የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላብራቶሪ መሣሪያዎች ድጋፍ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፦ ለምርምር ሥራዎች አጋዥ የሆኑ 30 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የላብራቶሪ መሣሪያዎችን በድጋፍ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ። መሣሪያዎቹ በከፍተኛ ጥራት ምርምሮችን ለማድረግ እንደሚያግዙ የሥነ-ምግብ፣ የአካባቢ ጤና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተናግሯል።

የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ ዶክተር እንዳለ አማረ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መሣሪያዎቹን የጌትስ ፋውንዴሽን በድጋፍ ሰጥቷል። መሣሪያዎቹ ጂሲ-ኤፍ አይ ዲ የሚሰኙ ሲሆኑ ሶስት የጋዝ ጄኔተሮችና ለምርምር የሚያግዙ የውሃ ማጣሪያ ሲስተሞች ናቸው።

እንደ ምርምር ክፍል ኃላፊው ገለፃ፤ የላብራቶሪ መሣሪያዎቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው እና በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚገኙ ባለሙያዎች የምግብ እና ሥነ-ምግብ ጥናትን በማካሄድ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች የሚፈቱ ናቸው። እንደ ፋቲ አሲድ ደረጃዎችን ለመለየት እና ለመተንተን የሚያገለግል ወሳኝ የትንታኔ መሣሪያ ነው።

‹‹የላብራቶሪ መሣሪያው የምግብ አይነቶች ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፋቲ አሲድ ያሉ ኦርጋኒክ ውህዶችን በመለየት እና በመለካት ረገድ ውጤታማ ነው›› ያሉት ዶክተር እንዳለ፤ የፋቲ አሲድ ክፍሎችን የመለየት ችግርን ለመፍታት በጣም ውጤታማ እና ትክክለኛ የሆኑ ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ትንተና ለመሥራት አማራጭ ይሰጣል ብለዋል።

ትንተናው የምግብ አይነቶችን በአስፈላጊ የፋቲ አሲድ መገለጫቸው ላይ በመመሥረት ለመመደብ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተው፤ በተጨማሪም መሣሪያው ትራንስ ፋቲ አሲድ ያለበትን ደረጃ ለመወሰን ጠቃሚ ነው። ትራንስ ፋቲ አሲድ ደም ወሳጅ ቧንቧዎችን የሚዘጉ ንጥረ ነገሮች የሚከሰት ሲሆን የልብ ድካም እና ሞት ተጋላጭነትን ይጨምራል። የላብራቶሪ መሣሪያዎቹ እነዚህን ችግሮች በጥራት ለመለየት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር እንዳለ ገለፃ ፤ ከመሣሪያዎቹ ጋር አብረው ከጌት ፋውንዴሽን በድጋፍ የተገኙት የጋዝ ጄነሬተሮች ደግሞ ናይትሮጅን፣ ሃይድሮጂን እና የአየር ጋዞችን ከአካባቢው በማምረት ለተለያዩ የላብራቶሪ መሣሪያዎች እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። እነዚህ የጋዝ ማመንጫዎች ውድ የሆኑ የጋዝ ሲሊንደሮችን ከመግዛትና ከከፍተኛ ወጪ ኢንስቲትዩቱን ይታደጋሉ። በአነስተኛ ወጪ የላብራቶሪ ሙከራዎችን ለማመቻቸት ይረዳሉ ብለዋል።

በላብራቶሪ ውስጥ ያለውን የውሃ ንፅህና መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር እንዳለ፣ የላብራቶሪ ሙከራዎች ትክክለኛነት በንፁህ ውሃ መኖር አሊያም አለመኖር ላይ እንደሚመሠረት አመልክተዋል።

ውሃ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል የሚሉት ኃላፊው፤ እያንዳንዱ አይነት የላብራቶሪ ምርምርና ሙከራ የተለያየ የውሃ ንፅህና ወይም ደረጃ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። ይህንን ጥራት ለማስጠበቅና የሚፈለገውን የውሃ ጥራት ደረጃ ለማግኘት በድጋፍ የተገኙት መሣሪያዎች መፍትሄ ይሰጣሉ ብለዋል።

ዶክተር እንዳለ አያይዘውም ከዳይሬክቶሬቱ ለተውጣጡ አምስት ባለሙያዎች የመሣሪያዎቹን አጠቃቀም በተመለከተ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዳይሬክቶሬቱ በድጋፍ ያገኘው ጋዝ ክሮማቶግራፊ (ጂሲ) በኬሚስትሪ ሳይበሰብስ ሊተኑ የሚችሉ ውህዶችን ለመለየት እና ለመተንተን የሚረዳ መሣሪያ ነው። የአንድን ንጥረ ነገር ንፅህና ለመፈተሽ ወይም የተለያዩ ድብልቅ ነገሮችን ለመለየት እንደ ጂሲ ዓይነት መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You