
ኃይለኛው እሸቴ (ዶ/ር) ይባላሉ። የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ናቸው። በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባዮ ሜዲካል ተመራማሪ ሆነው ረዘም ላሉ ዓመታት አገልግለዋል። የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል። የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሲያከናውነው የነበረውን የኤች አይቪ ኤድስ ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ ፕሮጀክት ዳይሬክተር በመሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ባለፉት ዓመታት የእናቶች እና ሴቶች የሥነተዋልዶ ጤና ጉዳይ ላይ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሙያን ተጠቅመው በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲፈጠር የላቀ ድርሻ ወስደው እየሠሩ ይገኛሉ። ከስደት ተመላሽ ሴቶች እንዲቋቋሙ፣ እናቶችና ሴቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ቀርፀው በሚመሩት ድርጅት ውስጥ የተግባር ሥራ ይሠራሉ። በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን በመወከል ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ፣ የምርምር ውጤቶቻቸውን በጆርናሎች ላይ በማሳተም ተሳትፈዋል። በዛሬው «የሕይወት ገጽታ» አምዳችን ላይ የእኚህን ሰው ልምድ ማካፈል ብንችል ብዙ ወጣቶችን ሊያስተምር ይችላል በሚል እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ !
ትውልድና እድገት
ብዙዎች የኢትዮጵያ የንግድ እምብርት ይሉታል። ከመሸጥ ከመለወጥ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብሩ፣ የኢትዮጵያን ሁሉንም መልኮች የሚያሳይ ድባብ መኖሩ ከተወዳጅ ሥፍራዎች መካከል ቀዳሚው አድርገውታል። ብዙ ሺህ ሰዎች በቀን ወጥተው ይገቡበታል፣ ሸጠው ይሸምቱበታል። ታዲያ ይህ ሥፍራ እሳት የላሱ ነጋዴዎችን ብቻ አላፈራም፤ ይልቁኑ ለሀገር ባለውለታ የሆኑ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎችን ጭምር ያዋጣ ተወዳጅ ሰፈር ነው፤ መርካቶ።
ኃይለኛው እሸቴ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ተደርጎ በሚቆጠረው መርካቶ አካባቢ ነው የተወለዱት። በአካባቢው ተወልደው ያደጉ ብዙዎች በንግድ ሥራ ይሳባሉ። ርሳቸው ግን ሸጦ ከማትረፍ አሊያም የግል ሥራዎች ላይ ከመሠማራት ይልቅ የትምህርት ዘርፉ የበለጠ የሳባቸው ይመስላል። የመርካቶ ማራኪ ግርግር፣ ከልጅነት ጀምሮ ብዙዎችን የሚያጓጓው ገንዘብ ቀልባቸውን የወሰደው አይመስልም።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ያቀኑት፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ልዑል ወሰን ሰገድ በሚባል ትምህርት ቤት ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አሁን አዲስ ከተማ የቀድሞው ልዑል መኮንን እየተባለ በሚጠራ ትምህርት ቤት ነበር። በትምህርት ብቃታቸው አስፈላጊውን ደረጃ ይዘው ያለሙትን ሊያሳኩ፣ ያሰቡት ሊደርሱ በመሻታቸው በትምህርታቸው ገፍተውበታል።
በወቅቱ በርሳቸው የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ሊያሳኩት የሚሹት አንድ ህልም አለ። በጊዜው የከፍተኛ ትምህርት ልቆ መገኘት ከቤተሰብ፣ ከአካባቢ ማህበረሰብ እና ከሕዝቡ ከፍተኛ ከበሬታን የሚያጎናፅፍ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ዩኒቨርሲቲ የነበረ በመሆኑ በዚያ ተወዳድሮና ልቆ ተገኝቶ ስኬታማ መሆን አስቸጋሪ ነበር። ስለዚህ ወጣቶች በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እየተባለ በሚጠራው በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባት ህልም ነበራቸው። ይህንን የትምህርት ስኬት ከግብ ማድረስ ከቻሉ የጊዜው ባለድል ወጣቶች መካከል ደግሞ ኃይለኛው እሸቴ (ዶ/ር) አንደኛው ነበሩ።
ወቅቱን መለስ ብለው እያስታወሱ የሚናገሩት እንግዳችን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከመላው ሀገሪቱ የ12ተኛ ክፍል ፈተናን ተፈትነው ማለፍ የሚችሉ ወጣቶች የሚቀላቀሉበት ብቸኛው ዩኒቨርሲቲ ነበር በማለት ርሳቸውም የዚህ እድል እጣ ተካፋይ እንደሆኑ ያስረዳሉ። በ1964 ዓ.ም የመልቀቂያ ፈተናቸውን ወስደው በ1965 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉት እንግዳችን በጊዜው የመቀበል ኃይሉ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት በዓመት ከ1500 እስከ 2000 ተማሪዎች ብቻ ይገቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ወደዚያ ለመግባትም ብዙ ፉክክር እንደሚደረግ ያስረዳሉ። ይህንን እድል ያገኙት በርካታ ተፈታኞችን ተወዳድረው በማለፍ መሆኑንም ይገልፃሉ።
‹‹በጊዜው መልቀቂያ ፈተናው ላይ ብቻ ሳይሆን ግቢ ውስጥም ከፍተኛ ፉክክር ነበር›› የሚሉት እንግዳችን፤ የመጀመሪያ ዓመት ላይ በሴሚስተሩ ጥሩ ውጤት ያላመጣ በተለምዶ ክሪስማስ (የገና ማዕበል) እየተባለ በሚጠራው ፈተና ብዙ ተማሪ ይባረር እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያት በትምህርት ጠንክሮ መሥራት፣ ትኩረትን ያለማጣትና ፉክክሩ ላይ ልቆ መገኘት የግድ እንደነበር ይናገራሉ።
ኃይለኛው (ዶ/ር) በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነበራቸው ቆይታ ከትምህርት ባሻገር በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ ምክንያት እክል ገጥሞት ነበር። በጊዜው በተማሪዎች ንቅናቄ፣ በደርግ አብዮት እና በወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ተረጋግቶ ትምህርትን መከታተል አስቸጋሪ ነበር። በተለይ ዋና የፖለቲካው፣ የሕዝቡን ብሶትና የመብት ጥያቄ አቀንቃኞች ከፊት በመሆን የሚመሩት ተማሪዎች በመሆናቸው በእነሱ ላይ ብዙ እንግልትና እስር ይደርስ ነበር። እንግዳችንም የዚህ እጣ ፈንታ ሰለባ ነበሩ። በተለይ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል። ይህ ችግር የርሳቸው ብቻ ሳይሆን የወቅቱ ሁሉም ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ነበር።
በ1966 ዓ.ም የንጉሡ ሥርዓት ማብቂያ መሆኑ ሲታወጅ ከልጅነታቸው የተጉበት የትምህርት እቅዳቸው ፈተና ገጥሞታል። የደርግ መንግሥት ያወጀው የእድገት በሕብረት ዘመቻ ተካፋይ የመሆን ግዴታ ስለነበር ትዕዛዙን ተቀብለው ርሳቸውም ልክ እንደ አቻዎቻቸው መቀላቀል ነበረባቸው። ‹‹በዘመቻው የተሳተፍኩት እና ያገለገልኩት በወላይታ ሱባ በምትባል ቀበሌ ነው›› የሚሉት እንግዳችን እነዚህ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቀድመው ሊጨርሱት የሚገባውን ትምህርታቸውን እንዳስተጓጎለው እና ከሰባት ዓመት በኋላ መጨረሻቸውን ይናገራሉ። ኃይለኛው (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በባይሎጂ ትምህርት ነው።
ያስተማረን ወገን ማገልገል
እንደ ዛሬው የተማረ የሰው ኃይል በሚፈለገው ብዛት በሌለበት በዚያን ወቅት ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ምሩቅ መሆን በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል። የወጡበትን ወገን ማገልገል ደግሞ ለግለሰቡም ይሁን ለቤተሰብ ክብር ነው። በጊዜው እንግዳችን በባዮሎጂ ትምህርት ተመርቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ያስተማራቸውን ወገንና ሀገር ለማገልገል ቁርጠኛ ነበሩ።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የዘወትር ህልማቸው ወደ ሆነው ማህበረሰብን በሙያና እውቀታቸው የማገልገል ኃላፊነት ነበር ያቀኑት። በጊዜው በተመረቁበት ሙያ የተመደቡበት በጊዜው የኢትዮጵያ ጤናና ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት (ፓስተር ኢንስቲትዩት) በአሁኑ ስያሜው ደግሞ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተባለ በሚጠራው መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ ነበር። በዚህ መሥሪያ ቤት ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ከ እኤአ ከ1980 እስከ 1996 ድረስ ለ16 ዓመታት በምርምር ሙያ አገልግለዋል።
በኢንስቲትዩቱ ማህበረሰባቸውን የማገልገል እድሉን እንዲያገኙ ያስቻለው አንዱ ምክንያት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የመመረቂያ ጽሑፋቸው ከምርምር ሥራዎች ጋር የተያያዘ ርእሰ ጉዳይ በማንሳቱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ተማሪ ቤት በነበሩበት በእዚያን ወቅት መመረቂያ ጽሑፋቸው ለማጠናከር በኢንስቲትዩቱ በተደጋጋሚ ይገኙ ነበር። አማካሪዎች በሚያደርጉት ውይይት ምክንያት በመሥሪያ ቤቱ ለማገልገል ሁኔታዎች ምቹ ነበሩ።
የምርምር ሥራ
ኃይለኛው (ዶ/ር) የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንደተቀላቀሉ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ምርምር ሥራ ውስጥ ነው የገቡት። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የምርምር ቆይታቸው በተለያዩ የቆላ በሽታዎቸ በሚባሉ (ትሮፒካል ዲዚዝ) እንደ ብልሀርዚያ፣ የወባ በሽታ በጥገኛ ትላትሎች እና በመሳሰሉት በሽታዎች ላይ በርካታ ምርምር ማድረግ ችለዋል።
የመጀመሪያዎቹ የሥራ ዘመናት የወጡበትን ማህበረሰብ ያገለገሉበትን፣ የሙያ በኩር ጅማሬን ያዩበትን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ይህ መሠረት በዲግሪ ትምህርት በምርምር ሥራ ከመቀጠለ ባሻገረ ለተጨማሪ ዓመታት ራሳቸውን በትምህርት እንዲያዳብሩና የበለጠ የእውቀት ትጥቅ ለመታጠቅ እንዲያልሙ በር የከፈተላቸው ነበር። በኢንስቲትዩቱ ለአራት ዓመታት እንደሠሩ በነበራቸው ውጤታማ ቆይታ ምክንያት በአሜሪካን ሀገር የትምህርት እድል አግኝተው ወደዚያው ያቀኑት።
አሜሪካ በቱሪን ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት እንደደረሱ ቀደም ሲል በኢንስቲትዩቱ ሲያደርጉት በነበረው የትሮፒካል ቆላ በሽታዎች እና በሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ላይ በማተኮር ነበር ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት። ቆይታቸውን ያደረጉት በዓለም የጤና ድርጅት ባገኙት ድጋፍ የነበረ ቢሆንም በዚያው እያሉ ግን ተጨማሪ የሁለት ዓመት ድጋፍ በማግኘታቸው ምክንያት ሁለት ትምህርት ለመማር ወሰኑ።
በአሜሪካን ሀገር በቆዩበት በእነዚያ ዓመታት የማስተር ኦፍ ሳይንስ ትሮፒካል ዲዚዝ እና ፓራስቶሎጂ (ከጥገኛ ህዋስ) ጋር በተያያዘ ሲሠሩ ከዚህ ጎን ለጎን ያገኙትን ድጋፍ ተጠቅመው በማስተር ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ በኢፒዲሞሎጂ መመረቅ ችለዋል። በቆየታቸውም የፒ ኤች ዲ እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ግን ከመሥሪያ ቤታቸው ጋር የነበራቸውን ስምምነት ለማፍረስ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
«የገባሁትን ቃል ጠብቄ ሀገሬ ገብቼ ማገልገልለ ስለነበረብኝ ወደ ኢትዮጵያ መጥቻለሁ» በማለት የነበራቸውን ቆይታ ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ተመልሰው በምርምር ሥራ መቀጠላቸውን ይናገራሉ። በጊዜው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ረሃብ የተከሰተበትና ብዙዎች በድርቁና በረሃቡ ምክንያት ፈተና ውስጥ የወደቁበት ነበር። እርሳቸውም የራሳቸውን ፍላጎት ከማስቀደም ይልቅ የሀገራቸውን አደራና ኃላፊነት ለመወጣት በቅተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ቀደም ሲል ይሠሩበት በነበረው የምርምር ሥራ ሳይሆን በሌላ የምርምር መስክ ላይ ነበር የተሠማሩት። እንደሚታወቀው ወቅቱ የኤች አይ ቪ ኤድስ አሳሳቢ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ እሳቸውም የኅብረተሰቡን ጤና የሚያውከውን ይህንን አዲስ ፈተና ለመጋፈጥ በሚል የምርምርና ጥናት ትኩረታቸውን በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ አድርገዋል።
ኃይለኛው (ዶ/ር) በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ በመሆን በወቅቱ ሥጋት እየሆነ በመጣው በሽታ ላይ በርካታ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል። በጊዜው እርሳቸው ከሚያስታውሱት ዋና ሥራ መካከል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር አዲስ ታስክ ፎርስ (ግብረ ኃይል) ሲመሠረት በዚያ አባል በመሆን አገልግለዋል። ተከታታይ የጥናትና ምርምር
ሥራዎችን መፍትሔ ጠቋሚ መርምሮችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በሚካሄዱ ኮንፍረንሶች ላይ በማቅረብ የበኩላቸውን መወጣታቸውን ቀጥለዋል። በተለይ የጤና ባለሙያዎች ማህበር በየዓመቱ በሚያደርጋቸው ኮንፍረንሶች ላይ የእርሳቸው የምርምርና ጥናት ውጤቶች ግብዓት ነበሩ።
ኃይለኛው (ዶ/ር) ሙያና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ሀገራቸውን ማገልገል የጀመሩት ከትምህርት ገበታቸው በተመረቁ ማግሥት ነበር። ይህ ጥረታቸው ቀጥሎ የወቅቱ ሥጋት የነበረው ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ላይ ሙያዊ እውቀታቸውን አጋርተዋል። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳንፍራንሲስኮ (ስድስተኛው የኤች አይቪ ኮንፍረንስ) እንዲሁም በሰባተኛው ጉባኤ ደግሞ በጣሊያን ፍሎሬንስ በተጨማሪ በስምንተኛው ጉባኤ በአምስተርዳም በመገኘት ከባልደረቦቻቸው ጋር የሠሩትን የጥናት ውጤት በማቅረብ እየተስፋፋ ለነበረው የወቅቱ አስጊ በሽታ መፍትሔ ለማመላከትና የሰው ልጆችን ከጉዳት ለመጠበቅ መታገላቸውን ቀጠሉበት።
በዚህ የኤች አይ ቪ ሥርጭት ላይ ምርምር ለማድረግ ምክንያት የሆናቸው በአሜሪካን ሀገር በተጨማሪነት የተማሩት የኢፕዲሞሎጂ (የበሽታ ሥርጭትን የሚቆጣጠር አቅጣጫ ማስያዝን የተመለከተ በመሆኑ) ለሥራቸው በእጅጉ አግዟቸው ነበር። በዚህ ምክንያት በርካታ ምርምርና ጥናቶችን በማድረግ አስተዋጽኦ ለማድረግ ችለዋል።
ጥረታቸውን በዚህ ብቻ ሳያቆሙ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረቦቻቸው ጋር በመተባበር ኤችአይቪን እንግታ (ስቶፕ ኤድስ) የሚል ንቅናቄን በመፍጠር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር ሥርጭቱን ለማቆም በሚደረገው ጥረት ላይ የፊት መስመር ተሰላፊ ሆነው የድርሻቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። በተለይ በተለያዩ የበሽታ ምርምር ላይ ትኩረታቸውን በሚያደርጉ ጆርናሎች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸው ያሳትሙ ነበር።
በጥረታቸውና በሥራቸው እያሳዩ በነበረው ትጋት ምክንያት በአሜሪካን ሀገር ሳንፍራንሲስኮ የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመውሰድ እ.ኤ.አ በ1990 አቅንተዋል። በቆይታቸውም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ጋር ቅንጅት በማድረግ የጋራ ምርምሮችን ሲያደርጉና ለተጨማሪ ሥራ የሚረዳቸውን ሥልጠናዎች መውሰድ ችለዋል። ዳግም በዚሁ ሀገር በ1992 ተመልሰው ለበርካታ ወራት ተመሳሳይ ሥራዎችን መሥራታቸው እና ለአካዳሚክ ሙያቸው ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው በሀገራቸው ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ አመላካች ምርምሮችን እንዲያደርጉ በር ከፋች ነበር።
ዳግም ወደ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ብዙዎች የተሻለ የሥራና የጥቅም እድል ይገኝባቸዋል በሚባሉ ሀገራት በዚያው ይቀራሉ። ሀገራቸውን ለማገልገል እድሉን ሳያገኙ በቁጭት ይኖራሉ። ኃይለኛው (ዶ/ር) ግን ይህንን ለማድረግ አልፈቀዱም። በተደጋጋሚ ጊዜ በውጭ ሀገራት የመመላለስ እድሉን ቢያገኙም ለእርሳቸው ግን ሀገራቸውንና ወገናቸውን ከማገልገል ሊበልጥባቸው አልቻለም። በዚህ ምክንያት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የምርምር ሥራቸውን ማከናወናቸውን ተያያዙት።
እርሳቸው እንደሚሉት በወቅቱ በኢንስቲትዩቱ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎች የሚገኙበት የምርምርና መሰል ሥራዎች በስፋት የሚገኝበት እንደነበር ይገልፃሉ። በተለይ በጊዜው ወጣቶችን የሚያበረታቱና ለተሻለ የተግባር ሥራ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት በመሆኑ በርካቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ።
ወደ ሀገራቸው በተመለሱበት ወቅት ከሠራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ኢንስቲትዩቱ የተሻለ ቁመና እንዲኖረው፣ የምርምር ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረጉ የሚያግዝ የድጋፍ ስምምነት ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር በመስማማት እና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ (በኤች አይ ቪ ዙሪያ) ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ይናገራሉ። በተለይ የሕክምና ቁሳቁሶችን፣ ላብራቶሪ መሳሪያዎችን ኢንስቲትዩቱ በተሻለ መልኩ እንዲያደራጅ የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ያስታውሳሉ። ይህ ፕሮጀክት ከቁሳቁሱ፣ ከምርምር ሥራ ድጋፍ ባሻገር ለእውቀት ሽግግር ልዩ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይናገራሉ። በተለይ ዘጠኝ የፒኤች ዲ ተማሪዎች ፕሮግራም እንዲያዝ አስችሏል። እርሳቸው እና ሌሎች በሁለት ባልደረቦቻቸው ለፒኤች ዲ ትምህርት ወደ ኔዘርላንድ ተልከው ተምረዋል። ይህን ፕሮጀክት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመቅረጽ ለምርምር እና ለሕክምና መሳሪያዎች በጥራትና በውጤታማነት ኢንስቲትዩቱ የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ አስችለዋል።
መጻሕፍትን ማሳተም
ኃይለኛው (ዶ/ር) የትምህርትና የምርምር ሥራ የሕይወት መንገዳቸውና ምርጫቸው ነው። በዚህ ምክንያት የያዙትን ሙያ ከእለት ወደ እለት እያሻሻሉ፤ የእውቀት አድማሳቸውን እያሰፉ የሕይወት መንገዳቸውን ቀጥለዋል። የቀሰሙትን እውቀት ለራሳቸው ብቻ በማድረግ ግን የጋን ውስጥ መብራት አልሆኑም። ይልቁንም የደረሱበትን የምርምር ውጤት፤ ያወቁትን ክህሎት እና ያገኙትን ልምድ ሁለት መጻሕፍትን በማሳተም አጋርተዋል።
የመጀመሪያው መጽሐፍ «ውሃ ወለድ በሽታዎች እና መከላከያቸው» የሚል ነው። ይህ መጽሐፍ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር ድጋፍ አግኝቶ ታትሞ ለጤና ባለሙያዎች እንዲሠራጭ የተደረገ ነው። መጽሐፉ በውሃ ወለድ በሽታዎች ዙሪያ ባለሙያዎች በቂ እውቀት እንዲጨብጡ በእለት ተእለት ሥራቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የራሱ ድርሻና አበርክቶ ነበረው።
ሌላኛውና ሁለተኛው የእንግዳችን መጽሐፍ ‹‹ጥያቄ አለኝ›› የሚል ርእስ የታተመ ሲሆን ርእሰ ጉዳዩን በኤች አይቪ ዙሪያ ያደረገ ነበር። መጽሐፉ በተለይ ለረጅም ዓመታት በዚህ በሽታ ዙሪያ ከፍተኛ ምርምር፣ ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችና ከሳይንቲስቶች ጋር ቅንጅት በማድረግ በርካታ ጆርናሎችን እና ውጤታማ ሥራዎችን ለሠሩት እንግዳችን የጠለቀ እይታን ያጋሩበትና ምሁራዊ አበርክቷቸውን ያጠናከሩበት እንዲሆን አድርጓል።
ወደ ግል ሥራ
ሀገራዊና ሙያዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ከቆዩበት የመጀመሪያ መሥሪያ ቤታቸው ከ16 ዓመታት በኋላ ነበር የወጡት። ምክንያታቸው ደግሞ በእውቀታቸውና በሥራ ልምዳቸው ምክንያት የግል የማማከር ሥራዎችን ለመሥራት አዳዲስ እይታዎችን ለማምጣት ነበር። በዚህ ተግባራቸውም ለእርሳቸውም ሆነ ለወገኖቻቸው የሚጠቅሙ ተግባራትን አከናውነዋል ኃይለኛው (ዶ/ር)።
በዚህም ከዓለም የጤና ድርጅት፣ ከዩኤንዲፒ፣ ከዩኤን ኤድስ እና ከመሳሰሉት ዓለም አቀፍ በርካታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲሠሩ ቆይተዋል። ከእነዚህ ተግባራት ባሻገር በልዩ ልዩ ቦታዎች የሥራ ኃላፊነቶችን ወስደው የአመራርነት አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በጤና አጠባበቅ ማህበር
እንግዳችን በልዩ ልዩ መስኮች ላይ ስኬታማ የሆነ የሙያ ጊዜን አሳልፈዋል። ከእዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው ከማማከር አገልግሎቱ ባሻገር ልዩ አበረከቶ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ውስጥ ከ2010 እስከ 2015 ድረስ የማህበሩ ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉበት ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር የተመሠረተው እኤአ በ1989 ነው። ስለ ማህበሩ ምስረታ የሚናገሩት እንግዳችን ምስረታው እውን የሆነው ለሙያው ቆራጥ የሆነ አመለካከት እና ጥረት ባደረጉ ሰዎች አማካኝነት መሆኑን ይናገራሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከልም እርሳቸው ይገኙበታል። ማህበሩ ቢሮና መሰብሰቢያ ቦታ ሳይኖረው በተለያዩ አካላት ድጋፍ እየጠየቀ ሥራውን መጀመሩን ይናገራሉ። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎችና የጤና ባለሙያዎች እገዛ እንዳልተለየውም ይናገራሉ።
እንግዳችን ማህበሩን ባገለገሉበት አምስት ዓመታት ውስጥ ከሠሯቸው ሥራዎች የመጀመሪያው አራት ወለል ወዳለው የተሻለ ጽሕፈት ቤት (ወደ መስቀል ፍላወር) እንዲዛወር ማድረግ አንዱ ነው። ይህ መሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ማህበሩን ከሚደግፉ ርዳታ ሰጪ ድርጅቶች (ሲዲሲን ከመሳሰሉት) እንዲገኙ የሚያስችል መዋቅራዊ ማሻሻያ አድርገዋል።
13ተኛው ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ማህበር (የዓለም ፌዴሬሽን ፐብሊክ ሄልዝ አሶሲዬሽን) በየሶስት ዓመቱ የሚያደርገውን ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ በመወዳደር እንድትመረጥ ምክንያት ሆነዋል። ሌላው በርሳቸው የአመራር ዘመን ከሥራ ባልደረቦቻቸው እና ከቦርድ አባላት ጋር በመሆን ማህበሩ የሊዝ ቦታ እንዲያገኝ እና አሁን በቀበና አካባቢ የሚገኘው ህንፃ እንዲሠራ መሠረት መጣል አንዱ ነበር። ይህም ማህበሩ ከነበረበት የኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንዲድን ምክንያት ሆኗል።
ወደ ሌላ ኃላፊነት
ኃይለኛው (ዶ/ር) በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ውጤት የሚያመጣ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከአይ ካፕ (የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ) ጋር የሠሩት ሥራ ነው። ለሁለት ዓመት በቆየው በዚህ ሥራቸው በኤች አይ ቪ ሥርጭት ዙሪያ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ አጥንቶና ተንትኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላሉ ፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን መረጃ መስጠት ነበር። በዚህ ተግባራቸው ቀደም ሲል የነበራቸው የዳበረ ልምድን በመጠቀም ጥናቱን በማቀነባበር እና በመከታተል የተሻለ ውጤት እንዲገኝ ምክንያት ሆነዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ላይ 14 የሚደርሱ ባለሙያዎችን በሥራቸው በማስተባበር፣ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የመስክ ሥራዎችን በማድረግ፣ የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭት ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ሳይንሳዊ የጥናት መለኪያዎችን የተመለከተ ጥናት ሠርተዋል።
ይህንን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥናት በመምራት በሙያ ዘመናቸው ሀገራቸውን የማገልገል ውጥናቸውን አሳክተዋል።
ቆይታ በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር
ባለፉት በርካታ ዓመታት ኃይለኛው (ዶ/ር) በሙያ ጉዟቸው እጅግ በርካታ ስኬቶችን እውን አድርገዋል። በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ምርምር ካገኙት ውጤት ባሻገር ሀገራቸውን በጤናው ዘርፍ ለውጥ እንድታመጣ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። የጤና ሙያ ማህበሩ በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምስረታ ጀምሮ የአመራርነት ዐሻራቸውን አኑረዋል።
አሁን ደግሞ ከተመሠረተ ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ነቅሶ በሴሪያል ድራማና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ያቀርባል። ዜጎችም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በሥነ ተዋልዶና ጤና ዙሪያ እውቀት እንዲኖራቸው ግንዛቤ ይፈጥራል፣ የፆታ ትንኮሳ ላይ፣ በሥነ ሕዝብና እድገት ዙሪያ ሥራዎችን ይሠራል። በተለይ የተለያዩ ድራማዎችን ያቀርባል። ይህንን ድርጅት በአሁኑ ጊዜ እየመሩ ይገኛሉ።
እንግዳችን አሁን እየመሩት በሚገኙት የፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ውስጥ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ድጋፍ እንዲያገኙ በማመቻቸት፣ ፕሮግራሞቹ በመንግሥትም ይሁን በተራድኦ ድርጅቶች ተቀባይነት እንዲያገኙ ጉትጎታ በማድረግ ማህበረሰቡ ከላይ በተነሱት ጉዳዮች ዙሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን በቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የአመራር ጥበብና ለዓመታት ያዳበሩትን ልምድ እየተገበሩ ይገኛሉ።
‹‹እነዚህ ድርጅት ውስጥ የሀገሪቱ ተጠሪ ሆኜ ሥሠራ ማህበረሰቤን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ነው›› በማለት የመጨረሻ ሃሳባቸውን የሰጡን ኃይለኛው (ዶ/ር) በተለይ ከስደት የሚመለሱ እህቶቻችን የተሻለ ኑሮ በሀገራቸው እንዲመሩ፣ ሴቶችና እናቶች ከጉዳትና ከጥቃት ተጠበቀው እንዲቆዩ የሚሠሩት ሥራ የኅሊና እረፍትና እርካታን እንደሚሰጣቸው ገልጸውልናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም