
አዲስ አበባ፡- ‹‹በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተመረጡ አምስት የእድገት ምንጮች ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የባለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን አብራርተዋል።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ በተቀመ ጠው የ 10 ዓመት እቅድ መሠረት ተከታታይ የሆኑ ሪፎር ሞች ተደርገዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲናጠናቀቅ ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።
የሪፎርም ትግበራው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣የዘርፎችንምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ፤ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከባቢን ማሻሻል ፣ የመንግ ሥትን የመፈጸም አቅም ማሳደግ በሚሉት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች እንዳሉ ሆኖ በተመረጡ አምስት የእድገት ምንጮች ላይ በተሠሩት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል። በግብርና ዘርፍ የመኸር ምርት እድገት ማሳየቱንና የበጋ ስንዴን ውጤታማነት ጠቅሰዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢነርጂ ፍጆታ መጨመሩን የማምረት አቅም እያደገ መሆኑን የሚያመላከት ነው፡፡
ብለዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የብረትና የሲሚንቶ ምርት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል። በቱሪዝም እና ዲጂታል ዘርፍም መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸዋል።
ፍጹም (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 8 ነጥብ 4 በመቶ እንደሚያድግ እና ሁሉም ዘርፎች ጠንካራና አዎንታዊ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ግመታው ያሳያል ብለዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚው የሪፎርሙ ውጤት ተደርገው የሚወሰዱት የሀገር ውስጥ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት መሆናቸውንም አንስተዋል። ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት በጂዲፒ ያላቸው ድርሻ ከ2015 በጀት ዓመት በፊት መቀዛቀዝ የታየበት ነበር ያሉት ፍጹም ዶ/ር)፤ ለአብነትም ኢንቨስትመንት በ2016 ከጂዲፒ 20 በመቶ ፤ በ2017 23 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚሆን አሁን ያሉት አፈጻጸሞች ያመላክታሉ ብለዋል።ይህም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያመጣው ለውጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለአድገት ወሳኝ ሚና የሚጫተው አንዱ የፌዴራል መንግሥት ገቢ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ከገቢ ጋር በተገናኘ የሪፎርም ሥራዎችን የሚያስተባብር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በየሳምቱ እየተገናኘ የታክስ ፖሊሲን፣ የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎችን ፣ ዲጂታይዜሽን በአጠቃላይ ከታክስ ጋር የተገናኙ ብልሹ አሠራሮችን መፍታት የሚያስችሉ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ከፌዴራል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ ፈተና የነበረው ፊሲካል አቅም እንደነበር ጠቅሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን በማሻሻል፤ የክልሎችን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻለ የጋራ ገቢ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ድጎማ መደረጉን ጠቅሰው፤ ባለፉት 9 ወራት 211 ቢሊዮን ብር ድጎማ እንደተደረገ እና ዓመቱ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚው ጤንነት አመላካች የብድር ሁኔታ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ጋር በተደረገ ትብብር ከፍተኛ የእዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አስገንዝበዋል።
የእዳ ሽግሽጉ ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት የ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጊዜያዊ የእዳ ክፍያ የማቆም እድል መገኘቱ ጫናን እንደቀነሰ እና ያለውን ገንዘብ ለልማት ለማዋል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።በአጠቃላይ ሪፎርሙ የ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እዳ ሽግሽግ ይዞ የመጣ ስለመሆኑ አመልክተዋል።
በ2017 ይህ የእዳ ሽግሽግ ባይገኝ ኖሮ ይከፈል የነበረው እዳ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ጠቅሰው፤ የእዳ ሽግሽግ መገኘቱ የእዳ ክፍያውን ወደ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር አውርዶታል ብለዋል።
በሪፎርም ሥራው ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንጻር አጠቃላይ የአሠራር ለውጥ በማድረግ ሁሉንም ትርፋማ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል። በዚህም የመንግሥት የልማት ርጅቶች ጠቅላላ ገቢ አንድ ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ሆኗል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማምጣታቸውን ፤ 98 ቢሊዮን ብር ታክስ መክፈላቸውን፤ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን የመንግሥት ትርፍ ድርሻ ለገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ፓስፖርትን ጨምሮ የሴኩሪቲ ህትመት በሀገር ውስጥ ማድረግ እንደተቻለ ፣ የኢትዮጵያ የሰነዶች ሙዓለ ነዋይ ገበያ መጀመሩ ፣ የኢትዮ ግሪን ኩባንያ መቋቋሙ፣ የውጭ ምንዛሪ ሪፎርምና ከዚያው ጋር የተያያዙ አፈጻጸሞች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሚገኙ ጠቅሰው፤ በዚህም የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጨመሩን ገልጸዋል።
በተለይም በማዕድን ፣ በገቢና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የታዩ ለውጦችን በሌሎችም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም