
56ሺ ሯጮችን ጨምሮ በርካታ ስመጥር አትሌቶች የሚካፈሉበት 45ኛው የለንደን ማራቶን ነገ ይካሄዳል። ከሰባቱ የዓለም ዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው በእዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮም ታላላቅ አትሌቶች ይሳተፋሉ። አዲስ ታሪክ ለማጻፍ የሚያደርጉት ፉክክርም ትኩረት አግኝቷል።
በውድድሩ ለውጤት ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ ሲሆኑ፤ በኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክ የሠሯቸውን ጀብዱዎች በለንደን ይደግማሉ የሚል ግምትም አግኝተዋል።
በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ በተሰጠው የለንደን ማራቶን የረጅም ርቀት ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ እና በሴቶች የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷ ሩት ቼፕጌቲችን የመሳሰሉ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ አትሌቶቹ ውድድሩ ቀናት ሲቀሩት ተሳትፏቸውን ሰርዘዋል። ይሁን እንጂ እጅግ ጠንካራ የተባሉ አትሌቶች ለበላይነት የሚያደርጉትን ፍልሚያ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በተለይም ይህ ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚካሄድበት እንደመሆኑ ሀገራቸውን ወክለው በመድረኩ ለመካፈል የለንደን ማራቶንን በመሳሰሉ ውድድሮች ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የግድ ነው። በመሆኑም በርቀቱ ዝናን ያተረፉ አትሌቶች ነገ የሚያደርጉት ፉክክር የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት የሳበ ነው።
የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ በወንዶቹ ፉክክር ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። እአአ ከ2000 በኋላ በኦሊምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው ታምራት ለለንደን ማራቶን አዲስ አይደለም። እአአ በ2023 የለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ በኦሊምፒኩ በተጠባባቂነት ወደ ፓሪስ እንዲጓዝ አድርጎታል። በቡድን አጋሩ አትሌት ሲሳይ ለማ ጉዳት ተተክቶ 2:06:26 በሆነ ሰዓት የኦሊምፒክን ክብረወሰን ማሻሻልም ችሎ ነበር። ከኦሊምፒኩ በኋላ በኒውዮርክ ማራቶን ተሳትፎም 4ኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።
የዓለም አትሌቲክስም ከስታዲየም ውጪ በተደረገ ውድድር ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አትሌት በሚል ባበረከተለት ሽልማት ዓመቱን ያጠናቀቀው ታምራት፤ በአዲሱ 2025 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ተሳትፎው ለንደን ላይ ያደርጋል። በረጅም እረፍትና ልምምድ ያሳለፈውና በታታሪነቱ የሚታወቀው የኦሊምፒክ ባለድል የቀጣዩ የቶኪዮ ዓለም ቻምፒዮና ተሳትፎውን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ሰዓት ለማስመዝገብም ነገ ለንደን ላይ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል የለንደን ማራቶን ጀግናው ኬንያዊ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ እአአ ከ2020 በኋላ በመድረኩ በድጋሚ የሚሮጥ መሆኑም ተረጋግጧል። የ4 ጊዜ የቦታው አሸናፊ አትሌት በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎው ቢጠበቅም እንደታሰበው ውድድሩን ሳይጨርስ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ከእዚያ በኋላ በሌሎች ውድድሮች ላይ ባይታይም ነገ በለንደን ጎዳናዎች ላይ በዓመቱ የመጀመሪያ የሆነ ውድድር ያደርጋል። አትሌቱ ወደቀድሞ ተፎካካሪነቱ ይመለስ ይሆን የሚለውም የስፖርት ቤተሰቡ የሚጠብቀው ነው። ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞም የመጀመሪያውን የማራቶን ተሳትፎውን ለንደን ላይ ሲያደርግ የሚያሳየው ብቃት ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር የቀድሞ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ትኩረት የተሰጣት ኢትዮጵያዊት ናት። እአአ በ2023 የበርሊን ማራቶንን 2:11:53 በሆነ ሰዓት በመሮጥ የዓለም ክብረወሰንን በእጇ ማስገባት የቻለችው ትዕግስት፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ በርቀቱ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። ትዕግስት አምና በለንደን ማራቶን ተሳትፎዋ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በመድረኩ በድጋሚ ስኬታማ ለመሆን ተዘጋጅታለች።
ሀገሯን በፓሪሱ ኦሊምፒክ የወከለችው ጠንካራዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ከባድ የአሸናፊነት ተጋድሎ ብታደርግም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሜትሮች በሲፈን ሀሰን በመቀደሟ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ከወርቅ ሜዳሊያ ግስጋሴዋ የገታቻት ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት ሲፈን ሃሰንም በነገው የለንደን ማራቶን ዳግም ልትፈትናት ተዘጋጅታለች። የአትሌቲክስ አፍቃሪዎችም የሁለቱን አትሌቶች ፉክክር በጉጉት የሚጠብቅ ሲሆን፤ የሲፈን ድል ይደገም ይሆን ወይስ ትዕግስት ቁጭቷን ትወጣለች የሚለው አጓጊ ነው። ቪቪያን ቺሪዮትን የመሳሰሉ ጠንካራ ኬንያውያን አትሌቶችም ፉክክሩን ብርቱ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።
በለንደን ማራቶን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች 41ሺ ፓውንድ የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ በወንዶች ከ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃ በታች ለሚገባ ወንድ እንዲሁም በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በታች ለምትገባ ሴት አትሌት ደግሞ 112ሺህ ፓውንድ ጉርሻ በተጨማሪነት እንደሚያገኙም የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም