
በአይነቱ ልዩ በሆነውና በተለያዩ ርቀቶች ቻምፒዮኖችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያፋልመው የግራንድ ስላም ውድድር አርብ ምሽት በጃማይካ ኪንግስተን ተጀምሯል። ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት እጅጋየሁ ታዬም የቻምፒዮኖቹን ፍልሚያ በረጅም ርቀት ድል ጀምራለች።
በሦስት ሺህ ሜትር የተወዳደረችው እጅጋየሁ አስደናቂ ብቃቷን ባሳየችበት ፉክክር 8:28.42 ሰዓት አስመዝግባ ስታሸንፍ በውድድር ዓመቱ የርቀቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር ነው። ይህም አንድ መቶ ሺህ ዶላር በሚያሸልመው ውድድር 12 ነጥብ እንድትሰበስብ አስችሏታል። ባለድሏን ተከትላ ኬንያዊቷ አትሌት አግኔስ ንጌቲች 8:28.75 በሆነ የግሏ ፈጣን ሰዓት ሁለተኛ ሆናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ ደግሞ በ8:38.15 ሰዓት ሦስተኛ ሆና በመፈፀም 6 ነጥብ መያዝ ችላለች።
አስደናቂ ፉክክር በታየበት የሴቶች ስምንት መቶ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት ድሪቤ ወልተጂ ለጥቂት ተቀድማ 1:58.29 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። አሜሪካዊቷ ኒኪ ሂልትዝ ድሪቤን በአምስት ማይክሮ ሰከንድ ቀድማ በመግባት የውድድሩ አሸናፊ ስትሆን፣ አውስትራሊያዊቷ ጄሲካ ሀል የግሏን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በ1:58.58 ሦስተኛ ሆናለች።
በወንዶች 5 ሺህ ሜትር አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት ብርቱ ፉክክር ቢያደርግም በመጨረሻ ሜትሮች ጉልበት ጨርሶ 4ኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ሃይሌ ደግሞ 7ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። አሜሪካውያኑ ግራንት ፊሸር ኮፐር ቲር እና ደይላን ጃኮብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከታትለው በመግባት በበላይነት አጠናቀዋል።
በቅርብ ዓመታት በውድድር ቁጥር ማነስ ምክንያት እየተቀዛቀዘ የነበረውን የትራክ ሩጫ ያነቃቃል ተብሎ እየተካሄደ የሚገኘው የግራንድ ስላም ውድድር በቀድሞው የአራት ጊዜ የኦሊምፒክ አሸናፊ በማይክል ጆንሰን የተመሠረተ ሲሆን፣ ውድድሩ ለአትሌቶች የመታየት እና የስፖንሰርሺፕ እድሎችን እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ ነው የተዘጋጀው። ይህም ትልልቅ አትሌቶች በተደጋጋሚ እርስ በእርስ እንዲገናኙ እድሎችን ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል።
ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች ከ100 ሜትር እስከ 5 ሺህ ሜትር ድረስ ያሉ አትሌቶች በውድድር ዓመቱ ባስመዘገቡት የተሻለ ሰዓት መሠረት ተጋብዘው ወይም በማኔጀሮቻቸው አማካኝነት የመካፈል እድል የሚያገኙበት ሲሆን፣ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በዚህ ውድድር ላይ አስቀድማ በመመዝገብ የመጀመሪያዋ አትሌት ናት።
በአጠቃላይ 96 አትሌቶች የሚካፈሉበት አዲስ የትራክ ግራንድ ስላም ሊግ በአራት ግራንድ ስላም ውድድሮች የመጀመሪያ ዓመት እስከ 12.6 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።
በእያንዳንዱ ውድድር በድምሩ 3 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ለሽልማት ቀርቧል። በሎስ አንጀለስ ከተማ መቀመጫውን ያደረገው የትራክ ግራንድ ስላም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ለውድድሩ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።
ውድድሩ በሎሳንጀለስ ፤ ኒዮርክ ፣ ጀማይካ ኪንግስተን እና በእንግሊዟ በርሚንግሃም በሚያዚያ ወር ሁለት ሣምንት እና በግንቦት ወር ሁለት ሣምንት እንደሚካሄድ ታውቋል።
በውድድር አትሌቶች በአንድ የውድድር ዘርፍ አራቱን የግራንድ ስላም ሊጎች ቢያሸንፉ 400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም