ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የ240 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ አደረገ

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ላለፉት 50 ዓመታት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የ240 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ኅብረት የ50 ዓመታት የትብብር ሂደት ውስጥ ወሳኝ ትርጉም ያለው እና ኅብረቱ በበርካታ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ጠንካራ ድጋፍ የሚያመለክት ርምጃ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የኅብረቱ የፋይናንስ ድጋፍ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተገበረች ባለችበት ወቅት የተገኘ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ልማት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

እንደሚኒስትሩ ገለፃ፤ ስምምነቱ በሙያና ቴክኒክ የትምህርት ተቋማት የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግ፣ የድህረ ግጭት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለመመለስ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የሽግግር ፍትሕንና  የፆታ እኩልነትን ለማስፈን፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም የታክስና ጉምሩክ ሥርዓቶችን በማዘመን የግሉ ዘርፍ በእሴት ሠንሠለት ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዝ ወሳኝ ድጋፍ ነው፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ድጋፎች በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ተጠቃሚ ሆናለች። እነዚህ ድጋፎች ሀገሪቱ ድህነትን ለመቀነስና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ለምናደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ አላቸው›› ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ከማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባሻገር በሰላምና ፀጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሕገ ወጥ ስደት እና በሌሎች ፖለቲካዊ ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት መሥርተው በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ከኅብረቱና ከአባል ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግም አቶ አሕመድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያና የኅብረቱ ግንኙነት በየጊዜው እየሰፋና እየተጠናከረ የመጣ ጠንካራ ትብብር መሆኑን ገልፀው፣ ይህ ግንኙነት የትብብር መስኮችን በማስፋት በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

አምባሳደሯ እንዳሉት፣ የተፈረመው ስምምነትም ከኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ እና ከአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት እቅድ ጋር የተጣጣመ ነው። የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነቱ በኅብረቱና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን በወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆች ላይ የተመሠረተውን ጠንካራ ትብብር የሚወክል ነው።

ኢትዮጵያ በበርካታ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች፣ በተለይም በግብርናው ዘርፍ፣ ጠንካራና ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቁመው፣ ኅብረቱ የሀገሪቱን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት እንዲያስመዘግብ ኅብረቱ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እየደገፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You