
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብርቅዬ እንስሳ የሆነው ዋሊያ አይቤክስ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ለተዘጋጀው ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስገነዘበ።
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ምርምርና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፈቀደ ረጋሳ (ዶ/ር) በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ በኮሮና እና በሰሜኑ ጦርነት ወቅቶች በተፈጠረ ክፍተት በአማራ ክልል ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኘው በዋሊያ አይቤክስ ላይ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል፤ ይህን ተከትሎም ቁጥሩም እየተመናመነ መጥቷል።
ይህን አደጋ ለመቀልበስ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ የዱር እንስሳውን መታደግ ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በተለይ ፓርኩ ያለበት አካባቢ ማህበረሰብ ከመንግሥትም ሆነ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ቢሮ በላይ ለብሄራዊ ፓርኩ ጥበቃ ማድረግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
የዱር እንስሳው በሕገ ወጥ አደን እና በግጦሽ መሬት ፍላጎት መጨመር ስጋት ውስጥ ገብቶ መቆየቱን አስታውሰው፣ የዱር እንስሳውን ለመታደግ የሚያስችል ስትራቴጂክ ጥናት ተካሂዶ እቅድ መውጣቱን ገልጸዋል። በጥናቱ መሠረት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ከማስቀመጥ ጀምሮ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በማድረግ ቀጣይ ዋስትናውን ለማረጋገጥ መታቀዱን አስታውቀዋል።
ስትራቴጂክ ጥናቱ ሕግ በማውጣት እና የወጡ የዱር እንስሳት ጥበቃ ሕጎችን በማጠንከር ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑን አስገንዝበው፣ ማህበረሰቡ ለሕጉ ተገዢ እንዲሆን የማብቃት ሥራ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በተለይ ስለብሄራዊ ፓርክ እና ስለብርቅዬ እንስሳዎቹ ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የራሳችንን ሀብት ራሳችን የምንጠብቅበት ሁኔታ መፈጠሩ በቀጣይ ነገሮችን አስተካክሎ ለመሄድ ሚናው ከፍ ያለ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
ስትራቴጂክ እቅዱ መፍትሄ ተኮር ዓላማ ማንገቡን ጠቅሰው፣ ለአምስት ዓመታት የሚተገበርና በዋሊያ አይቤክስ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በመቅረፍ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል። ስትራቴጂክ እቅዱ በጥናት እና በብዙሃን ተሳትፎ የጎለበተ መሆኑን አስታውቀው፣ ከመንግሥት አካላት ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደተሳተፉበትም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የሕግ ማሕቀፉን በማስተካከል ህልውናውን ማስጠበቅ ቀዳሚ ሥራ መሆኑ ሲነሳ ቁጥሩን በመጨመር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደነበረበት ለመመለስ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የመሪነት ሚናውን ይወጣል። በትግበራው ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብርም ይካሄዳል።
ስካውቶችን በማሠልጠን እና የዋሊያ አምባሳደሮችን በማዘጋጀት እንደሀገር ሰፊ ንቅናቄ መዘጋጀቱን አስታውቀው፣ በዋሊያ ላይ እየደረሰ ላለው የህልውና ስጋት ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም