የግብርናው ማርሽ ቀያሪ ፋብሪካ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአመዛኙ በግብርና ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ዘርፉ ዛሬም ድረስ ከኋላ ቀር አሠራር ተላቅቆ ለሀገር እድገት ማበርከት ባለበት ልክ ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑ የሚያስቆጭ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብሩ ይፋ ከሆነ በኋላ ግብርና ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ እየተሠራበት መሆኑን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያወጣና ከፍተኛ ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት‹‹ከሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ቀጣዩ ፕሮጀክታችን የማዳበሪያ ፋብሪካ መትከል ነው›› ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።በሀገራችን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መተከሉ ምን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል? ስንል ምሁራንን አነጋግረናል።

የሆርን ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ፕሬዚዳንት እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የእርሻ ምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ሚልኬሳ ወቅጂራ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ የኢትዮጵያ ግብርና ለረጅም ጊዜ ዘመናዊነት ያልጎበኘው በመሆኑ የሚጠበቅበትን ያህል ለሀገር አስተዋጽኦ እያበረከተ አልመጣም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአርሶ አደሩን ሕይወት የመለወጥ አቅም እንኳን አላጎለበትም፡፡ ግብርናችን የሚከተለው ኋላ ቀር አሠራርን በመሆኑ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥም አልቻለም፡፡

እንደዚህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ግብርና በአሁኑ ጊዜ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጥቅል ሀብት 36 በመቶ፣ በሥራ እድል ፈጠራ 80 በመቶ፣ በውጭ ምንዛሪ 83 በመቶ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጥናቶች ማመላከታቸውን ይጠቅሳሉ። ቀደም ሲል ከነበረው ኋላ ቀር አሠራር ለመውጣት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማነቷ እያደገ ፤ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችም እየታዩ መጥተዋል ይላሉ ሚልኬሳ ወቅጂራ (ዶ/ር)።

መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የመገንባት እቅድ መያዙም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ ወሳኝ ርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ እና የኢኮኖሚክስ መምህር ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው ግብርና መር ፖሊሲ እንደመሆኑ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት የነበራት ከደርግ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ከዚያም ወዲህ በኢህአዴግ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ተጀምሮ ለውጤት ሳይበቃ በእንጭጩ እንደቀረ ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ እያራመደች እስከ አሁን ለምርታማነት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ያለመገንባቷ ትልቅ ስህተት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ከግብርና ሥራ ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ ጉዳይ በተጠቃሚው ዘንድ ሮሮ የሚበዛበት ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ የተናገሩት ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)፤ ፋብሪካውን ገንብቶ የአርሶ አደሩን ጥያቄዎች መመለስ እና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማስቀረት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ይፈጥራል ብለዋል።

ማዳበሪያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ ፕሮጀክቱ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊገነባ ይገባዋል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ግብርናውን ለማዘመን እና የግብርና አቅሞችን ለማሳደግ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ እያደረገ ያለው ንቅናቄና እየተገበረ ያለው ሥራ በሽግግር ወቅት ላይ እንዳለን የሚሳይነው የሚሉት ሚልኬሳ ወቅጂራ (ዶ/ር) ከእነዚህም፣ የማዳበሪያ፣ የብድር እና የምርጥ ዘር አቅርቦትን፣ የኩታ-ገጠም እርሻን ፤ የባለሙያ ድጋፍና ክትትልን፣ የመስኖ ልማትን፣ የሜካናይዜሽን እርሻን፣ የጸረ-አረምና ጸረ-ተባይ መድሃኒቶች አጠቃቀምን፣ የገበያ ትስስርን እንደጥሩ ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል ይላሉ።

እንደሶማሌ እና አፋር ክልል ያሉ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶች በግብርና ልማት እንዲካተቱ፤ በተለይም ለመስኖ ልማት እንዲውሉ መደረጉ መንግሥት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያሳይ ሌላው አዲስ ልምምድ እንደሆነም ይገልጻሉ።

የሀገሪቱን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ ከሆኑ ግብዓቶች አንዱ የአፈር ማዳበሪያ ነው ያሉት ሚልኬሳ ወቅጂራ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እያደረገች የአፈር ማዳበሪያ እንደምታስገባም ይጠቅሳሉ፤ በሁለት ዓመት የምትፈጽመው የማዳበሪያ ግዢ ሲደመር እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ጠቁመው፤ ይህም የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት እንደሚያስችላት ይናገራሉ፡፡ ለማዳበሪያ ፋብሪካ የሚውሉ ግብዓቶችም በአፋር፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች እንደሚገኙ የሚያመላክቱ ጥናቶች ስለመኖራቸውም ይጠቅሳሉ።

ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ግብርናው ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ የውሃ ሀብት እየተጠቀመ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወቅት የማዳበሪያ ፋብሪካን መገንባት ትርጉም ያለው  ለውጥ የሚያመጣ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።በየዓመቱ ሀገሪቱ ያላትን የውጭ ምንዛሪ እየሰበሰበች ለማዳበሪያ መግዣነት ማዋሏንም ያስቀራል ይላሉ።

ልክ እንደማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ሁሉ የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን እንዴት መጠቀም እንዳለበት፤ ከዝናብ ውጭ በበጋ ወቅት እርጥበታማ መሬትን እንዴት ተጠቅሞ ማምረት እንደሚገባው፤ ግንዛቤ በመስጠትም ሆነ ሠርቶ በማሳየት ነባሩን አስተሳሰብና እና አሠራር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ሲያገኙ ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥም አልፋ ከራሷ የሚተርፍ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያስቻላታል ይላሉ።

ሚልኬሳ ዋቅጂራ (ዶ/ር) ፤ ይህንኑ ሃሳብ ሲያጠናክሩ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ማምረት ቢቻል፤ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረትም በዘለለ ምርቱን ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል፤ አርሶ አደሩም ግብዓቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘ በወቅቱ በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደግ ይችላል። ሕብረተሰቡ ልክ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ሊገነባ በታሰበው የማዳበሪያ ፋብሪካ ላይ ርብርብ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይኖርበታልም ነው ያሉት።

ሞላ አለማሁ (ዶ/ር) ፕሮጀክቶች አስፈላጊነታቸው ታምኖበት፣ ዲዛይን ከወጣላቸውና በጀት ከተያዘላቸው፤ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በጀታቸው ለሌላ ነገር እየዋለ የሚቋረጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ አሁን እየታየ ያለውን ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ልምድን ተግባራዊ በማድረግ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ለውጤት በማብቃት የግብርናውን ምርታማነት ማሳደግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን እንደማይገባው ያስረዳሉ።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You