‹‹ኢትዮጵያ በችግኝ ተከላ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ አሻሻለች››
ቢቢሲ
የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ቀን ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የዓለም ሪከርድ ለመያዝ የችግኝ ተከላ አካሂዷል። በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት የደን ሀብትን ለማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ዓላማ ያደረገ ነው። ችግኝ ተከላው ሁሉም ህብረተሰብ ተሳታፊ እንዲሆን የመንግስት ተቋማት እንዲዘጉ ተደርገዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ 35 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ አራት በመቶ ማሽቆልቆሉን አመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንደተናገሩት፣ የችግኝ ተከላው በአንድ ሺ ሳይቶች ላይ እንደሚከናወንና ፕሮጀክቱ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ አንደኛው ግብዓት ነው። አጠቃላይ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዟል።
የቢቢሲ ዘጋቢ ቃል ኪዳን ይበልጣል እንደዘገበችው፤ በአዲስ አበባ ስለችግኝ ተከላው የተለያዩ ማስታወቂያዎች ሲነገሩና በመገናኛ ብዙኃን በኩል የተለያዩ ቅስቀሳዎች ሲደረጉ ነበር። እአአ 2016 በህንድ 800ሺ በጎ ፈቃደኞች በአንድ ቀን 66 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረወሰን ይዘው ነበር። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያን ምንጭ አድርጎ የዜና ምንጩ እንደዘገበው፤ በኢትዮጵያ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ 5፡21 ድረስ 67 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል የዓለም ክብረወሰን መያዝ ችላለች።
በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርባ ምንጭ ላይ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር ንብረት ለውጦችን ለመቆጣጠር የችግኝ ተከላ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ በንግግሮቻቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል። በእቅድ የተያዘውን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መቶ ሚሊዮን ህዝብ ሁለት ችግኝ መትከል ይጠበቅበታል።
ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብዙ ችግኝ የመትከል ሪከርድ አስመዘገበች
ዘኔሽን
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር በአንድ ቀን ከሁለት መቶ ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ቀድሞ የነበረውን ሪከርድ በማሻሻል አዲስ ሪከርድ አስመዝግባለች። ዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በቲውተር ገፁ ያሰፈረውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በአረንጓዴ አሻራ ቀን በተተከለው ችግኝ ኢትዮጵያ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቧን አትቷል። ከ224 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እስከ ከሰዓት ድረስ መትከል በመቻሉና በህንድ ተይዞ የነበረውን በአንድ ቀን ብዙ ችግኝ የመትከል ሪከርድ መስበር መቻሉን ዘገባው ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬትን ምንጭ አድርጎ ጠቅሷል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉም ዜጋ በእለቱ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ባደረጉት ጥሪ በአገሪቱ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ ተደርጎ ሁሉም ህብረተሰብ በተከላው ተሳታፊ ሆኗል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአገሪቱ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተከናወነ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ባወጣው ሪፖርት በአገሪቱ ዋነኛ ችግር የሆኑት የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር ለምነት ማጣት፣ የደን መመንጠር፣ የብዝሀ ህይወት መመናመን፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የአየር ብክለት የአየር ንብረት ለውጡ ያስከተላቸው ችግሮች ናቸው።
‹‹ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተከለች››
አሶሼትድ ፕረስ
ኢትዮጵያ ከ200 ሚሊዮን ችግኞች በላይ በመትከል የአለም ሪከርድ አስመዘገበች። ይህ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ችግኝ ተከላ ሀሳብ የቀረበው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሲሆን ዓላማውም በአገሪቱ የደን ሀብቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና የደን ሀብቱን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ነው።
የዜና ምንጩ ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬትን ምንጭ አድርጎ እንደዘገበው፣ በዕለቱ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ የተያዘ ቢሆንም በተደረገው ተከላ ከ224 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በቲውተር ገፁ ያሰፈረውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በአረንጓዴ አሻራ ቀን በተተከለው ችግኝ ኢትዮጵያ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቧን አትቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የችግኝ ተከላ አካሂደዋል። ኢትዮጵያ ከግንቦት ወር እስከ ጥቅምት ወር ድረስ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ነው። የግብርና ኃላፊዎች እንደሚሉት፤ ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ መተከሉን ጠቅሰዋል።
እንደ ፋርም አፍሪካ አገላለፅ፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአገሪቱ የደን ሽፋን 30 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአገሪቱ በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥር የእርሻ መሬት በማነሱ ምክንያት የደን ሀብቱ እየተመናመነ ይገኛል። በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች እና የንግዱ ማህበረሰብ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ከፍተኛ ርብርብ በማድረጉ በህንድ በአንድ ቀን ተተክሎ የነበረውን የ66 ሚሊዮን ችግኝ ሪከርድ መስበር ተችሏል።
እስካሁን የጊነስ ወርልድ ሪከርድ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብዙ ችግኝ የመትከል ሪከርድ መውሰዷ ላይ ያለው ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትን ዋቢ ያደረገው አሾሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፤ ለችግኝ ተከላው በተሰራው ሶፍትዌር የተተከሉት ችግኞች ምን ያክል እንደሆኑ የመቁጠር ስራ ተከናውኗል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር