ቻይና ሀገራት በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ዙሪያ እንዲጠነቀቁ አስገነዘበች

ቻይና ዶናልድ ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ወቅት አሜሪካን የምትፈልገውን በማድረግ ለማስደሰት እንዳይሞክሩ አስጠነቀቀች።የቻይና ንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የዋሺንግተን መንግሥታት ወደ አሜሪካ የሚልኳቸው ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑላቸው ከቤይጂንግ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ላይ ጫና ለመፍጠር ማቀዷ ከተሰማ በኋላ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር ከንግድ አጋሮች ጋር ታሪፍን በተመለከት ንግግር መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የጃፓን ልዑካን ቡድን ዋሺንግተንን የጎበኙ ሲሆን፤ በእዚህ ሳምንት ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ለመወያየት ቀጠሮ ይዛለች።ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን፤ ሌሎች በርካታ የዓለም ሀገራትም ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።የቻይና የንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ “ለማስደሰት የሚደረግ ጥረት ሰላምን አያመጣም፤ እንዲሁም ጥቅምን አሳልፎ መስጠት ክብርን አያቀዳጅም” ብለዋል።

“ቻይና ሁሉም አካላት ከፍትሐዊነት ጎን መቆም እንዳለባቸው ታምናለች. . . እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት እና የንግድ ሕጎች እንዲሁም ሀገራት የንግድ ሥርዓትን መከላከል አለባቸው።”ባለፈው ሳምንት ዎል ስትሪት ጆርናል አሜሪካ ታሪፍን በተመለከተ ከሀገራት ጋር በምታደርገው ድርድር ከቻይና ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ አዲስ ገደብ በመጣል ጫና ለማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቦ ነበር።

በንግድ ጉዳዮች ላይ የሚሠራው ሞኔክስ ግሩፕ ባልደረባ የሆኑት ጄስፐር ኮል “ቁጥሮችን የምንመለከት ከሆነ የጃፓን 20 በመቶ ትርፋማነት የሚመጣው ከአሜሪካ ነው፤ 15 በመቶው ደግሞ ከቻይና ነው” ብለዋል።ስለዚህም “ጃፓን በእርግጠኝነት ከአሜሪካ እና ከቻይና ልትመርጥ አትችልም።”ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ታሪፍን በተመለከተ የተለያዩ ውዝግቦች ተቀስቅሰዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በገቢ ምርቶች ላይ የሚጣል ግብር ሸማቾች በአሜሪካ የተመረቱ ምርቶችን እንዲገዙ ያበረታታል፤ የሚሰበሰበው ታክስ ይጨምራል እንዲሁም ወደ አሜሪካ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ይስባል ሲሉ ይከራከራሉ።ተቺዎች ግን ግዙፍ አምራቾችን ወደ አሜሪካ ለመሳብ እንዲህ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም ይላሉ።

ምናልባት አስርት ዓመታትን ሊወስድ ስለሚችል በመካከል የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ ይገባል ሲሉ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን እንዲያጤን ምክራቸውን ይለግሳሉ።ትራምፕ በሀገራት ላይ ታሪፉን ይፋ ካደረጉ በኋላ ውሳኔያቸው ተፈጻሚ የሚሆንበትን ቀን አራዝመውታል።ትራምፕ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።ሌሎች የዓለም ሀገራትም እስከ ሐምሌ ወር ድረስ አነስተኛ ነው የተባለው 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት አዲስ የሚጣሉ ታሪፎች ሲጨመሩ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ እስከ 245 በመቶ እንደሚደርስ ተናግሯል።ዶናልድ ትራምፕ በሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን ካስታወቁ በኋላ ከ70 ሀገራት በላይ ለድርድር ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You