ኢትዮጵያ እና የዓሣ ሀብቷ

የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ሲመገባቸው ከነበሩ ምግቦች ውስጥ ዓሣ ተጠቃሽ ነው:: በተለይ ወንዝ፣ ሐይቅ ባላቸው፤ በባሕርና በውቅያኖስ በሚዋሰኑና በተከበቡ ሀገሮች ዓሣን እንደ መደበኛ ምግብ የመጠቀም ባሕል ሰፊ ነው:: በኢትዮጵያ ግን ያለው የአመጋገብ ባሕል ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው:: ዓሣ የአዘቦት ምግብ ከመሆን ይልቅ በጾም ወቅት እና በአንዳንድ ሆቴሎች ብቻ የሚዘወተር የምግብ ዓይነት ነው::

በባሕላችን የማኅበር ድግስ፣ ጽዋ ማውጣት፣ ድሆችን ደግሶ የማብላት፣ ሠርግ፣ የተማሪዎች ምርቃት፣ የዕድር ምርቃት፣ የቤት ምርቃት፣ የሆቴል ቤት ምርቃት፣ ሲኖር ምግብ ይዘጋጃል:: ከላይ በጠቅስኳቸው የግብዣ ቦታዎች ግብዣው ቡፌ ቢሆንና በመኖሪያ ቤት ውስጥ ቢዘጋጅ የዓሣ የምግብ ዓይነት ለማግኘት መሞከር ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ይሆናል:: ዓሣ ለሌማታችን ባዳ፤ ለማዕዳችን እንግዳ በመሆን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የቅርብ ሩቅ ሆኗል::

ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ሕይወታቸው ላይ ጠንካሮች ናቸው:: በእነዚህ ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ በርካቶች የሚታደሙባቸው ግብዣዎች እና የምግብ መስተንግዶዎች ይዘጋጃሉ:: በአንዳቸውም ላይ ግን ዓሣን ማግኘት ዘበት ነው:: ለሠርግም ሆነ ለለቅሶ ወይም ለእዝን፤ ለልዩ ልዩ በዓላት ሥጋን እንጂ ዓሣን የሚያስታውሰው የለም:: ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲሄዱ፤ ሠራተኞች ሥራ ቦታ ሲሄዱ ዓሣ እንደ ምግብ ይዘው ሲሄዱ አይታይም ሳይሆን አይታሰብም ማለት ይሻለናል:: በአጠቃላይ ባሕላችን ዓሣን እንደ መደበኛ ምግብ አይመለከተውም::

ዓሣ የመብላት ባሕላችን ከአዲስ አበባ ይልቅ ሐይቆች በሚበዙባቸው አካባቢዎች የተሻለ ይመስለኛል:: ሀዋሳ፤ ባህር ዳር፤ ዝዋይ፤ አርባ ምንጭ የመሳሰሉ ከተሞች ባላቸው የውሃ ጸጋ አማካኝነት ዓሣን የመብላት ባሕላቸው የተሻለ ሆኖ ይገኛል:: በውስጧ ከሚያልፉ ወንዞቿ ባሻገር የአቃቂው አባ ሳሙኤልና የቢሾፍቱ ሐይቆች አፍንጫዋ ላይ ያለችው አዲስ አበባ ዓሣ የመብላት ባህል ግን በደካማነት የሚያስፈርጃት ነው::

በርግጥ አዲስ አበባ በርካታ ወንዞች ያሏት ቢሆኑም ሁሉም በሚባል ደረጃ የተበከሉ እና ሕይወት የሌላቸው ስለሆኑ የዓሣ ምርት የሚሰጡ አይደሉም:: ሆኖም እነዚህ የተበከሉ ወንዞች በአግባቡ ተይዘው ቢሆኑ ኖሮ ከከተማዋ አልፎ ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎችም የዓሣ ምርት የማቅረብ አቅም ይፈጥሩ ነበር:: የበርካታ ዓለም ከተሞች ተሞክሮ እንደሚያሳየውም ዓሣን የመሳሰሉ የከተማ ግብርና ምርቶች የሚገኙት ከአካባቢ ባሉ ወንዞች ነው::

በርግጥ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የወንዝ ልማት በሰፊው እያከናወነች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወንዞቻችን እንደገና ሕይወት ዘርተው ዓሣ ይመግቡን ይሆናል:: በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለውን ወንዞች ልማት ተዘዋውሮ ለተመለከተ ሰው ይህንን ቢመኝ የሚያስፈርድበት አይደለም:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ ዓሣ ነው:: ስለዚህም በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንዞች ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በዓሣ ምርት እንደሚጥለቀለቁ ይሰማኛል::

ሆኖም እዚህ ላይ ትኩረት መደረግ ያለበት ዓሣ የመመገብ ባሕላችን ነው:: አልተጠቀምንበትም እንጂ ኢትዮጵያ በዓሣ ምርት የታደለች ሀገር ነች:: የበርካታ ወንዞች እና ሐይቆች ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ዓሣ በሰፊው ይመረትባታል:: ሆኖም የአመጋገብ ባሕላችን ኋላቀር በመሆኑ የተመረተውንም ምርት በአግባቡ ስንመገብ አንታይም፤ ተጨማሪ ምርትም ለማምረት አንነሳሳም:: ይህ የአመጋገብ ባሕላችን የፈጠረው ክፍተት ነው::

በየቤታችን ሄደን ዓሣ እንኳን ቢገኝ እንዴት መሥራት እና መብላት እንዳለብን ቢፈተሽ ለምግብነት በቅጡ የማዘጋጀት ክፍተት እንደሚኖርብን እሙን ነው:: ዓሣን ብዙም ስለማንጠቀመው የአሠራር ጥበቡንም በዛው ልክ ልናውቀው አንችልም:: ሆኖም ልክ ኢትዮጵያውያን ለእንጀራ እና ለሽሮ ስሱ ልብ እንዳላቸው ሁሉ ዓሣን ከማዕዳቸው የማያጡ በርካታ ሀገራት አሉ::

በዓለም ላይ የዓሣ ሀብት ልማትና መብላትን በቅደም ተከተል ካየን ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቬትናም እና ፔሩ ተጠቃሽ ናቸው:: ዩናትድ ስቴትስ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ደቡብ ኮሪያና ሚያንማር ይከተላሉ:: በፈረንጆቹ በ2022 ቻይና ከዓለም 36 በመቶውን ዓሣ አልምታለች:: ህንድ 6 በመቶ፣ ኢንዶኔዥያ 7 በመቶ፣ ቬየትናም 5 በመቶ፣ ፔሩ 3 በመቶውን ከዓለም ዓሣ ሀብት አልምተው ነበር::

ቻይና በ2022 የዓለም እርሻ ድርጅት ፋኦ ባወጣው መረጃ 88 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዓሣ ሀብት አልምታለች:: ኢንዶኔዥያ 22 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን፣ ህንድ 15 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን፣ ቬትናም 8ነጥብ8፣ ሩሲያ 5 ነጥብ 3፣ ባንግላዴሽ 4ነጥብ 8፣ ዩናትድ ስቴትስ 4ነጥብ 7 ሜትሪክ ቶን ዓሣ ሀብት አልምተው ነበር::

ከአፍሪካ ዓሣ ሀብት በማልማት ግብጽ ቀዳሚ ናት:: በ2022 ግብጽ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዓሣ፣ ናይጄሪያ 260 ሺህ ሜትሪክ ቶን ዓሣ ሀብት በማልማት ትከተላታለች:: ይህን መረጃ ያወጣ www.researchgate.net ድረ ገጽ ኢትዮጵያን ዓሣ ሀብት በማልማት የአፍሪካ ጭራ ግብጽ ደግሞ የአፍሪካ አውራ አድርጎ አስቀምጧታል::

ጎበዝ አያስቆጭም እውነትም ‹‹የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› ያስብላል:: ስለዚህ ግብርና ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሚዲያ ተቋማት በደካማው ዓሣ ሀብት ልማት እና የመብላት ባሕላችን ላይ የማነቃቂያ ዘመቻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::

የዓለም ምግብ ድርጅት ፋኦ ከአፍሪካ ዓሣ ሀብት ልማት በጥሬው እና ዓሣ በምግብነት ኤክስፖርት ከሚያደርጉ አስር ሀገራት 89 በመቶ የአህጉሩን ዓሣ ምርቶች ወደ ውጭ ይልካሉ:: ከነዚህም መካከል ሞሮኮ 28 በመቶ፣ ናሚቢያ 15 ነጥብ 8፣ ደቡብ አፍሪካ 12 ነጥብ3 በመቶ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ እንደያዙ መረጃው ያሳያል::

ኢትዮጵያ ዓሣ በመጠቀም ደረጃ ስሟ አይነሳም:: የለችም፤ በዓለም ዓሣ ባለመጠቀም ኢትዮጵያ፣ ታጃኪስታንና ሞንጎልያ ቀዳሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ:: በሀገራቱ በነፍስ ወከፍ በዓመት አንድ ኪሎ ግራም ዓሣ ለምግብነት እንደማይውል እነዚሁ መረጃዎች ያስረዳሉ:: ይህ እንግዲህ ሁሉ በእጇ ሁሉ በደጇ የሆነላት ሀገር ከፍተኛ የምግብ ንጥረ ነገር ያለውን ምግብ ለምን ችላ እንዳለችው አጠያያቂ ነው::

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተጠቀሱት ሀገራት ዓሣ የመብላት ባሕላቸው አናሳ የሆነበት ምክንያት ሲጠቀስ የተመጣጠነ ምግብ መሆኑን እንደ ባሕል አለመወሰዱ፤ መልክዓ ምድር አቀማመጣቸውና ከባሕር ጠረፍ ራቅ ያሉ በመሆናቸው ነው ሲል ያስረዳል:: ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው ደግሞ በድህረ ገጹ (worldpopulationreview.com ) ባወጣው አንድ መረጃም በፈረንጆቹ በ2022 ኢትዮጵያ 102 ነጥብ 5 ኪሎ ቶን ዓሣ ሀብት በማልማት ከዓለም 85 ደረጃ እንደነበረች ያሳያል::

ከላይ እንደገለጽነው ዓሣ ሀብት ልማትና የመመገብ ባሕላችን ደካማ ቢሆንም እንደ አርባ ምንጭ፣ እንደ ሀዋሳ በመሳሰሉ ከተሞች ወጣቶች ዓሣ እያጠመዱ እና በምግብ እያዘጋጁ ለተመጋቢዎች በስፋት ሲቀርብ ይታያል:: ከዚህም አልፎ ጥሬ ዓሣ ለምግብነትም እስከ ማዋል የደረሰ ባሕል ተገንብቷል:: ልክ በሌላው አካባቢ ጥሬ ሥጋ እንደሚበላው ማለት ነው::

ሰሞኑን የጋዜጠኞች ቡድን በሐረሪ ክልልና በሐረርጌ ዞን በነበረው የመስክ ምልክታ ዓሣን እንደ ዶሮ በጓሯቸው እያረቡ ለምግብነት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ስለመፈጠራቸው በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንብቤ ነበር:: ግቢያቸው ውስጥ ውሃ ቆፍረው በማውጣትና በገንዳ ውስጥ በማቆር በሌማት ትሩፋት ዓሣን ማርባታቸው አስደሳች ከሆኑ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ነበር:: ከዚህ ቀደም በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች ዓሣ የማልማት ልምድ አልነበረም:: ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ለአትክልትና ፍራፍሬ በሚያቁሯቸው የውሃ ጉድጓዶች ምቹ የሆኑ ዓሳ ዝርያዎችን ማርባት ተችሏል::

ሐረር ከተማ አነስተኛ ከተማ ነች:: ደግሞ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት የመጠጥ ውሃ ችግር የነበረባት ከተማ ነበረች:: ዛሬ ላይ የመጠጥ ውሃ ችግሩ ተፈትቶ በዓሣ ሀብት ልማት ወደፊት እየገሰገሰች ነው:: ይህ ሲሆን ግን ዓሣ ሀብት ለማልማት ወንዝ ከሌለኝ አይቻልም አላለችም:: ሌሎች ከተሞች በዓሣ ሀብት ልማት የሐረር ከተማንና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ ቢያዩ ይመረጣል:: ወንዝ ባይኖርም ዓሣን ማርባት ይቻላል:: በአነስተኛ ጉድጓዶች፤ ኩሬዎች እና ገንዳዎች ዓሣን አምርቶ መብላት፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ይቻላል:: አለፍ ሲልም ለገበያ አቅርቦ ገቢ ማግኘት ይቻላል::

ሀሮማያ ሐይቅ ራሱ በአንድ ወቅት ሐይቁ ደርቆ ሜዳ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል:: በወቅቱ በአካል ሄጄ አይቼዋለሁ:: ሐይቁ በነበረበት ወቅት ስለማውቀው አዝኜም ነበር:: በኋላ ግን ዛፎች በመተከላቸውና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በመሠራታቸው ሐይቁ እንደገና ሊወለድ ችሏል:: ይህም የሆነው ‹‹ውሃውም እንዳይደርቅ ዓሣውም እንዳያልቅ›› በመደረጉ ነው:: የዚህ ጽሑፍ መነሻውም የሐረር አስተዳደርና የሀሮ ማያ ዩኒቨርሲቲ ዓሣ ለማልማት የሠሩት አመርቂ ሥራ ነው:: ለጭሮ ከተማም ዓሣ ሀብት ልማት በማሳየት እና ከሀሮማያ ሐይቅ እንዲመገቡና እንዲሸጡ የማድረግ ባሕል መበረታታት አለበት::

ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን እንድትችል ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ይታወቃል:: ዝናብ ከመጠበቅ ተላቃ ስንዴ ማምረት ጀምራለች:: ይህም መንግሥት ከሠራቸው ሥራዎች ከፍተኛ ምስጋና የሚቸረው እና ሀገሪቱንም ከስንዴ ተመጽዋችነት ያላቀቀ ነው:: ልክ እንደዚሁ ሁሉ ዓሣ ሀብት የማልማትና የመጠቀም እንዲሁም ኤክስፖርት የማድረግ የቤት ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል:: በመስከረም ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሕዳሴ ግድብ የዓሣ ሀብት ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል:: ከኃይል ማመንጨቱ ቀጥሎ የዓሣ ልማቱ ቀዳሚው ፕሮጀክት እንደሚሆን መረጃዎች ያሳያሉ::

ግድቡ ሲጠናቀቅ 246 ኪሎ ሜትር ወደኋላ በመዘርጋት በ1ሺህ 680 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ 44 ሜትር ጥልቀትና 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወይንም የጣና ሐይቅን ሦስት እጥፍ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይፈጠራል::

ይህ ሰው ሠራሽ ሀይቅ የጀልባ ትራንስፖርት እና መዝናኛ አገልግሎትን ከመስጠቱም ባሻገር ሰፊ የሆነ የዓሣ ሀብት የሚገኝበትን እድል የሚፈጥር ነው:: በዓባይ ወንዝ ላይ ናይል ፐርች፣ታይገር ፊሽና፣ ካት ፊሽ የተባሉ የዓሣ ዝርያዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ ::

እንደ ባለሙያዎች ግምት በተፈጥሯዊ መንገድ ብቻ በዓመት ከ5ሺህ እስከ 10 ሺህ ቶን ዓሣ ማምረት ይቻላል:: በመሆኑም በህዳሴ ግድብ በሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ብቻ ኢትዮጵያ በዓሣ ሀብት ልምት የአህጉራችን ቀዳሚ ሀገር እንደምትሆን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት የተገኘ መረጃ ያስረዳል:: ይህም ከላይ እንደገለጽነው በዓሣ ሀብት ልማት የአፍሪካ ጭራ የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ አውራ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አመላካች ነው::

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You