አሜሪካና ኢራን በኑክሌር ጉዳይ ይስማሙ ይሆን?

ተጠባቂው የአሜሪካና የኢራን የኑክሌር ውይይት በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት ተካሂዷል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያደረጉት ውይይት ለኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ውዝግብ አንዳች መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል በሚል ተስፋ መላው ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበር ተገልጿል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በውይይቱ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢራን ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባት በድጋሚ አስጠንቅቀው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር ጉዳይ ወደፊት ስለሚደረጉ ውይይቶች

በአስተዳደራቸውና በኢራን መካከል ቀጥተኛ ንግግሮች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።‹‹ከኢራን ጋር በቀጥታ እየተነጋገርን ነው፤ ቅዳሜ ትልቅ ውይይት ይኖረናል›› ብለው ነበር።ኢራን ግን ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ መነጋገር እንደማትፈልግ ቀደም ብላ በማሳወቋ ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ‹‹በሁለቱ ሀገራት ንግግር ጉዳይ ላይ የተለወጠ አቋም ይኖር ይሆን?›› የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹የቀጥታ ንግግር ላይኖር እንደ ሚችል ሲወራ ቆይቷል። ብዙ ሰዎች ‹በቀጥታ አትነጋገሩም፤ በሦስተኛ ወገን በኩል ልትደራደሩ ነው› ሲሉ ነበር። አሁን ግን ቀጥተኛ ንግግሮችን እያደረግን ነው። ስምምነት ላይ ልንደርስም እንችላለን። ስምምነት ላይ መድረስ የተሻለ ነው›› ብለዋል። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ ግን ከአሜሪካው የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ኦማን ላይ በሌላ አደራዳሪ በኩል እንደሚነጋገሩ መግለጻቸው ይታወቃል።

የአሜሪካ ልዑክ በስቲቭ ዊትኮፍ የተመራ ሲሆን፣ በኢራን በኩል የልዑክ ቡድኑ መሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ፣ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ማጂድ ታኽት-ራቫንቺ፣ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትሩ ካዘም ጋሪባባዲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ሁለቱም ሀገራት ‹‹ገንቢ›› በማለት ገልፀውታል። ሁለት ሰዓት ከግማሽ የፈጀው የመጀመሪያው ውይይት ለቀጣይ ውይይቶች መሠረት የተጣለበት መድረክ እንደሆነም ተገልጿል። የአሜሪካና የኢራን ተወያዮች በኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር ቢን ሃማድ አል-ቡሳይዲ በኩል የተነጋገሩ ሲሆን፣ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ስቲቭ ዊትኮፍ እና አባስ አራግቺን ጨምሮ የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች ለጥቂት ደቂቃዎች ፊት ለፊት ተገናኝተዋል።

በእርግጥ ሁለቱ ሀገራት ስለውይይቱ የያዙት አቋም እስካሁን እንደተለያየ ነው።አሜሪካ ውይይቱን ‹‹ቀጥተኛ ንግግር›› በማለት ስትገልጸው፣ ኢራን በበኩሏ ውይይቱ ቀጥተኛ ንግግር ሳይሆን በኦማን ባለሥልጣናት በኩል የተደረገ እንደሆነ ገልፃለች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ውይይቱ ከተጀመረ በኋላ ባሰራጩት አጭር መልዕክት፣ ውይይቱ በቀጥታ ሳይሆን በኦማን አደራዳሪዎች በኩል እየተካሄደ እንደሚገኝና በውይይቱ የሚነሳው ብቸኛ ጉዳይ የኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር እንደሆነም ተናግረው ነበር።

የአልጀዚራ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች አርታኢ ጀምስ ቤይስ ከኦማኑ ስብሰባ ብዙም ውጤት መጠበቅ እንደማይገባ አሳስቦ፣ ‹‹ጠቃሚውና ወሳኙ ጉዳይ ንግግሩ ጨርሶ አለመክሸፉና ሂደቱ መጀመሩ ነው›› ብሏል።

‹‹ዋይት ሃውስ›› ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ውይይቱ ገንቢና አወንታዊ እንደነበር አመልክቷል። ‹‹ጉዳዮቹ ውስብስብ ናቸው። የልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ የቀጥታ ንግግር የጋራ ተጠቃሚነት ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ወሳኝ ርምጃ ነው። ዊትኮፍ ልዩነቶችን ከተቻለ በውይይት እና በዲፕሎማሲ ለመፍታት እንደሚፈለግ ለኢራን ገልፀዋል›› ብሏል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺም ስለውይይቱ የተናገሩት አዎንታዊ ሃሳብ ነው። ‹‹በእኔ አስተ ያየት የመጀመሪያው ስብሰባ በጣም ሰላማዊ እና መከባበር በተሞላበት መንገድ የተካሄደ ገንቢ ስብሰባ ነበር። ምክንያቱም ምንም አይነት ተገቢ ያልሆነ ቋንቋ አልነበረም። ሁለቱም ወገኖች ውይይቱን ወደ ስምምነት ለማድረስ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል›› ሲሉ ለኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ተናግረዋል። የአራግቺ ዲፕሎማሲያዊ ቃላት እንደሚጠቁሙት ከሆነ በስቲቭ ዊትኮፍ የሚመራው የአሜሪካ ቡድን ‹‹ይህ ውይይት ካልተሳካ ኢራን ትልቅ አደጋ ሊደርስባት ይችላል›› በማለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋግመው የተናገሩትን ዛቻ አለመጠቀሙን ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ሁለተኛው ዙር ውይይት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚካሄድም ሁለቱም ወገኖች አረጋግጠዋል። ቀጣዩ ውይይት በቀጥታ ይሁን በሦስተኛ ወገን በኩል እንዴት እንደሚካሄድ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለኢራን ካላቸው አመለካከት አንፃር በርካቶች የሁለቱን ወገኖች ውይይት ፍሬያማነት ይጠራጠሩታል። ለአብነት ያህል ትራምፕ ኢራን በውይይት ስምምነት ላይ ካልደረሰች ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባት ደጋግመው ማስጠንቀቃቸውን የጥርጣሬያቼው ማስደገፊያ አድርገው ያቀርቡታል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው አርብ ዕለት ምሽት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ‹‹ኢራን ታላቅና ደስተኛ ሀገር እንድትሆን እፈልጋለሁ፤ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ግን ሊኖራት አይችልም። ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ለኢራን መጥፎ ቀን ይሆናል›› ብለው ነበር። የ‹‹ዋይት ሃውስ›› የፕሬስ ኃላፊ ካሮሊን ሌቪት፣ በሀገራቱ ውይይት ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያስቀመጡት እቅድ ካልተሳካ ኢራን የምትከፍለው ከባድ ዋጋ እንዳለባት በመግለፅ የአለቃቸውን ዛቻ ደግመውታል።

የኢራን የዓለም አቀፍና የፀጥታ ስትራቴጂ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ሙስጠፋ ናጃፊ እንደሚያብራሩት፣ ዋሺንግተንና ቴህራን ውይይቶቹ በሚያተኩሩባቸው እና ከስምምነት ላይ ሊደረስባቸው በሚገቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ልዩነቶች አሏቸው። ‹‹ኢራን በውይይቶቹ የሚነሳው ብቸኛ ጉዳይ የኑክሌር መርሃ ግብሯ እንዲሆን ትፈልጋለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ኢራን የኑክሌርና የባሊስቲክ ሚሳኢሎቿን መሥሪያዎች እንድታወድም ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ያላትን ፖሊሲ እንድትቀይርም ይፈልጋሉ።ኢራን ደግሞ ይህን ዓይነቱን ሃሳብ እንደቀልድ ትቆጥረዋለች።አሜሪካ በኢራን ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር አካሄዷን የምትገፋበት ከሆነ ውይይቶቹ መክሸፋቸው አይቀርም›› ይላሉ።

በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (European Council On Foreign Relations) የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ኤሊ ጌራንማይህ፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር በምታደርገው ድርድር ፍላጎቷ ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ‹‹ኢራን በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ መደራደር እንደምትፈልግ በግልፅ አሳውቃለች። የአሜሪካስ? ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን በወሰኗ ውስጥ ዩራኒየም እንድታበለጽግ ይስማማሉ ወይንስ የኑክሌር መሥሪያዎቿን እንድታስወግድ ይፈልጋሉ የሚሉት አማራጮች ግልጽ መልስ የላቸውም። ስለዚህ ዋናዎቹ ጉዳዮች በግልጽ ተለይተው መቀመጥ አለባቸው›› በማለት በሀገራቱ የመስማማት ተስፋ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ያስረዳሉ።

የትራምፕ ባለሥልጣናትም ቢሆኑ በጉዳዩ ላይ ወጥ አቋም ይዘዋል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ማይክ ዋልዝ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን የኑክሌር መሥሪያዎቿን ሙሉ በሙሉ እንድታስወግድ እንደሚፈልጉ ለ‹ሲቢኤስ ኒውስ› (CBS News) የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።

ልዩ መልዕክተኛው ዊትኮፍ በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በላኩት ደብዳቤ ኢራን የኑክሌር ግንባታዋን ለወታደራዊ ግልጋሎት እንደማትጠቀምበት የሚያሳይ ማረጋገጫ እንድታበጅ አሜሪካ ሃሳብ ስለማቅረቧ ተናግረዋል። ስቲቭ ዊትኮፍ አሜሪካ ኢራን ኑክሌር መታጠቅ እንደሌለባት ፅኑ አቋም እንደያዘች ከውይይቱ መጀመር አስቀድመው ለ‹‹ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል›› ተናግረዋል።

‹‹የኑክሌር አቅምን ለጦር መሣሪያነት መጠቀም ቀይ መስመራችን ነው›› ብለዋል። የሙስካቱ ውይይት መተማመንን ለመገንባት እንደሚጠቅም ገልፀው፣ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ግንባታዋን ለማቆም ካልተስማማች ምን መደረግ እንዳለበት የሚወስኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የ‹‹ዋይት ሃውስ›› የፕሬስ ኃላፊ ካሮሊን ሌቪት፣ ከኦማኑ ውይይት ቀደም ብለው፣ በሀገራቱ ውይይት ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያስቀመጡት እቅድ ካልተሳካ ኢራን የምትከፍለው ከባድ ዋጋ እንዳለባት በመግለፅ የአለቃቸውን ዛቻ ሲያስተጋቡ ነበር። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ በበኩላቸው ‹‹ስብሰባ ይኖራል፤ ድርድር ግን የለም›› በማለት የተናገሩት ንግግር ነጩን ቤት እና የሃሪ ትሩማን ህንፃን ያልተግባቡ አስመስሏቸዋል።

የኢራንን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት የህልውናዋ ዋና አደጋ አድርጋ የምትመለከተው የአሜሪካ ቁልፍ አጋር እስራኤልም፣ አሜሪካና ኢራን በሚኖራቸው ጥቂት የመግባቢያ መንገዳቸው ላይ መቆሟ እንደማይቀርም የብዙዎች ግምትና ስጋት ነው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You