የተገኙ ስኬቶችን በፈተና ውስጥም ሆኖ ማስቀጠል ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያን ብልፅግና ማማ ለማድረስ የሚታዩ ጅምር ሀገራዊ ስኬቶችን በፈተና ውስጥም ሆኖ ማስቀጠል እንደሚጠበቅ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሥዩም መኮንን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ከለውጡ በኋላ የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ “ትላንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል ትናንትና በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ለውጥ ከመጣና ብልፅግና ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ፈተናዎች የገጠሙ ቢሆንም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲ አበረታች ውጤቶችን ለማስመዝገብ ተችሏል።

በሀገሪቱ ከነበሩ የፖለቲካ ስብራቶች መካከል ዋነኛው የነጠላ ትርክት መሆኑን አውስተው፤ ይህንን ለማስቀረት ባለፉት ሰባት ዓመታት አስተሳሳሪና ብሔራዊ የወል ትርክት ለመገንባት በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ችግሩ የቆየና የተወሳሰበ በመሆኑ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

በተጨማሪ ቀደም ሲል በፖለቲካው መስክ የመጠላለፍ የመጠፋፋት አካሄድ መኖሩን አንስተው፤ ይህ ኋላቀር የፖለቲካ ልምድ ለመቀየር በተሠራው ፈርጀ ብዙ ሥራም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በመንግሥት ሥልጣን እንዲያገኙና አካታችነትም እንዲኖር መደረጉን በአብነት ጠቅሰዋል። ይህም አዲስ የፖለቲካ አካሄድ ለመጀመር ያስቻለም እንደሆነም አመልክተዋል።

ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣ እንደ ምርጫ ቦርድና ዕንባ ጠባቂና መሰል የዲሞክራሲ ተቋማት በገለልተኝነት እንዲመሩ ማድረግ መቻሉ በፖለቲካዊ ዘርፉ ከተገኙ ለውጦች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ኢኮኖሚ ዘርፉም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድንና በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፤ በግብርናው መስክ በመካናይዜሽን ግብርና መስፋፋት፤ በበጋ ስንዴ ልማት፤ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርናና በእንስሳት ልማት የተገኙ ውጤቶችን ጉልህ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በከተማ ልማት ረገድም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች እየተካሄዱ ያሉ የኮሪዶር ልማቶችና የገጠር ኮሪዶር ልማት ውጤቶች የለውጡ ትሩፋት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂው መስክም በዲጂታል ፋይናንስና በሰው ሠራሽ አስተውሎት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መሠረት የጣሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ ሁሉ ውጤቶች ሊመዘገቡ የቻሉት እንደ ኮሮና፤ የሰሜኑ ጦርነት ያሉ ትልልቅ ተግዳሮቶች በነበሩበት ወቅት መሆኑ በቀጣይ በርትተን ከሠራን ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል አመላካች ነው ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You