አሜሪካ ለደቡብ ሱዳናውያን የሰጠችውን ቪዛ ሰረዘች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን ለመቀበል ዳተኛ በመሆኗ ምክንያት የደቡብ ሱዳን ፓስፖርት ለያዙ የተሰጠ ማንኛውም ቪዛ መሰረዙን አስታወቁ። ሩቢዮ ሀገራቸው ማንኛውም የደቡብ ሱዳን ዜጋ ወደ አሜሪካ በየትኛውም መንገድ እንዳይገባ እንደምታግድ ተናግረዋል።

“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ዜጎቹን በወቅቱ ባለመቀበሉ” ለችግሩ ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት አዲሱ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ የተነሳ ሕገወጥ ስደተኞችን “በጅምላ ከሀገር” እያስወጡ ነው።

“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት አሜሪካን መጠቀሚያ ማድረግ የሚያቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ሩቢዮ አስጠንቅቀዋል። “አሜሪካም ሆነች ሌሎች ከሀገራቸው የሚያስወጧቸውን ሰዎች ሀገራት ወድያውኑ መቀበል ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተሰማው ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው። አሜሪካ በቀጣናው ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የካቲት 29 /2017 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ያልሆኑ ዜጎቿ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛ ነበር። ደቡብ ሱዳናውያን ቀደም ሲል በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ (TPS) ተሰጥቷቸው ለተወሰነ ጊዜ በሀገሪቱ መቆየት ይችላሉ። ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን ያወጀችው እአአ በ2011 ነው።

ነገር ግን ልክ ከሁለት ዓመት በኋላ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርታ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እኤአ በ 2018 በሁለቱ መካከል የተደረሰው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ጦርነቱን እንዲቆም አድርጓል። ነገር ግን የስምምነቱ ዋና ዋና ክፍሎች የሆኑት አዲስ ሕገ መንግሥት ማጽደቅ፣ ምርጫ እና የታጠቁ ቡድኖችን ወደ በአንድ ጦር ሠራዊት መቀላቀል የሚሉት አልተተገበሩም።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በጎሳና በአካባቢ ተወላጆች መካከል አልፎ አልፎ የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ነው። የትራምፕ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ከአሜሪካ በሚባረሩ ዜጎቻቸው ምክንያት ከመንግሥታት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።

በጥር ወር የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቻቸውን የጫኑ ሁለት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሀገራቸው እንዳያርፉ ከልክለዋል። ፔትሮ ትራምፕ በኮሎምቢያ ላይ ከበድ ያሉ ታሪፎችን እና ማዕቀቦችን ለመጣል ቃል ከገቡ በኋላ ውሳኔያቸውን አጥፈዋል ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You