
– የሥራ ዕድል እያደገ እና እየተስፋፋ መምጣቱን ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገልጿል
አዲስ አበባ፦ በ22ኛ ዓመት ዕድሜ ደረጃ ላይ የደረሰ ወጣት በሥራ ላይ ወይም በትምህርት ገበታ ሊገኝ ሲገባ በወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት በሥራ ላይ ሆነ በትምህርት ገበታም የመሆን ዕድሉ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ እንደሚገኝ ያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ ያካሄደው ጥናት አመለከተ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ የሥራ ዕድል እያደገ እና እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጿል፡፡
ያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ እ.እ.አ በ2023-24 ባደረገው ጥናት 22 ዓመት የሞላቸው ወጣቶች የሚያገኙት የሥራ ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጿል። ለአብነትም በናሙናነት በተወሰዱ ሦስት ሺህ በሚሆኑ የ22 ዓመት ዕድሜ ወጣቶች ላይ ጥናቱ የተካሄደ ሲሆን ከእነዚህም 16 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በሥራ፣ በትምህርት ወይም በሥልጠና (NEET) ላይ አይደሉም። ይህም እ.እ.አ በ2016 በተመሳሳይ ዕድሜ ከነበረው ዘጠኝ በመቶ ከፍ ያለ መሆኑን በጥናቱ ተብራርቷል።
በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ አብዛኞቹ ወጣቶች እየሠሩ ያሉት በአነስተኛ ሥራዎች፣ ያለ ጽሑፍ ውል የተቀጠሩ እና ረጅም ሰዓት የሚሠሩ መሆናቸውን በጥናቱ ተገልጿል።
የያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ ዋና ተመራማሪ ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ሮ) የጥናቱን ግኝት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በጥናቱ ግኝት መሠረት አንድ 22 ዓመት የሞላው ወጣት ተማሪ ወይም ሠራተኛ የመሆን ዕድሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን መረዳት ተችሏል ብለዋል።
ይህም ማለት የ22 ዓመት ወጣት ጊዜውን ያለአግባብ እያጠፋ መሆኑን ያሳያል። በተለይ በአማራና በትግራይ ክልል ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤ ለዚህም ኢኮኖሚው የሚፈለገውን ያህል የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉ፣ ግጭት፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ማለፍ አለመቻል ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጉዳዩ ባለቤቶች ነን የሚሉ ሁሉ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ወጣቶች በ22 ዓመታቸው መድረስ የሚገባቸው ቦታ ላይ እንዲደርሱ ርብርብ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሕግ ዝግጅትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ባለሙያ አቶ ዳዊት ላቀው በበኩላቸው፤ ያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ በጥናቱ ለወጣቶች ያለው የሥራ ዕድል እያነሰ መጥቷል ቢልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወረዳዎች ድረስ ባለው መዋቅር የሥራ ዕድል በየዓመቱ እየሰፋ መሆኑን ያውቃል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥራ አጥ ወጣቶችን የሚመዘግብበት ሀገራዊ የመረጃ ቋት (E-LMIS) አለው። በዚህም ሥራ ፈላጊ ወጣቶቹን የማብቃትና ችሎታቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በኢንተርፕራይዝ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድሎችን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየፈጠረ ይገኛል ያሉት አቶ ዳዊት፤ በዚህም ለወጣቱ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን መረዳት ይቻላል ብለዋል።
ለአብነት በዘንድሮ በጀት ዓመት አሥር ወራት ውስጥ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ብቻ ከ341 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ይህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ምን ያህል እየሠራ እንደሆነ ያሳያል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ ሥራ ቀጣሪዎች የሚፈልጉት ክህሎት በወጣቱ ዘንድ እንዲኖር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች አቅም የማሳደግ ሥራን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሴፍ አበራ በበኩላቸው፤ እንደሀገር በትምህርት ዘርፉ ላይ ያለው ስብራት ዘርፈ ብዙ ነው። ይህም በተማሪዎች፣ በወላጆች፣ በመምህራትን እንዲሁም አጠቃላይ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋል ነው ብለዋል።
ይህንንም ለማስተካከል ኩረጃን ማስቀረት አንዱ ሥራ ነው። በዚህም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ሊቀንስ ችሏል ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ እንደሀገር የሚፈለገው የትምህርት ጥራት እውን እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ እ.እ.አ ከ2000 ጀምሮ በኢትዮጵያ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የትምህርት ሁኔታ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰባት ዙር ጥናቶች መካሄዱን ታውቋል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም