
አዲስ አበባ፦ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተተገበረው ብሄራዊ ሪፎርም ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ። ሪፎርሙ ዘርፉን ከዋና ዋና የኢኮኖሚ መሰሶዎች መካከል አንዱ አድርጎታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በሚያሳትመው የእንግሊዝኛ ዲጂታል መፅሄት ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ሚኒስትሯ፤ ሪፎርሙ ቱሪዝም ሚኒስቴር እራሱን ችሎ እንዲደራጅ ከማድረጉም ባሻገር በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ መስህቦችን ለማልማት እና መዳረሻ ለማድረግ ቅድሚያ የሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ሪፎረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ የሚያሳድግ የተሻሻለ የፖሊሲ ማሕቀፍ በማዘጋጀት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል ማሕቀፍ እየተፈጠረ ነው። የፖሊሲ ማሻሻያውም ከወቅቱ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመድና ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲኖራት እድል የሚከፍት ነው። የፖሊሲ ማሻሻያው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አካታች ስልትን ተከትሎ የመጨረሻው ለትግበራ ምዕራፍ መድረሱን ገልፀዋል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለሁለተኛ ጊዜ አሳትሞ ባሰራጨው የእንግሊዝኛ ዲጂታል መፅሄት ላይ ይፋ እንደተደረገው፤ የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ አጠቃላይ የማሻሻያ ክለሳ ለአንድ ዓመት ከፈጀ የምክክር ሂደት በኋላ ተጠናቋል።
በረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅቱ ላይ ቁልፍ ሚና የነበራቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፖሊሲ ተንታኝ የዚህ ዓለም ሲሳይ (ዶ/ር)፤ የተሻሻለው ማሕቀፍ የመዳረሻ ልማት፣ የቅርስ ጥበቃ፣ የቴክኖሎጂ ውህደት እና የባለድርሻ አካላት ትብብርን ጨምሮ በሰባት ምሰሶዎች ላይ ያተኩራል ብለዋል። ፖሊሲው ዘላቂነትን፣ ማህበረሰብ ማጎልበት እና የአየር ንብረት ለውጥ እና የጂኦፖለቲካል ለውጦች በቂ ምላሽ ለመስጠት እድል የሚሰጥ ነው።
ሕዝብ ግንኙነቱ አሳትሞ በይፋ ባሰራጨው የዲጂታል መረጃ መስጫ መፅሄት ላይ እንደተመላከተው፤ ሪፎርሙን ተከትሎ በዘርፉ በመሠረተ ልማትና በቅርስ እድሳት ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል። በተለይ በቅርቡ እየተገነቡ አገልግሎት ላይ የዋሉ መዳረሻ ልማቶች ኢትዮጵያን ተመራጭ መዳረሻ እያደረጓት መሆኑን አመላክቷል።
በጎንደር የሚገኙት ታሪካዊው የፋሲለደስ ግንቦች ለዓመት የፈጀ እድሳት ተደርጎላቸው ከወትሮው የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኙና የቱሪስት መስህብነታቸው እንዲጨምር፤ የአዲስ-አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል በአዲስ አበባ በመክፈት ፣ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የሚያስተናግዱ ዘመናዊ መገልገያዎች እንዲኖር ማድረጉን አመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቶቹን ‹‹የኢትዮጵያን ድብቅ ውበትና መስህቦች ለመግለፅ የተደረገው ሰፊ ጥረት አካል ነው›› ሲሉ ማድነቃቸውንም አውስቷል።
እንደ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ መረጃ፤ አዲስ አበባን በአፍሪካ ትልቁ የአየር መጓጓዣ ማዕከል መሆኗን በማሳየት ቱሪዝምን ለማቆም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም አቅርቦቷን በ ITB Berlin 2025 አውደ ርዕይ ማሳየቷን፤ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር በፕራግ የሉሲ እና የሰላም ቅሪተ አካላትን ለማሳየት ስምምነት መድረሷን፤ ታዋቂው ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን እና የሬጌ ኮከብ ፕሮቶጄ በሚዲያ ዘመቻዎች የኢትዮጵያን መስህቦች አጉልተው ማሳየታቸውን እንደ ስኬት ተጠቅሷል። እነዚህ ውጤታማ ሥራዎች ባለፉት ጥቂት የሪፎርም ዓመታት ተግባራዊ መሆናቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በ2024 ከዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ፍሰት በ40 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገብ በአፍሪካ ፈጣን የቱሪስት መዳረሻ አንዷ ሆናለች። ስኬቱ ከተሻሻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የቱሪዝም ፖሊሲ ጋር የሚገጣጠም ሲሆን ዘላቂ እድገትን ለማምጣት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ተስፋ ሰጪ ምሳሌ እንደሆነ ያመላክታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም