
ዜናሐተታ
የሰው ልጆች የአኗኗር መልክ ሁሌም በአብሮነት ሂደት ይገለጻል። ይህ ማህበራዊነት ደግሞ አንዳንዴ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ ችግሮች እክል ሊያጋጥመው ይችላል። እንዲህ በሆነ ጊዜ የሌሎችን ትኩረት የሚሹና በብዙ አጋርነቶች የሚገለጹ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ኃላፊነቶች በተግባር ይተረጎማሉ።
በርካቶች ከራሳቸው መልካም ማንነት በመነሳት ለብዙሃን የበጎፈቃድ አገልግሎትን ይሰጣሉ። ይህን ሲያደርጉ በማንም አስገዳጅነትና ግፊት ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታቸው በሚፈቅደው ይሁንታ ላይ ተመርኩዘው ነው። ከግለሰቦች በጎነት ባለፈ በተቋማት ላይ በሚስተዋለው እውነታም በርካታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በማህበረሰቡ መሃል ሲገኙ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን አሟልተው ማህበራዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ።
ይህ አይነቱ የማህበራዊ ግዴታ አገልግሎት በበርካታ ቦታዎችና ማህበረሰብ ዕውን ሲሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መልስ ያገኛሉ። በአብሮነት ትስስርም ሕይወት፣ ኑሮና አካባቢዎች ይለወጣሉ። በዚህ ለውጥ መሃል የሚመዘገበው የማህበራዊ ግዴታ ኃላፊነትም ለአካባቢውና ለስፍራው ነዋሪዎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ይሆናል።
ዋነኛ ሥራውን በአበባ ኢንቨስትመንት ላይ ያደረገው ሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ፤ በዝዋይና አካባቢው ለሃያ ዓመታት የልማት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ ኩባንያ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በዓለም ገበያው ተመራጭ የሆኑ አበቦችን በጥራት በማምራት ለውጭ ሀገራት በሽያጭ ማቅረብ ነው። ይህ ተግባር የኩባንያው የዓመታት መገለጫ ይሁን እንጂ አገልግሎቱ ግን በዚህ ብቻ አልተገደበም።
ወይዘሮ የዝና አያሌው በሼር ኢትዮጵያ ኩባንያ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ናቸው። ኩባንያው በዝዋይና አካባቢው ለዓመታት ሲቆይ በርካታ ማሕበራዊ ሃላፊነቶችን እየተወጣ መሆኑን ይናገራሉ። ከእነዚህ መገለጫዎች መሀል ለአካባቢው ነዋሪዎች የከፈተው የሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል አንዱ ነው ይላሉ።
እንደ ሃላፊዋ ገለጻ ሆስፒታሉ ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአበባ እርሻ ልማቱ ሠራተኞች ሙሉ ለሙሉ ነጻ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ። የአበባ እርሻ ልማቱ ዝዋይ ላይ የተቋቋመ እንደመሆኑ ሁሉም ሠራተኞች ተጠቃሚዎች ናቸው የሚሉት ኃላፊዋ ለአካባቢው ነዋሪዎችም አነስተኛ በሆነ ክፍያ አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ይገልፃሉ።
ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት በአካባቢው ሆስፒታል አልነበረም›› የሚሉት የዝና ፤ይህ ሆስፒታል ያለፉትን ሁለት አስር ዓመታት ነዋሪውን በብቸኝነት በማገልገል ማህበራዊ ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱን ያስታውሳሉ።
አቶ ኑራ ነገዎ የሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። አቶ ኑራ እንደሚሉትም ሆስፒታሉ እንደማንኛውም ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ተቋም አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶችን ያሟላ ነው። ሁሉን አቀፍ ግልጋሎት እንደመስጠቱ የህፃናትና የእናቶችን ጤና ጨምሮ እስከ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና የሚደርስ አገልግሎት ይካሄድበታል።
የሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል በቅርብ ጊዜ በአካባቢው በተከፈተው የመንግሥት ሆስፒታል ምክንያት የነበረበት ጫና ቀንሶለታል። እንዲያም ሆኖ በቀን ከሶስት መቶ በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ለዓመታት ህክምና የሚሰጣቸው፣ ከአምስት መቶ በላይ ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ወገኖችም የነጻ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው። ሆስፒታሉ ለማህበረሰቡ ከሚያበረክተው የአነስተኛ ክፍያ ግልጋሎት ባለፈ በአካባቢው ለሚገኙ ከሃምሳ በላይ ድርጅቶች የዱቤ አገልግሎት በማበርከት ላይ እንደሆነ አብራርተዋል።
ፍጹም ፀጥታ የሞላውን ሰፊውን የሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል መጎብኘት ይዘናል። በየክፍሉ በሥርዓት የተዘረጉት አልጋዎች በንጹህ አልባሳት ተሸፍነዋል። የማዋላጃ ክፍሎች የላብራቶሪና የኤክስሬ መሣሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው። የፊዚዮቴራፒ አገልግሎትም እንዲሁ በመሰጠት ላይ ይገኛል። ሆስፒታሉ ከሌሎች ለየት ያደርገዋል የተባለውን እውነት በመስማታችን ለሚመለከታቸው ጥያቄዎችን አቀረብን። የአቶ ኑራ ምላሽም ሆስፒታሉ ሥራውን በቴክኖሎጂ የሚያቀላጥፍለት ‹‹ኢንተርኬር›› የሚባል የራሱ የሶፍትዌር መተዳደሪያ እንዳለው ነገሩን።
በሆስፒታሉ በዚህ ሶፍትዌር የእያንዳንዱን ታካሚ ማንነት በለየ መልኩ ጠቋሚ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ሂደት ከኤክስሬ እስከ ካርድ ክፍል በቀላል መንገድ የሚተገበር ነው። በዚህም የወረቀት ልማድን በመተው የኤሌክትሮኒክስ አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል።
አቶ ኑራ እንደሚሉት ፤ ሆስፒታሉ ስምንት ሀኪሞች አሉት። ሶስት በተለያዩ ህክምናዎች የሚታወቁ ስፔሻሊስት ሀኪሞችም አገልግሎት እየሰጡ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ባለሙያዎች ተጠቃሚውን የማገልገል ማህበራዊ ሃላፊነቶችን በመወጣት ላይ ናቸው።
የአበባ አርሻ ልማቱ በየጊዜው ለሆስፒታሉ አስፈላጊ የሚባሉ መድሃኒቶችንና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት ችግሮችን ይፈታል። እንዲህ መሆኑ ቀደም ሲል ወደ ውጭ ተልከው ውጤት የሚጠበቅባቸውን ምርመራዎች ለማስቀረት ተችሏል።
ዶክተር ነጻነት አበበ፤ በሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል የጥርስ ሀኪም ናቸው። ዶክተሯ እንደሚሉት በሆስፒታሉ የጥርስ መንቀልን ጨምሮ ተያያዥ ህክምናዎች ይከናወናሉ። ለዚህ ሕክምና ጠቀሜታ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪዎች መኖራቸውና ሙያው በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መተግበሩ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ውጤታማ እንዳደረገው ይናገራሉ።
በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ለዓመታት ያገለገለችው ወይዘሮ የውብዳር ፋንታዬም የሆስፒታሉን ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶች የምትገልጸው ከታላቅ ምስጋና ጋር ነው። ወይዘሮዋ የእሷን ልጆች ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በነጻ መማራቸውን ትገልጻለች።
ሆስፒታሉ ለአበባ እርሻ ልማቱ ሠራተኞች የጤና ክትትል ከማድረግ ባሻገር ለከፍተኛ ሕክምና ውጭ ሀገር ድረስ እስከመላክ ዕድልን ይሰጣል። በዚህም የውብዳር የብዙሃኑ ሠራተኛ የጤና ዋስትና ተረጋግጧል ትላለች።
የሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ለአካባቢው ህብረተሰብ ከሚሠጠው የጤና አገልግሎት ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ግዴታዎችን ይወጣል። በከተማው የ‹‹ሀርቨር ግሮስ›› ልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤትን በመክፈትም የጤና ችግር ያለባቸውን ልጆች በነጻ እያስተማረ ነው።
ድርጅቱ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ተገቢውን መጠለያ በመሥራትም ማሕበራዊ ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል። ይህ እውነት የአካባቢውን ነዋሪዎች ሠብዓዊ ችግሮች በመፍታት ማህበራዊ ሃላፊነቶችን በተግባር ለማሳየት ያስቻለ መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም