
የዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪያን ሁሌም ሊመለከቱ የሚሹት የረጅም ርቀት ንጉሱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የማራቶን ጉዞ ዳግም ተደናቅፏል:: ጀግናው አትሌት ድንቅ የአትሌቲክስ ብቃቱን ባሳየባቸው የለንደን ጎዳናዎች ዘንድሮ አንድ አዲስ ነገር ያሳያል ብለው በርካቶች ጓግተው ቀናትን ሲቆጥሩ ቆይተዋል:: ይሁን እንጂ የለንደን ማራቶን ጥቂት ቀናት በቀሩት በእዚህ ወቅት ቀነኒሳ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ተሳትፎውን መሰረዙን ከትናንት በስቲያ አሳውቋል:: የቀነኒሳ ከውድድሩ ውጪ መሆን ብዙዎች አስቀድመው የጠበቁትና ከምንጊዜም ተፎካካሪው ኬንያዊ የማራቶን ኮከብ ኢሉድ ኪፕቾጌ ጋር ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ይገናኙበታል በሚል ተስፋ ለተጣለበት መድረክ መርዶ ሆኗል::
በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀት በታሪክ ከታዩ አትሌቶች አቻ ያልተገኘለት ቀነኒሳ፤ በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ጉዳት ጋር ተያይዞ ከዓመታት ወዲህ ያለው ተሳትፎ ውስን መሆኑ ይታወቃል:: እንደ ለንደን ማራቶን ከታላላቆቹ ማራቶኖች መካከል አንዱ በሆኑ ሩጫዎች መሳተፉ ሲረጋገጥም የስፖርት ቤተሰቡን ስሜት በእጅጉ የመያዝ አቅም አለው:: በእርግጥም ከቀናት በኋላ 56ሺ ሰዎችን በማሳተፍ የሚካሄደውን የለንደን ማራቶን የሚያደምቀው የሯጮች ቁጥር ሳይሆን እንደ ቀነኒሳ ያሉ በስፖርቱ የከበሩና የገነኑ ስሞች ናቸው:: ብቃቱን የማይጠራጠሩ የስፖርቱ ቤተሰቦች በ41 ዓመቱም ቀነኒሳ ስለሚሠራው ጀብድ እያሰቡ በማራቶን የሚሠራውን ታሪክ ከመናፈቅ ወደኋላ አላሉም::
በሁለት ኦሊምፒኮች የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች 3 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው ጀግናው አትሌት፤ በአራት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረኮች ደግሞ 5 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል:: በመም የረጅም ርቀት ውድድሮች ለዓመታት ተፎካካሪ ሳይገኝለት የበላይነቱን ጠቅልሎ ከመያዙም ባለፈ በሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና 11 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ማስገኘት ችሏል:: በእዚህም በሀገር አቋራጭ ውድድር ታሪክ በዓለም የእሱን ያህል በድል የተንቆጠቆጠ አትሌት አልታየም:: ቀነኒሳ ወደ ማራቶን ከተሸጋገረም በኋላ በለንደን እና በርሊን ማራቶኖች ተደጋጋሚ ፉክክር በማድረግ በርቀቱ ክብረወሰኑን ለማሻሻል ከጫፍ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም:: እአአ በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ ያስመዘገበው 2:01:41 የሆነ ሰዓት በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ከነበረው ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነበር::
እአአ በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር አራተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ በተካሄዱ ኦሊምፒኮች ሳይታይ የቆየው ጀግናው አትሌት፤ አምና በፓሪስ ኦሊምፒክ በማራቶን ዳግም ኢትዮጵያን መወከል ችሎ ነበር:: በወቅቱ የቀነኒሳ ወደ መድረኩ መመለስ ጎን ለጎን ከኬንያዊው ድንቅ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በአንድ ውድድር መገናኘት በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪካዊ ሁነት ተብሎ ነበር:: ይሁንና ኪፕቾጌ ውድድሩን አቋርጦ በመውጣቱ በሁለቱ አትሌቶች መካከል ይኖራል በሚል የተጠበቀው ፉክክር ሳይታይ ቀርቷል:: የዘንድሮው ለንደን ማራቶን ደግሞ በድጋሚ አንጋፋዎቹን አትሌቶች ለአሸናፊነት ያፋጥጥ ይሆን የሚለው የበርካቶች ጉጉት ነበር::
ከለንደን ማራቶን ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው ቀነኒሳ በተደጋጋሚ ከተካፈለባቸው ሩጫዎች ውስጥ ይጠቀሳል:: እአአ በ2016 እና 2017 የለንደን ማራቶን ተሳትፎው የነሐስና የብር ሜዳሊያዎችን ቢያጠልቅም በተከታዩ ዓመት 6ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው:: በ2020 በለንደን ግማሽ ማራቶን የቦታውን ክብረወሰን ሲያሻሽል፤ በ2022 በማራቶን ተሳትፎ 56ኛ ደረጃን ቢይዝም በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ መቀጠል ሳይችል ቀረ:: በ2024 ደግሞ የግሉን የቦታውን ሰዓት በማሻሻል ጭምር ድንቅ ፉክክር በማድረግ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በማጠናቀቁ ዳግሞ ወደ ኦሊምፒክ መመለሱ የሚታወስ ነው::
የዘንድሮው የለንደን ማራቶን ደግሞ አንጋፋዎቹን አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ኢሉድ ኪፕቾጌን የሚያገናኝ ይሆን ይሆናል በሚል ቢጠበቅም እንደታሰበው አልሆነም:: ይልቁኑ በማህበራዊ ድረ-ገጹ “በለንደን ማራቶን ያለፈው ዓመት ውጤታማነቱን ለመድገም ብጓጓም በልምምድ ወቅት በደረሰብኝ መጠነኛ ጉዳት መሳተፍ አልችልም፤ በእዚህም እጅግ አዝኛለሁ” ሲል አስታውቋል:: ይህንንም ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን የስፖርት ቤተሰቡ በዜናው የተሰማውን ስሜት በስፋት አንጸባርቋል:: ቀነኒሳ በመጪው እሁድ በሚካሄደው የለንደን ማራቶን ለሚሳተፉ ሌሎች አትሌቶችም መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም