ትራምፕ ለመወያየት ከፈለጉ የጣሉትን ታሪፍ እንዲያነሱ ቻይና አሳሰበች

ቻይና ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት ለማስቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን ለማሳየት ወደ ሀገራቸው በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ እንዲሰርዙ ጠየቀች።የትራምፕ አስተዳደር የንግድ ውይይት እየተካሄድ መሆኑን ቢገልጽም፤ ይህ ከእውነት የራቀ መሆኑን አንድ የቻይና ባለሥልጣን ተናግረዋል።

በሁለቱ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል ያለው የንግድ ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፤ በተጣለባት ታሪፍ ምክንያት ቻይና ከአሜሪካ ያዘዘችውን ቦይንግ አውሮፕላኖች አልፈልግም በማለት መልሳለች።ትራምፕ በቻይና ላይ ያላቸውን አቋም መለዘብ የተያበት መሆኑ ሲገለጽ፤ እስካሁን በቻይና ምርቶች ላይ የጣሉት ቀረጥ “በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል” ቢሉም “ዜሮ ግን አይሆንም” ብለዋል።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት እየተፋፋመ ሲሆን፤ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ እስከ 145 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ሲጥሉ ቻይና ደግሞ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ቀረጥ ጥላለች።ቻይና በታሪፍ ጦርነቱ ዙሪያ እስካሁን ከሰጠቻቸው በጣም ጠንካራው ነው በተባለለት መግለጫ የንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ሄ ያዶንግ ችግሩን ለመፍታት በቻይና ላይ የተጣለውን ሁሉንም “የአንድ ወገን ታሪፍ” አሜሪካ ማስወገድ አለባት ብለዋል።“ታሪፉን የጣለው ሰው ይህንን መቀልበስ አለበት” ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን ደግሞ ቻይና እና አሜሪካ “ስምምነት ላይ መድረስ ይቅርና በታሪፍ ላይ ምክክርም ሆነ ድርድር አላደረጉም” ብለዋል።ከእዚህ በተቃራኒ ያሉ ዘገባዎች “ውሸት” መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ ከእዚህ ቀደም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ድርድር “እየተካሄደ” ነው ቢሉም፤ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት መንም ድርድር አልተጀመረም ሲሉ ተቃራኒ ሃሳብ አቅርበዋል።ቤሴንት አክለውም በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና የንግድ ልውውጥ ላይ “ትልቅ ስምምነት” ለመፍጠር ዕድል አለ።ከእዚህ ቀደም “ዘላቂ ያልሆነው” የንግድ ጦርነት እንደሚለዝብ ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ አሁን ያለው ሁኔታ “ቀልድ አይደለም” ብለዋል።

ትራምፕ የንግድ ስምምነቱን ለማሳካት ከቤጂንግ ጋር የሚያደርጉት ድርድር “በጣም ጥሩ” እንደሚሆን ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።ቻይና በቅርቡ የወሰደችውን ርምጃ ተከትሎ ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ቻይና በሚያምር ሁኔታ የተጠናቀቁትን አውሮፕላኖች ባለመውሰዷ ቦይንግ ሊቀጣት ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ይህ ቻይና ለዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ያደረገችው ትንሹ ማሳያ ነው” ከማለት ባለፈ ሰው ሰራሽ ኦፒዮይድ ፌንታሊን “ከቻይና በሜክሲኮ እና በካናዳ በኩል ወደ ሀገራችን መግባቱን በመቀጠሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን እየገደለ” ነው የሚለውን ውንጀላ ደግመዋል።የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ከታሪፉ ጋር በተያያዘ ቻይና በወሰደችው የበቀል ርምጃ ከአሜሪካ ያዘዘችውን አውሮፕላኖች መልሳ እንደላከች ገልጿል።

በእዚህ ሳምንት ሁለት አውሮፕላኖች መመለሳቸውን ኬሊ ኦርትበርግ ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት ተከትሎ ሌላ አውሮፕላንም ሊመለስ እንደሚችል ጠቁመዋል።ከ80 የሚበልጡ የውጭ ኩባንያዎች የአሜሪካ ታሪፍ በቻይና ኢንቨስትመንታቸው ላይ እያሳደረ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ቻይና ረቡዕ ዕለት ውይይት ማድረጓን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የንግድ ምክትል ሚኒስትሩ ሊንግ ጂ “ የውጭ ኩባንያዎች ፈተናዎችን ወደ እድሎች እንደሚቀይሩ ተስፋ ይደረጋል” ሲሉ ማመልከታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You