የሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ አጓጊ ፉክክሮች

የ2025 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ባለፈው ሳምንት በቻይና ዚመን ተጀምረዋል። የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች ሁለተኛ መዳረሻ ከተማም በቻይና ሻንጋይ ዛሬ ሲካሄዱ በርካታ አጓጊ ፉክክሮች ይጠበቃሉ። በተለይም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉባቸው የተለያዩ ሦስት ርቀቶች የሚጠበቁ ሲሆን በርካታ አትሌቶችም ተሳታፊ ናቸው።

ዛሬ በሻንጋይ ከሚጠበቁ ፉክክሮች አንዱ በሴቶች 800 ሜትር የሚካሄደው ነው። በእዚህ ውድድር ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። ከወራት በፊት በናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ንግስት ጌታቸው ዛሬ ሻንጋይ ላይ የመጀመሪያ የዳይመንድሊግ ውድድሯን ለማሸነፍ ትፎካከራለች። የካቻምናዋ የርቀቱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮንና የፓሪስ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ፅጌ ዱጉማ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ነች። የወቅቱ የርቀቱ የዓለም አራተኛ ደረጃን የያዘችው ኮከቧ አትሌት ፅጌ ባለፈው የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለወርቅ ሜዳሊያ ትልቅ ግምት ተሰጥቷት በፍፃሜው ፍልሚያ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት አልቻለችም። ዛሬ ግን ያንን ቁጭቷን ሻንጋይ ላይ በማሸነፍ ለመወጣትና የወቅቱ የርቀቱ ኮከብ መሆኗን ለማሳየት ተዘጋጅታለች። በርቀቱ ብዙ ልምድ ያላት ሀብታም ዓለሙም በፉክክሩ ቀላል ግምት የሚሰጣት አትሌት አይደለችም። ወጣቷ አትሌት ሳሮን በርኸም በፉክክሩ የምትታይ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ትሆናለች። ዩጋንዳዊቷ የቀድሞ የርቀቱ ቻምፒዮን ሀሊማህ ናካዪ እንዲሁም አውስትራሊያዊቷ ሳራ ቢሊንግስ የኢትዮጵያውያኑ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በ5ሺ ሜትር ወንዶች በሚካሄደው ውድድር በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ የአሸናፊነት ግምቱም የተሰጠው ለእነሱ ነው። የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ኮከብ በሪሁ አረጋዊ ሻንጋይ ላይ ለድል የሚጠበቅ ዋነኛው አትሌት ነው። ባለፈው የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ካጠለቀ ወዲህ ዛሬ የመጀመሪያ ውድድሩን የሚያደርገው ወጣት አትሌት በርቀቱ ያለው 12:40.45 ፈጣን ሰዓትና አቅም ለአሸናፊነት አሳጭቶታል። ሌላኛው ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ኃይሌም ካለው 12:42.70 ፈጣን ሰዓት አኳያ ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናል። የ3ሺ ሜትር መሰናክል ስፔሻሊስቱ ጌትነት ዋለም ለአሸናፊነት ከሚፎካከሩ ጠንካራ አትሌቶች አንዱ ነው። ግርማ ኩማ፣ ኪዳኑ አታክልቲና መዝገቡ ስሜ በውድድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ኒኮላስ ኪፕኮሪርን ጨምሮ ፣ ኪምቦይ ኮርኔሊስና ቤንሰን ኪፕላንጋት በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ኬንያውያን ናቸው።

ዛሬ በሻንጋይ በጉጉት የሚጠበቀው ሌላኛው የትራክ ውድድር የ3ሺ መሰናክል ወንዶች ይሆናል። የውድድር ዓመቱ የዳይመንድሊግ ፉክክሮች ባለፈው ሳምንት በዚመን ሲጀመሩ በርቀቱ የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑን ሞሮኳዊ ሱፊያን ኤል ባካሊን በድንቅ ብቃት ማሸነፍ የቻለው ፍሬው ሳሙኤል የአሸናፊነት ግምቱን ወስዷል። ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ባለፈው ሳምንት ያሸነፈበትን 8:05.61 የራሱን ምርጥ ሰዓት ዛሬ 8:04.34 ማሻሻል ይፈልጋል። በዚህ ውድድር ይፈትኑታል ተብለው የሚጠበቁት ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው። ከሳምንት በፊት በመጀመሪያው የዳይመንድሊግ ፉክክር ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሳይመን ኪፕሮፕ ከባድ ተፎካካሪ ሲሆን፣ የርቀቱ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮን ኤድሙንድ ሳሬም እንዲሁም የኦሊምፒክ የርቀቱ የነሐስ ሜዳሊያአሸናፊ አብረሀም ኪቢዮት ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኑ ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው።

ባለፈው ሳምንት አምስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አትሌት ኃይለማርያም አማረና አብረሀም ስሜም በውድድሩ የሚፎካከሩ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሆናሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You