
– አቶ ፈጠነ ተሾመ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እያገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ እንደሚያሳይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ አስታወቁ፡፡ 300 የነበረው ዘመናዊ የአየር ጠባይ መመዝገቢያ አውቶማቲክ መሣሪያዎች ቁጥርን በቅርቡ ወደ 507 ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን አመለከቱ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፈጠነ፣ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ከየካቲት እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም ባሉት ወራት የበልግ ወቅት የሚኖረው ዝናብ መደበኛም ከመደበኛ በላይም ነው፡፡ አጠቃላይ በመደበኛ ሁኔታ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ሲሆኑ፣ እነዚህ አካባቢዎች ዓመቱን ሙሉ ማለትም እስከ ስምንት ወራት ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ናቸው፡፡ የተተነበየውም ጥሩ የዝናብ ወቅት እንደሚኖራቸው ነው ብለዋል፡፡
አቶ ፈጠነ እንደገለጹት፤ ዋናው ነገር ኢንስቲትዩቱ ትንበያ ከሰጠ በኋላ በየመሃሉ ማለትም በአስር ቀን፣ በየወሩ የሰጠውን ትንበያ እያሻሻለ ይሄዳል። በአሁኑ ወቅት የተተነበየው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ነው፡፡ ሌሎቹ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያ ተሰጥቷል፡፡
የተወሰኑት የደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ተተንብይዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጥቅሉ በበልግ ወቅት የሚጠበቀው ዝናብ እየተገኘ ነው ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በልግ ከየካቲት እስከ ግንቦት ድረስ ያሉ ወራትን የያዘ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የበጋ ወቅት ደግሞ ከጥቅምት እስከ ጥር፣ የክረምት ወቅት ደግሞ ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉትን ወራት የሚያካትት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ፈጠነ እንዳሉት፤ እነዚህ ወቅቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተለያየ እንድምታ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በማዕከላዊ አካባቢ ክረምት ሁልጊዜ ዝናብ ነው። በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አካባቢዎች ግን ክረምት ደረቃማ ነው፡፡ ይህ ማለት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ደቡብ ኦሮሚያ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ የባሌ ቆላማ ዞኖች በልግ ዋንኛ የዝናብ ወቅታቸው፤ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው፡፡
በክረምት ወቅት እነርሱ ዘንድ ዝናብ የሚጠበቅ አይደለም። ቢዘንብ እንኳ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተብሎ የሚፈረጅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍል፣ ከመካከለኛ አጋማሽ ጀምሮ ያሉ አካባቢዎች ደግሞ ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው እንደሆነ አመልክተው፤ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው። አሁን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚዘንበው ዝናብ እና የበልግ ዝናብ ለእኛ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታችን ነው ብለዋል።
ዝናቡ ለእርሻውም ለእንስሳቱም አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተው፤ ይሁንና ዋነኛ የዝናብ ወቅታችን አይደለም። ለምሳሌ የምስራቅ አማራ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የምስራቅ ትግራይ አካባቢዎች በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው፡፡ በክረምቱም ወቅት ዝናብ ያገኛሉ። ደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግን በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ሲሆን፣ በጋ ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው ብለዋል፡፡
አሁን ባለንበት ወቅት ለምሳሌ ቦረና እና ሶማሌ ዝናብ ማግኘት ያለባቸው ክልሎች እንደሆኑ አመልክተው፤ አሁን ባለንበት ጊዜ ዝናብ የማያገኙ ከሆኑ ዝናብ ለማግኘት የሚጠብቁት በቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ይሆናሉ፡፡ አሁን ዝናብ አላገኙም ማለት በቀጣዩ ዓመት የድርቅ ችግር ሊያደርስ ይችላል፡፡ ከብቶቻቸውም ጉዳት ይደርስባቸዋል ነው ያሉት፡፡
አቶ ፈጠነ እንዳሉት፤ በልግ እንደ ወቅት ለትንበያ የሚያስቸግር አይነት ሁኔታ አለው፡፡ ምክንያቱም ካሉት ወቅቶች ውስጥ የሚዋዠቅ ሁኔታ የሚታይበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡
ተቋሙን ይበልጥ እያዘመንን እንገኛለን ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፈጠነ፣ በሰው ኃይል ይሰበሰብ የነበረው የአየር ጠባይ መረጃ ወደ ዘመናዊ አውቶማቲክ መሣሪያ እየተተካ ይገኛል ብለዋል፡፡
እስካሁን የተከናወነው 300 ይሁን እንጂ ወደፊት የሚቀጥል እንደሆነ ጠቁመው፤ ቁጥሩን ወደ 507 ከፍ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡
መሣሪያው በውጭ ምንዛሪ የሚመጣ እንደመሆኑ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፤ በተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ ነን ያሉት አቶ ፈጠነ፤ በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወነው የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት መሠረት ወደ አንድ መቶ ተጨማሪ አውቶማቲክ መሣሪያ ግዥ ለማከናወን በሒደት ላይ ነው። በዚህም ጨረታ ወጥቶ ተጠናቅቋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሀገር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በሌላ ፕሮጀክት ደግሞ ከመስኖ እና ቆላማ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ አርብቶ አደር አካባቢ 107 ተጨማሪ መሣሪያዎችን ለመትከል መታቀዱን አመልክተው፤ በቅርቡ ከ300 ወደ 507 ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ እተሠራ ነው ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም