20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

  • ጉባኤው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትደምቅ ሌላ እድል የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፡- 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትደምቅ ሌላ እድል የሚፈጥር መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ:: ጉባኤው ከግንቦት 11 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተጠቆመ::

ሚኒስትሯ ጉባኤውን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ሁነቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናና የኮንፈረንስ ማዕከል መሆኗን የምታሳይበት ነው:: ይህም ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድትደምቅ ሌላ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር ሆና እንድትመረጥ ያደረጓት ምክንያቶች መካከል ለአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በሰጠችው ትኩረት፣ በመንገድ መሠረተ-ልማትና በሌሎች ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት መሆኑን አንስተው፤ ለአካባቢ ጥበቃና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አመች ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራች መሆኑም በተጨማሪነት ጠቅሰዋል::

ጉባኤው ሀገራዊ መሠረተ-ልማት እንዲስፋፋና ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር፣ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ ሰውና አካባቢ ተኮር የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና ኢንቨስትመንቱ በመሳብ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ ዕድሎች አሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል::

በጉባኤው ከአምስት አህጉራት የተውጣጡ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎች እንደየሀገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ተሞክሮዎቻቸውን ያካፍላሉ። ኢትዮጵያም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በአካታች እና ዘላቂ ልማት ረገድ እያስመዘገበች ያለችውን ውጤት ለአፍሪካ እና ለዓለም ለማስተዋወቅ እድል እንደምታገኝ ጠቁመዋል::

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ፣ አዲስ አበባን ከተማ አስደናቂ ለውጥና የኮንፈረንስ ፋሲሊቲዎች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሀገራችንም ሆነች አዲስ አበባ ተመራጭ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ እንደሆነች ለማሳየት እድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል::

በዓለም ሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ካምቡላ ናዳባ በበኩላቸው፤ ጉባኤው ኢትዮጵያ ራሷ የምታሳይትና ኢንቨስትመነት ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ነው ብለዋል::  የጉባኤው በዓለም ሥራ ድርጅትና በተመረጠው ሀገር ትብብር እንደሚዘጋጁ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በ19ኛው ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፍተኛ ድምጽ በመመረጧ የዘንድሮው ጉባኤ አዘጋጅ መሆኗ ጠቁመዋል::

ባለፈው ዓመት ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ49 ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በ20ኛው አህጉራዊ ጉባኤም በርካታ ሚኒስትሮች፣ የተቋማት ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም ተሳታዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ብለዋል::

ኢትዮጵያ 17ኛውን ጉባኤ አስተናግዳ እንደነበር ጠቁመው፤ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ ጉባኤዎች ላይም ስትሳተፍ ቆይታለች:: ለጉባኤው አዲስ ባለመሆኗ በአጠቃላይም መሰል ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት ካላት ተሞክሮ አንጻር ጉባኤው የተሳካ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል::

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ፤ ጉባኤው የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች ሰውና አካባቢ ተኮር የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ይመላከትበታል:: በሚደረጉ ውይይቶችም በተለያዩ ሀገራት ያሉ መልካም ተሞክሮዎች ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል::

ጉባኤው በሁለት ዓመት አንዴ እንደሚካሄድ የተጠቆመ ሲሆን፤ 20ኛው አህጉራዊ ጉባኤ “የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል::

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You