የብየዳ ሙያተኞች በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው

> እንደ አህጉር ያለውን እውቀትና ክህሎት አስተባብሮ መጠቀም ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- እንደአህጉር ያለንን እውቀት፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ አስተባብሮ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ) ገለጹ።

3ኛው የአፍሪካ የብየዳ ፌደሬሽን ዓመታዊ ጉባዔ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ “የአፍሪካን የብየዳ ሙያ በማጎልበት ቀጣናዊ ትስስር እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል ትናንት በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ) እንዳሉት፤ አፍሪካ የወጣቶችና የአዳዲስ ምሩቃን አህጉር ናት። እነዚህን ወጣቶች በእውቀትና በክህሎት ማነጽ፣ እንደአህጉር ያለንን እውቀት፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ አስተባብሮ መጠቀም ይገባናል ብለዋል።

የብየዳ ቴክኖሎጂ መጠናከር ለኢንዱስትሪዎችና ለሌሎችም ዘርፎች ትልቅ አአስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጉባዔው ሀገራት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮዎች በመጋራት ለአህጉራዊ ኢንዱስትሪዎች መጠናከር መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

በጋራ መሥራትና ልምድ መለዋወጥ ያላየነውን እድል ለማየት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ጸጋ የሌሎችም ሀገራት፣ ከሌሎች ሀገራት ያለ ጸጋም የኢትዮጵያ ጭምር መሆኑን አስበን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ ለሚገኘው እውቀት የምንሰጠውን ትኩረት ያህል ከቴክነክ ሙያ ለሚገኝ ክህሎትም መስጠት እንደሚያስፈልግ አመላክተው፤ ኢትዮጵያ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በማቋቋም ጭምር የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ሠልጣኞች በተግባር የተደገፈ ክህሎት ባለቤት ሆነው እንዲወጡ እየሠራች መሆኑን ጠቁመዋል።

የብየዳ ባለሙያዎች ለአንድ ሀገር እድገት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ እና  ኢነርጂ ዘርፍ ሥራዎች ይበልጡን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጉባዔው በአፍሪካ ሀገራት መካከል የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና ተመሳሳይ ደረጃን (ስታንዳድርድ) መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው። ይህም ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር ሄደው መሥራት የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በፊት የአፍሪካ የብየዳ ፌዴሬሽን አባል መሆኗን ገልጸው፤ አፍሪካ እንደአህጉር ዘርፉ ላይ ተቀራራቢ ክህሎት እንዲኖር የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክህሎትን ከማልማት ጎን ለጎን ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይም እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ የብየዳ ሙያ በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪዎችና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

በመሆኑም በየአካባቢው በልምድ ከሚሠራው ሥራ ወጥቶ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂና ክህሎት ያላቸው ዜጎችን በማፍራት በየትኛውም ቦታ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፤

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር)፤ ብየዳ በአጠቃላይ ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በኢንስቲትዩቱ ስር ዓለም አቀፍ የብየዳ ማዕከል መኖሩን ጠቅሰው፤ በዚህ ማእከል አማካኝነት ብቁ ሙያተኞችን ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጉባዔው በኢትዮጵያ መካሄዱም በሀገራት መካከል ትስስር ለመፍጠርና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

የአፍሪካ የብየዳ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሀሚድ አሕመድ እንደገለፁት፤ የአፍሪካ ብየዳ ፌዴሬሽን በዘርፉ ላይ አባል ሀገራቱ ያላቸውን አቅም እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረገ ነው።

ፌዴሬሽኑ በተቋቋመበት በስድስት ዓመታት ውስጥ 13 አባል ሀገራትን ማፍራት መቻሉን ጠቅሰው፤ ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠት፣ ጥናቶችን በማካሄድና አጋርነቶችን በመፍጠር የአህጉሪቱ የብየዳ ሙያተኞች በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን ለማስተሳሰር እየተጫወተች ያለው የመሪነት ሚና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አውስተው፤ ጉባዔው እንዲሳካ ላደረገችው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

ጉባዔው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You