ቆሻሻን ወደ ሀብት የመለወጡ ሥራ ከሁለት በመቶ ወደ 12 በመቶ አደገ

አዲስ አበባ፡- ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ወደ ሀብት የመለወጡ ሥራ ከሁለት በመቶ ወደ 12 በመቶ ማደጉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለፁ::

ሥራ አስኪያጁ “ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያችን ልዕልና” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን ባዘጋጀው የፅዳት ንቅናቄ መርሐ ግብር ላይ እንዳሉት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቆሻሻ ወደ ሀብት ለመቀየር በተደረገው ጥረት ከለውጡ በፊት ከነበረው ሁለት በመቶ ወደ 12 በመቶ ማሳደግ ተችሏል::

በተለይም ከተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ልማት ጋር ተያይዞ የተጀመረው ንቅናቄ በጅምር እንዳለ ጠቁመው፤ ይህን ሥራ አጠናቀን ሙሉ በሙሉ መተግበር ሲቻልም በተጨባጭ ቆሻሻን ሀብት ይሆናል ብለዋል::

ለዚህም ሁላችንም በጋራ መወጣት ያለብን ድርሻ አለ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የምንፀየፈው ቆሻሻ ሀብት መሆን እንዲችል እያንዳንዳችን ከቤታችን ሲወጣ ለይተን ማስቀመጥ አለብን ሲሉ አስረድተዋል:: ይህን ማድረግ ከቻልን የሚበሰብሰው ወደ ኮምፖስት ጣቢያዎች፤ መልሰን ጥቅም ላይ ልናውል የምንችለውን ደግሞ ወደ ሪሳይክሊንግ ጣቢያዎች በመውሰድ ጥቅም ላይ መሆኑን ጠቁመዋል::

ዜጎች ከዚህ ሀብት ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ኑሯቸው የሚቀይሩበት ሥራ መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፤ ይህም አዲስ አበባ በዘላቂነት ፅዱና አረንጓዴ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን አስረድተዋል::

ሁላችንም ቆሻሻን ከምንጩ የመለየት ሥራችን ላይ አጠናክረን መሥራት ይኖርብናል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ከቤታችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከቤታችን አካባቢ በሃያ ሜትር ሬዲየስ በድርጅት አካባቢ ደግሞ በሃምሳ ሜትር ሬዲየስ ያለውን ቦታ ማፅዳት መቻል እንዳለበት ጠቁመዋል:: ይህን ማድረግ ሲቻል በተጨባጭ አዲስ አበባን የአፍሪካ እንዲሁም የዓለም የፅዳት ተምሳሌት ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል::

አሁን ባለንበት ሁኔታ ለብዙ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የፅዳት፣ የንጽሕናና የብልፅግና ተምሳሌት መሆን እንደምንችል ብርሃን ያሳየንበት ተስፋን የፈነጠቅንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ሲሉ አመልክተዋል:: ይህንን በተሟላ መልኩ ሁላችንም በየራሳችን ቤት ተግብረንና ከማንነትና ከባህላችን ጋር አስተሳስረን ስንሠራ ይህ ከተሞችንና ወንዞችን ንጹሕና ሳቢ የማድረግ ሥራዎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል::

ሁላችንም በርትተን ከሠራን ከተማዋ የጀመረችውን ጉዞ ማዝለቅ የምትችል መሆኑን አይተናል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ልዩ ተስፋና ጊዜን ይዞ የመጣ መሆኑን ገልፀዋል::

በተለይም በወንዝ ዳርቻዎቻችን ፅዳት ወንዞች ወደ ተፈጥሯዊ ማንነታቸው የሚመለሱበት ጊዜ መጥቷል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሁላችንም ከየቤታችን የሚወጣውን ፍሳሽ ንፁሕ በማድረግ በተሟላ መልኩ ፅዳቱን ማስቀጠል ይኖርብናል ሲሉ አስረድተዋል:: ይህ ሥራ እውን እንዲሆን ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You