“አምራች ኢንዱስትሪው አራቱ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ዕድገት እንዲያስመዘግቡ አይተኬ ሚና ተጫውቷል” -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- አምራች ኢንዱስትሪው የራሱ ዕድገት እንደተጠበቀ ሆኖ አራቱ የኢኮኖሚ ሴክተሮች እንዲንቀሳቀሱና ውጤት እንዲያስመዘገቡ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ 2017 ትናንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መርቀው ከፈቱ። አምራች ኢንዱስትሪው የራሱ ዕድገት እንደተጠበቀ ሆኖ አራቱ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ማለትም ግብርና፣ ማዕድን፣ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ሴክተሮች እንዲንቀሳቀሱና ውጤት እንዲያስመዘገቡ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቀየር የግድ ነው።ያልተቀየረ ኢኮኖሚ የጸና ሀገር ሊያቆም አይችልም የሚል እሳቤ ይዘን ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ እንደ ማስፈጠሪያ የወሰድነው አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ኢንዱስትሪውን በመቀየር፣ በማዘመንና ምርታማነቱን በማሳደግ ዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል በ10 ዓመቱ ዕቅድ ተካቶ ሲሠራበት መቆየቱን አውስተዋል።

በተለይ አምራች ኢንዱስትሪው በራሱ እንዲያድግ ብቻ ሳይሆን አራቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሶሶዎችን ድልድይ ሆኖ መቀየር፣ማዘመንና ማሳደግ እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የግብርናን ሴክተር ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት በስፋት እንዲያመርት አምራች ኢንዱስትሪው ድልድይ ሆኖ ግብዓቶችን በማቅረብ ረገድ ዕገዛ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመው፤ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የግብርና ማሽኖችን መገጣጠምና ማምረት የሚያስችል አቅም እየጎለበተ ሲመጣም ለዓመታት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለገቢ ምርት ሲያስወጣን የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ማስቻሉን በአብነት ጠቅሰዋል።

ሌላው የቡናን ምርታማነት ለማሳደግም የችግኝ ፕላስቲኮችብ፣ የመስኖ የውሃ መሳቢያ ፓንፖችን፣መኮትኮቻዎችን፣ መልቀሚያና መፍልፈያ ማሽኖችን በማምረት አምራች ኢንዱስትሪው ለግብርናው ዕድገት ድልድይ መሆኑን አመልክተው፤ ዘንድሮ 400 ሺህ ቶን ገደማ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ አግኝተናል።ይህም ለግብርና አንዱ የዕድገታችን ምሰሶ ሆኖ እንዲቆም ያደረገው አምራች ኢንዱስትሪው እንደሆነ አብራርተዋል።

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ ማዕድን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት።ነዳጅ፣ ወርቅ፣የብረት ማዕድን፣ ፖታሽና ሌሎች በርከት ያሉ የከርሰ ምድር ሀብቶች አሉ።እነዚህን ሀብቶች አውጥቶ ለመጠቀም አምራች ኢንዱስትሪው ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጻ፤ከሁለት ዓመት በፊት የሲሚንቶ ምርት ቀንሶ ዋጋውም ከፍ ብሎ እንቸገር ነበር።በአሁኑ ጊዜ ሲሚንቶ በሀገር ውስጥ ተጨማሪ ምርት ማምረት በመቻላችን የሀገር ውስጥ ፍጆታ ማሟላት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን።ኢትዮጵያ ወርቅ ማምረት የምትችልባቸው ማሽኖች ማምረት በመቻሉም በአሁኑ ጊዜ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ከቡና በልጦ ትልቁን የውጪ ንግድ ድርሻ ወስዷል።አምራች ኢንዱስትሪው ማዕድን የታለመውን ግብ ለማሳካትም የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በሦስተኛ ደረጃ የኢኮኖሚው ምሰሶ ያልነው ቱሪዝምን ነው።ቱሪዝም ውስጥ ኢትዮጵያ በርካታ ባህልና ታሪክ አላት።እነዚህን አዘምነን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ከገነባን ሊታዩ የሚገባቸው በርካታ ሀብቶች አሉን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቱሪዝም ዘርፍ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባትና ታሪካዊ ቅርሶች ማደስ ረገድ ኢንዱስትሪው አይተኬ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።በእዚህም በዘንድሮ ዓመት ቱሪዝምን በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ድርሻ ይዘናል ነው ያሉት።

አራተኛው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ምሰሶ ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመው፤ በሞባይል ኔትዎርክ ተደራሽነትን ማስፋት ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከል፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን፣ፋይዳንና መሰል የአውቶሜሽን ሥራዎች ለመሥራት የአምራች ኢንዱስትሪው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን ፍላጎት መልሷል ባይባልም አራቱን ሴክተሮች እንዲነቃቁና የሚጠበቅባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ ከሦስት ዓመት በፊት የማምረት አቅማችን 46 በመቶ ያህል እንደነበር አውስተው፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄውም የማምረት አቅምን አሁን ላይ 61 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የተናገሩት።ይህ ትልቅ የምሥራች እንደሆነ አመልክተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመንፈቅ በተለያዩ ምክንያት ያቆሙና የተዘጉ 830 ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ፣የተበተኑ ሠራተኞች እንዲሰበሰቡ መደረጉን ገልጸው፤ እንዲሁም ከአንድ ሚሊዮን እስከ 90 ሚሊዮን ኢንቨስት የተደረገባቸው 13ሺህ 800 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ባለፉት ሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ባለፉት 9 ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር ገዳማ ተኪ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሦስት ዓመት በፊት በሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የገበያ ድርሻ 31 ገደማ እንደነበርና አሁን 41 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት ሲጀመር የኢንዱስትሪው ዕድገት 5 በመቶ እንደነበር አውስተው፤ ባለፈው ዓመት 10 በመቶ ማደጉንና በያዝነው ዓመትም 13 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

አሁንም አምራች ኢንዱስትሪውን ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ አሁንም ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

ጌትነት ምህረቴ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You