
ለረጅም ጊዜ በከባድ የጤና ችግር በሕክምና ላይ የቆዩት የ88 ዓመቱ አዛውንት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ፓፕ ፍራንሲስ ማረፋቸውን ቫቲካን አስታወቀች። ወደ ጵጵስናው መንበር ከመምጣታቸው በፊት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በመባል ይታወቁ የነበሩት ጳጳሱ፤ ቀዳሚያቸው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2013 የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እንዲመሩ የተመረጡት።
ፖፕ ፍራንሲስ ለወራት በሕክምና ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአደባባይ ርቀው ከቆዩ በኋላ እሁድ ዕለት በተከበረው የትንሳዔ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ምዕመን በአካል ተገኝተው የትንሳዔ በዓል መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ጳጳሱ ትናንት ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በፋሲካ በዓል ማግስት ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ካዛ ሳንታ ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በ88 ዓመት ዕድሜያቸው ማረፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች።
ብጹዕነታቸው ካርዲናል ፋረል በጳጳሱ ሞት ሐዘን ውስጥ ሆነው “የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ የቅዱስ አባታችን ፍራንሲስ ሞትን በጥልቅ ኀዘን አሳውቃለሁ ሲሉ የጳጳሱን ሕልፈት ይፋ አድርገዋል። ትናንት ሰኞ ላይ ቫቲካን ውስጥ ማረፋቸውን የጠቀሱት ካርዲናል ፋረል ፍራንሲስ ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰዋል። ሕይወታቸውን ለጌታ እና ለቤተክርስቲያናቸው ሰውተው ነበር” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም