
በለጠ ሞላ (ዶ/ር ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት 800 ቢሊዮን ብር በዲጂታል ክፍያ መንቀሳቀሱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ሚኒስትሩ የተቋሙን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ በዲጂታል ኢኮኖሚው መስክ በገንዘብ ዝውውር ረገድ እንደ ቴሌ ብር፤ ሲቢ ብርና ሌሎች መተግበሪያዎችን በመጠቀም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 800 ቢሊዮን ብር በዲጂታል ክፍያ ለማንቀሳቀስ ተችሏል። ይህ አንዱ የለውጡ ውጤት ሲሆን ገንዘብ ለማተም ብቻ እንደ ሀገር ሲወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት ያስቻለም ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የሰው ሀብት ልማት ትልቅ ትኩረት እንደሚፈልግ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ከተጀመረ በኋላ እስካሁን 688 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተመዝግበው ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ 270 ሺህ የሚሆነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምስክር ወረቀት ለማግኘት መብቃታቸውን አብራርተዋል። ይህም ሆኖ በሶስት ዓመት ውስጥ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ የተቀመጠ በመሆኑ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ካሉት ዋና ዋና ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ዲጂላይዜሽንን ማስፋፋት እንደሆነ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ተደራሽ ማድረግና አጠቃላይ ሥርዓቱን ማዘመን የሚጠበቅ ይሆናል። በዚህም ረገድ በዘርፉ ያለውን የሥራ እድል ፈጠራ ቁጥር በሚጠበቀው ደረጃ ለመጨመር ከመንግሥት፤ ከግሉ ዘርፍና በውጭ ሀገራት ካሉ ጋር በመተባበር የተቀመጠው እቅድ እንዲሳካ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረው እንዳብራሩት፤ በአሁኑ ወቅት አንደ ሀገር አጠቃላይ ያለው የዲጂታል ኢኮ ሲስተም ጥሩ እድገት እያሳየ ይገኛል። በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ረገድም ባሉት ሁለት ኦፕሬተሮች ኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪ ኮም በስፋት የማገናኛዎች ዝርጋታ እየተከናወነ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም የኢንተርኔትም ሆነ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
የዲጂታል መታወቂያንም በተመለከተ እስካሁን 14 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህ ከእቅዱ አንጻር አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በስታርት አፕ፣ በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ብዙ የተሠራ እንደሆነ አመልክተው፤ ለቀጣይ የፖሊሲ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት፣ ማጸደቅና ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅ በመሆኑ ፖሊሲዎች እየተዘጋጁ ይገኛል። እነዚህ ተግባራዊ ሲደረጉ አሁን ከተገኘው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም