ባለሀብቶች ለምገባ ማዕከላት ግንባታ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገዋል

  • በማዕከላቱም ከ37 ሺህ በላይ ዜጎች እየተመገቡ ነው

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ግንባታ ብቻ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። በከተማዋ በባለሀብቶች በተገነቡ በ26 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ከ37 ሺህ በላይ የዕለት ጉርስ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እየተመገቡ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶች በከተማዋ በቀን አንድ ጊዜ ተመግቦ ማደር ለማይችሉ ዜጎች የምገባ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ገንብተው ዜጎችን በመመገብ የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት በወጉ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ የማስተባበር ሥራ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የምገባ ወጪን ሳይጨምር ለተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ግንባታ ብቻ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገዋል ብለዋል።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ “አዲስ አበባ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉና ተመግቦ ለማደር በቆሻሻ ውስጥ የወዳደቀ ምግብ ሲፈልጉ የሚስተዋሉ ዜጎች የሚኖርባት ከተማ ልትሆን አይገባም” የሚል ጽኑ አቋም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይዘው፤ በርሳቸው ሃሳብ አመንጪነትና ቆራጥ አመራር ሰጪነት የመጀመሪያው የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አራት ኪሎ አካባቢ በ2013 ዓ.ም ተቋቁሟል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከተማ አስተዳደሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በወጉ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ በማስተባበር የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላትን እንዲገነቡ፣ እንዲያስፋፉ፣ እንዲያዘምኑ መሥራቱን አመልክተው፤ በቀን አንድ ጊዜ ተመግበው ማደር የማይችሉ ዜጎችን በማዕከላቱ አቅፈው እንዲመግቡ የተቀናጀ የማስተባበር ሥራ በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ከሰሞኑ የትንሳኤ በዓልን ታሳቢ ተደርጎ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት የገቡትን ጨምሮ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት 26 መድረሳቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በ 11ዱም ክፍለ ከተሞች በባለሀብቶች በተገነቡ በ 26ቱ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ከ37 ሺህ በላይ የዕለት ጉርስ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ለማዕከላቱ ግንባታ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ከማድረጋቸው ባሻገር በዓመት በአንድ የምገባ ማዕከል ለምገባ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ስንታየሁ አስገንዝበዋል።

ማዕከላቱ ዜጎች በነጻ የሚመገቡባቸው ከመሆናቸው ባሻገር ልዩ ልዩ ክህሎት ላላቸው ዜጎች የሥራ እድል ቋትና የኢኮኖሚ አቅማቸውን የሚገነቡበት ቦታ ሆነዋል የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ በ26ቱ ማዕከላት የሚመገቡ ዜጎች የተረጅነት ሥነ-ልቦና እንዳያዳብሩና የኢኮኖሚ አቅማቸው ጎልብቶ ከተረጅነት ወጥተው የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ልዩ ስትራቴጂ ተቀርጾ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በርካታ ተመጋቢዎች በየዓመቱ በገዛ ፍላጎታቸው ከተመጋቢነት ወጥተው ወደ ሥራ ፈጣሪነት እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በተመሳሳይ በተያዘው በጀት ዓመት 500 የሚደርሱ ተመጋቢዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው በገዛ ፈቃዳቸው ከተረጅነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በምገባ ማዕከላቱ የምገባ አገልግሎት እያገኙ ካሉ ዜጎች ውስጥ በገዛ ፈቃዳቸው ከተረጅነት ወጥተው የራሳቸውን የሥራ እድል ፈጥረው ለመሥራት የሥነ-ልቦና ዝግጁነትና አቅሙ ላላቸው 316 ሴቶች 3 ነጥብ 16 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ሠርተው ለመለወጥ የሚያግዛቸው ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶችን እንደየፍላጎታቸው ከሰሞኑ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You