ክልሎች ለመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እየተዘጋጁ ነው

ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ በቅርቡ እንደሚጀመር የውድድሩ ባለቤት የሆነው ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መጠቆሙ ይታወቃል። የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ምናልባትም በዚህ ወር በጅማ ከተማ አስተናጋጅነት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። የተለያዩ ክልሎችም ለመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ቅድመ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ጨዋታዎቻቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል ቀደም ብሎ ውድድሩን የጀመረ ሲሆን በአምቦ ከተማ አዘጋጅነት የመላ ኦሮሚያ ጨዋታዎቹን አከናውኗል። አማራ ክልል ደግሞ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ 9ኛው የመላ አማራ ጨዋታዎች ውድድርን “ስፖርት ለሰላም፣ ሰላም ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል በደሴ ከተማ ሆጤ ስታዲየም እያካሄደ ይገኛል።

የባህልና ስፖርት ሚንስትር ሸዊት ሻንካ በውድድሩ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት “ስፖርታዊ ጨዋታዎች ከውድድር ባሻገር የሕዝቦችን አንድነት በማጠናከር ሰላምን ፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ አብሮነትን የሚያስተምሩ ናቸው ። ከዚያም በላይ በዓለማችን ስፖርት የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ለማከናወን ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። ስፖርታዊ ውድድሮች የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት ያነቃቃሉ። መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት በመላ ሀገራችን ከዚህ በፊት ተቋርጠው የነበሩ ስፖርታዊ ውድድሮች በስፋት እየተካሄዱ ይገኛል” ብለዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም ከዘጠኝ ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታን ለማስቀጠል  ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በማቀድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል። ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ተሳትፎ የራሳቸውን ውድድር እያካሄዱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስፖርት በሰላማዊ አውድ ውስጥ የሚካሄድ አብሮነትን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ገልፀዋል። “የመላ አማራ ጨዋታ ሰውና ሰውነት በሚገለጥበት አካባቢ ደሴ የሚካሄድ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ስፖርት ወጣቶችን በአካል የዳበሩ በኢኮኖሚ የጠነከሩ ከሱስ የጸዱ ስለሚያደርጋቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። አክለውም፣ ስፖርት የጋራ ገዥ ትርክትን እንደሀገር ለመገንባት እና ብሔራዊነትን ለማስረጽ አጋዥ በመሆኑ እንደመንግሥት በትኩረት ይሠራበታል ብለዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ፣ የመላ አማራ ውድድር ዓላማ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር የክልሉን ሰላም ማጽናት መሆኑን ገልፀው፣ በጅማ ከተማ ለሚካሄደው መላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ክልሉን የሚወክሉ ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት ውድድሩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ 6ኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እየተካሄዱ ነው። የመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ፣ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፖርት እድገት ላይ የገጠመውን ስብራት በመጠገን ስፖርት ሕብረ-ብሔራዊነትን በሚያጠናክር መንገድ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ስፖርት ለሀገረ መንግሥት ገፅታ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠው የቆዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን እንዲጀመሩ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ሚንስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል። አክለውም፣ የዚህ ስፖርታዊ ውድድር መጀመር የመላውን የሀገራችን ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ስፖርተኞችን በአንድ ቦታ በማሰባሰብ ተሰጥኦ ያላቸውን ምርጥ ስፖርተኞችን በመመልመል ለኦሊምፒክና ለመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለማዘጋጀት ዓላማ ያደረገ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በባንባሲ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው 6ኛው መላ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስፖርታዊ ውድድር በ17 ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር መካከል በ11 የስፖርት አይነቶች እስከ ግንቦት 14/2017ዓ.ም ይቆያል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You