሞ የሀገር ገጽታ ይለወጣል። ቱሪስቶችና ባለሀብቶች ወደ ሀገር እንዲመጡ ያነሳሳል።

ስለዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ከግለሰቦች እንግልት ወይም ምሬት ያለፈ ሀገራዊ ትርጉም ያለው ወሳኝ ጉዳይ ነው። የትኛውም ሀገር ቢሆን አገልግሎት አሰጣጡንም ሳያስተካከል እና ለዜጎችም ተገቢውን ክብር ሳይሰት ኢኮኖሚውን ማሳደግ፤ ፖለቲካውን ማረጋጋት እና ማህበራዊ መስተጋብሮችን ጤናማ ማድረግ አይችልም። ስለዚህም አገልግሎት አሰጣጥ መሳለጥ ለአንድ ሀገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት የማይተካ ሚና እንዳለው መረዳት ይገባል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You