
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች ነው። ሂደቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ሕጋዊ መብቶች በማይጣረስ መልኩ እንዲከናወንም ድርድሮችን ለማድረግ እየጣረች መሆኑን በተከታታይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ‹‹WTO›› በሚል ሰያሜ የምናውቀው የዓለምን የንግድ እንቅሰቃሴዎች አስኳል የሆነው ድርጀት አባል መሆን የራሱ አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች እንዳሉት ይታወቃል።
የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል ኢትዮጵያ በተሟላ መልኩ የዓለም የንግድ ሥርዓት አካል እንድትሆን በር የሚከፍት ነው። አጋጣሚው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የተሻሉ አማራጮችን እንድታገኝ እና ከሌሎች ሀገሮች ጋር በድርጅቱ ሕግና ሥርዓት እንድትገበያይ ያስችላታል። በድርጅት ውስጥ አባል መሆን ሁሉንም ነገር አልጋ በአልጋ የሚያደርግ ሳይሆን የራሱ የሆነ ተግዳሮቶችን ይዞ የሚመጣ ነው።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም የግል ምልከታውን በማስቀመጥ፤ ዓለም አቀፍ ጥናቶችን በማጣቀስ ከዚህ እንደሚከተለው የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖችን ለመዳሰስ ይሞክራል። በቅድሚያ ግን ለጠቅላላው ግንዛቤ አንዲረዳን የዓለም የንግድ ድርጅት ተግባርና ኃላፊነቶቸን በጥቂቱ እመለከታለሁ።
የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) በጥር 1 ቀን 1995 የተመሰረተ ግዙፍ ተቋም ነው። የዚህ ሥርዓት መንበር ቀደም ሲል ይታወቅ የነበረውን እና እ.ኤ.አ በ1947 የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ጠቅላላ የንግድና የታሪፍ ስምምነት (GATT) የቆየ ሥርዓት የተካ ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት በሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ደንብ በማውጣት፣ በማረጋገጥ መብቶችንና የሕግ ጥሰቶቸን የመከላከል ሥራ ይሠራል።
ሀገሮች በንግድ ጉዳይ ላይ የደረሱትን ስምምነቶችና አለመግባባቶች አንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ለመቆጣጠርና ለመፍታት ይረዳል። በዚህ ምክንያት በርካታ ሀገራት በዚህ ሥርዓት ውስጥ እራሳቸውን አባል አድርገዋል፤ ዛሬ ላይ 164 ሀገሮች አባል ሆነዋል። እነዚህ ሀገሮች በዓለም ላይ አብዛኛውን የንግድ ልውውጥ በዚሁ ሥርዓት አማካኝነት ያደርጋሉ።
ስለ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን የመቀላቀል ሂደት የጀመረችው እ.ኤ.አ በ2003 እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፤ ሂደቱ ረጅም ጊዜን ፈጅቷል። ለመዘግየቱ ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህ አንዳንድ ምክንያቶች ውስጥ የቅርብ ግዜዎቹን ብንጠቅስ አንኳን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ የውስጥ ግጭቶች እንዲሁም በጥልቀት ሊዳሰሱና ሪፎርም ሊደረግባቸው የሚገቡ በሕግ ውስጥ ያሉ አዝጋሚ ለውጦች ማንሳት ይቻላል።
አሁን በተሟላ መልኩ ኢትዮጵያ እንደገና የድርጅቱ አባል ለመሆን እየሠራች ነው። በቅርቡ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን ብንመለከት መንግሥት አንዳንድ ሕጎችን እየቀየረ መሆኑን አንረዳለን። በተለይ አባል ለመሆን እንደ መስፈርት ከሚቀመጡት መካከል አንዱ የሆነውን የውጭ ኩባንያዎች በቴሌኮምና በፋይናንስ ሥራ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ ሂደት እየተተገበረ ነው። እነዚህ ማሻሻያዎችና ለውጦች የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ለመቀላቀል መደላደል እንደሚፈጥሩ ይታመናል።
ኢትዮጵያ አባል ለመሆን ከላይ ካነሳኋቸው ነጥቦችም በላይ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይኖርባታል። በተለይ የንግድ ሕጎቹን መለወጥ እና ከድርጅቱ መስፈርቶች ጋር ትስስር መፍጠር የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ማረጋጋጥ ያስፈልጋታል። እነዚህ ሕጎች ፍትሃዊነትን የሚያስቀድሙ እና ለዓለም አቀፍ ካምፓኒዎች ተወዳዳሪነት ክፍት የሆነ ግልፅ አሠራርን የሚከተሉ መሆን አለባቸው።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራትን እቃዎችን እና ምርትና አገልግሎቶችን በገበያዎቿ ውስጥ ያለገደብ (ሕጋዊ የሆኑትን) እንዲገቡና እንዲሸጡ መፍቀድ አለባት። ሌላው የአዕምሯዊ ንብረት (የብራንድ ስሞችን) ምርቶችን እና ባለቤቶቸን መብት የሚያስጠብቅ ጥብቅ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ሊኖራት ይገባል። በዚህ ሂደት ውስጥ በሚፈጠር የንግድ አለመግባባት ሀገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅት ሕግ ለመከተል እና በዚያ መሰረት አለመግባባቶቹን ለመፍታት መስማማት አለባት።
መልካም ጎኖቹ ምንድናቸው
ሀገራችን የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ በርካታ ጥቅሞች አንዳሉት አምናለሁ። አንዱ እና ዋንኛው ጥቅም የኢትዮጵያ ምርቶች በሌሎች ሀገሮች በቀላሉ መሸጥ መቻላችን ነው። ይህን መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማረጋገጥ መቻል ገበሬዎችን፣ ፋብሪካዎችን እና አነስተኛ ንግዶችን ይረዳል። በተለይ የውጪ ምንዛሬን በማሳደግ፣ የተሻለ የሽያጭ ሥርዓትን በመዘርጋት እና ጤናማ የንግድ ሰንሰለት በመፍጠር ለሀገሪቱ ተጨማሪ ሀብት ሊያመጣ ይችላል። ሌላው ጥቅም ብዙ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ፍላጎት አንዲኖራቸው የዚህ ድርጅት አባል መሆናችንና በተቀመጠው መርሆ መተዳደራችን ትልቅ ፋይዳ አለው። ኢንቨሰትመንት መስፋፋቱ ደግሞ ለወጣቶች የሥራ እድል በስፋት ይፈጥራል።
ሌላው የንግድ ችግሮች (ለምሳሌ በጤፍ የባለቤትነት መብት እና በቡናና በመሳሰሉት ጉዳዮች የተከሰቱና የሚከሰቱ ችግሮች) ሲከሰቱ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ሕጎችና ሥርዓቶች ተገን በማድረግ ጥሰቶቹን ለማስተካከል ይረዳታል። ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ንግድ ድርጅት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ ሀገሮች የሚሰጠውን እርዳታና ድጋፍ፣ ሥልጠና እንዲሁም ሌሎች ተሞክሮዎችን ያለገደብ ማግኘት ያስችላታል።
ከእነዚህ ቁልፍ ጥቅሞች አንፃር ስመለከተው ሀገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ በብዙ መንገድ እንድትጠነክር ያግዛታል ብዬ አምናለሁ። በዚህም ሀገሪቱ በፍጥነት እንድታድግ ከሚያግዛት መንገዶች ውስጥ አንዱ ይህን መሰል ሥርዓት ነው። ለዚህ ነው ዜጎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እና በዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ ያለገደብ እንዲካተቱ በሚያግዘው ስልት ውስጥ ድርሻ ሊኖራቸው የሚገባው። በተለይ አባል የመሆን ትሩፋቶቹን ተጠቅመው ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ ማስቻል የመንግሥት የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
አሉታዊ ጎኖቹስ?
የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል እንዲሁ ቀለል አድርገን መውሰድ አይገባንም። በአንክሮ ልንመለከታቸው የሚገቡ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም ልብ ልንል ይገባል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ አባል ሀገር በምትሆንበት ሰዓት አንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ ትናንሽ ሀገር በቀል ኩባንያዎች እስከ መክሰም የሚያደርስ የሕልውና ስጋት ሊጋረጥባቸው ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ ድርጅቶችና ካምፓኒዎች ከትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች ጋር መወዳደር ሊያቅታቸው ይችላል። ለዚህ ነው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግና ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስፈልገው። በተለይ መንግሥት እነዚህን የሀገር ውስጥ ንግዶች ማበረታታት መደገፍ የሚያስችለው የአሠራር ሥርዓት እንዲኖር ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ ይገባል። በተለይ ይህ ውሳኔ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ድሆችን እና አርሶ አደር ገበሬዎችን ሊጎዳ አንደሚችል ታውቆ በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
ሌላው ተግዳሮት የሕግ ማሻሻያ ነው። ቀደም ሲል የነበሩትን ሕጎች መለወጥ ብዙ የፋይናንስ አቅም እና ጊዜን ይወስዳል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የአሠራር ሥርዓትና የሕግ ማሻሻያ ለመተግበር ሀገሪቱ ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና ሥርዓቶችን ማሻሻል ይጠበቅባታል። አንደሚታወቀው መሰል ማሻሻያዎችን ማድረግ ቀላል አይደለም።
ዓለም አቀፍ ጥናቶች ምን ይላሉ?
ዓለም አቀፍ ጥናቶች የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎኖች እንዳሉት ያሳያሉ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ 2022 የዓለም ባንክ ያወጣው ጥናት በንግድ ሥርዓት ውስጥ የዓለም ገበያን በተሟላ መልኩ ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥብቅ እቅድ ያላቸው (ያደጉና ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው) ሀገራት ከዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት የበለጠ ትርፍ የሚያገኙ እንደሆነ ያትታል። ይሁን እንጂ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው እና መሰል እቅድ መንደፍና መወዳደር የማይችሉ ሀገሮች በዚህ ድርጅት ውስጥ አባል በመሆናቸው ብዙ ትርፍ እንደማያገኙ ያሳያል። ጥናቱ ‹‹ድሀ ሀገሮች ልዩ ድጋፍና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል›› በማለት ምክረ ሀሳቡን አስፍሯል።
ሌላው ሳይንሳዊ ጥናት በተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) የተደረገ ነው። ጥናቱ ‹‹ታዳጊ ሀገራት ለዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት እና የንግድ እንቅስቃሴ የውስጥ ፖሊሲዎቻቸውን እና ገበያቸውን ቀስ ብለው መክፈት አለባቸው›› በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ይሰጣል። ከዚህ በተቃራኒ ሆነው በጣም በፍጥነት ገበያቸውን ከከፈቱ ትናንሽና በማደግ ላይ ያሉ ሀገር በቀል ካምፓኒዎቻቸውን ሊያጡ ይችላሉ ሲል ያሳስባል። በተለይ ጥናቱ ሥርዓቱ ኢትዮጵያን በአነስተኛ ግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮችንና የንግድ ሥራዎችን እንዳይጎዳ ልትጠብቅ እንደሚገባ ይገልፃል። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ ሕጎቿን ለመለወጥ ጊዜ መውሰድ አንዳለባት እና ቀስ በቀስ ማሻሻል እንደሚጠበቅባት ምክረ ሀሳቡን አስፍሯል።
በ2023 በአፍሪካ የንግድ ፖሊሲ ማዕከል የተደረገ ጥናት ደግሞ ይህንን ስጋት ለመከላከል ኢትዮጵያ ጠንካራ ሕጎችን ማውጣት አለባት ብሏል። በተጨማሪነትም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጥምረት መሥራት አለባት ብሏል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የሚመጣውን ስጋት ለመቀነስና በተሻለ ሁኔታ ለመገበያየት እንደሚረዳ ያመለክታል። ይሁን አንጂ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ማበጀት ከተቻለ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት መሳብ እንድትችል ያግዛታል የሚል አዎንታዊ ምልከታንም አጋርቷል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ታዳጊ ሀገሮችን የሚጠቅም መሆኑን በአንዳንድ ባለሙያዎች ይታመናል። ይሁን አንጂ እነዚህ ባለሙያዎች ታዳጊ ሀገራቱ ዜጎቻቸውን ከስጋት ለመታደግ የራሳቸውን እቅድ ማውጣት ይገባቸዋል ይላሉ። በተለይ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል በመሆን በሚመጡ ተጨማሪ የንግድ ልውውጦች እና የሚሻሻሉ ሕጎች ምክንያት ለጉዳት ለሚጋለጡ ድርጅቶችና ዜጎች ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ድጋፍ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ አባል ለመሆን የሚያስችሉ መደላድሎችን ለመፍጠር ተጨማሪ ጊዜ መውሰድ አለባት ብዬ አምናለሁ። በተለይ ከድርጅቱ ጋር ለመሥራት በልዩ ሁኔታ በአንዳንድ ጉዳዮች ጋር በድርድር (በሰጥቶ መቀበል መርህ) መስማማት ይኖርባታል። በተይ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በማደግ ላይ ያሉ ንግዶች፣ ካምፓኒዎችና ድርጅቶች (ከባለቤቶችና ሠራተኞች ጋር ጭምር) ሰፊ ውይይት ማድረግ ይገባል። በተለይ የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባል መሆን ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ ማብራራት ይገባል። ይህንን ማድረግ ሲቻል በፍጥነት የሚመጡ ለውጦቹን ዜጎች እና የንግድ ድርጅቶች መረዳት እና ለለውጡም ድጋፋቸውን መስጠት እንዲችሉ ይረዳል።
በግሌ እንደማምነው የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል ትልቅ የእድገት እድል ነው። ነገር ግን ውሳኔውና አተገባበሩ በጥንቃቄ መከናወን አለበት። ትግበራው በትክክል ሀገራዊ አንድነትን በሚያስጠብቅ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርና የአሠራር ሥርዓትን በሚከተል መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከተሠራ ኢትዮጵያ ካደጉት ሀገራት ተርታ አንድትሰለፍና እንድትበለጽግ ይረዳታል።
እንደሚታወቀው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ለሀገሮች መብትና ግዴታ ይሰጣል። ከዚህ ውስጥ አባላት በሌሎች ሀገሮች እቃዎችን የመሸጥ መብት አላቸው። በሀገራቸው ውስጥም ተመሳሳይ ሥርዓትን ማስፈፀምና የመከተል ግዴታ አለባቸው። አባላት በግብይቱ ውስጥ እርስ በርሳቸው በፍትሃዊነት መመራት አለባቸው። በንግድ ውስጥ ማጭበርበርን የሚፈቅዱ አሰራሮችን ማስወገድ ይገባቸዋል። የሌሎችን ሀገራት ሕግንም ማክበር አለባቸው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት አነዚህን መርሆዎች ማስጠበቅ አንደሚችል ማረጋገጥ ይገባል።
ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንክሮ መሥራት አለበት። በተለይ የጉምሩክ ቢሮዎችን ማሻሻል ይጠበቅበታል። ዜጎች (ነጋዴዎች) በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ እንዴት ሕጋዊ ሥርዓትን ጠብቀው እንደሚሠሩ ማስተማር አለበት። ሌላው በዚህ ሥርዓት መምጣት ጉዳት ለሚደርስባቸው አነስተኛ አቅም ላላቸው ንግዶችን የጥበቃ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል።
የዓለም የንግድ ደርጅት ከመቀላቀል አስቀድሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች መሰል ሀገሮች መማር ይኖርባታል። ሩዋንዳ እና ካምቦዲያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ተቀላቅለዋል። በውጤቱም ጥብቅ ሕግና ሥርዓት ዘርግተዋል። እድሉን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለማግኘት ተጠቅመውበታል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ተሞክሮ መውሰድ ትችላለች።
በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዳይዋጡ ለመርዳት መንግሥት የሴፍቲኔት ሥርዓትን ማጠናከር ይገባዋል። በተለይ በትግበራ ሂደቱ ሥራ ለሚያጡ ዜጎች የድጎማ ገንዘብ (መቋቋሚያ) መስጠት አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በሌላ መልኩ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን እና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር ተፅእኖውን በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ኢኮኖሚው እንዲያድግ በር ይከፍታል።
ሌላው የመገናኛ በዙሀን ሚና ነው። ተቋማቱም ሆኑ ጋዜጠኞች በዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን እውነታ ማስረዳት ይገባቸዋል። በተለይ አባል ከመሆን ጋር ተያይዞ ያለውን ጥሩም ይሁን መጥፎ ጎኖች ማሳየት ይገባል። ይህንን ማድረግ ብዥታ እንዳይፈጠር እና መንግሥት ለመተግበር እያደረገ ያለውን ሂደት ዜጎች እንዲያምኑ ይረዳቸዋል።
ሌላውና ዋናው ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም ለመገንባት ወጣቶች ስለ ንግድ ሥራም መማር ይኖርባቸዋል። ትምህርት ቤቶች ስለ ንግድ በተለይም ‹‹በዓለም የንግድ ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ ተሳትፎ ውጤታማ መሆን እንዴት እንደሚቻል›› እውቀት ማስጨበጥ አለባቸው። ይህ ዜጎችን ለወደፊቱ ተወዳዳሪ አቅም እንዲፈጥሩ ያዘጋጃል።
መንግሥት ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት ይኖርበታል። በተለይ የሕግ፣ የአሠራር እና ለዓለም ገበያ ክፍት ከመሆን አንፃር የሚወሰዱ እርምጃዎችን ቀስ በቀስ ግዜ ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል። ይህን ሁሉ በጥንቃቄና ሳይንሳዊ ሂደቶችን ተከትሎ የሚያደርግ ከሆነ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሻለ ሕይወት ያመጣል። ነገር ግን ሂደቱን በተለይ የሀያላን ሀገራት ጫና ቀላል አያደርገውም። ለዚህ እራስን በሚገባ ማዘጋጀት ይገባል። በዕቅድና በጠንካራ ስልት አካሄዳችንን ካሳመርን ኢትዮጵያ ጠንካራ የዓለም የንግድ ሥርዓት አባል እና ተጠቃሚ መሆን ትችላለች የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ አይሆንም። ሰላም !!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም