ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው

በአውሮፓ እግር ኳስ የገነነ ስም ካላቸው ቡድኖች መካከል የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን አንዱ ሲሆን፤ የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ ተጫዋቾች ቁጥር ሚዛኑን ይደፋል፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአውሮፓ ዋንጫ ተሳታፊ ከነበረው ቡድን 14ቱ ፈረንሳዊ የሆኑት በዜግነት ብቻ ነው፡፡ ይኸው ሁኔታ በተለይ በአውሮፓ የተለመደ ሲሆን፤ በቻምፒዮናው በተሳተፉት 7 ቡድኖች ውስጥ 49 ተጫዋቾች ትውልዳቸው አሊያም የቤተሰቦቻቸው መነሻ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በአንጻሩ በአፍሪካ የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላቸው ሀገራትም ከተጫዋቾቻቸው መካከል በአውሮፓ ተወልደው ነገር ግን የቤተሰቦቻቸውን ሀገር የመወከል ፍላጎት ያላቸውን ተጫዋቾች ያካተቱ ናቸው፡፡ በስፔን ተወልዶ ቢያድግም የቤተሰቦቹን ሀገር በመምረጥ ለሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የሚጫወተው ኮከብ አሽራፍ ሃኪሚ እንዲሁም ከተወለደባት ፈረንሳይ ይልቅ ሴኔጋልን የመረጠው ምርጡ ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ ለማሳያ የሚጠቀሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች አንድም በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሠረት በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸው ፍላጎት መነሻቸው የሆኑ ሀገራትን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ይወክላሉ፡፡

በሌላ በኩል የእግር ኳስ ስፖርት ተወዳጅነትን ያህል ስኬታማ ያልሆነችው ኢትዮጵያ፤ በውጪ ሀገራት ተወልደው ያደጉና የእግር ኳስ ክህሎታቸው የተመሰከረላቸውን ተጫዋቾች አለማካተቷ አሁንም ድረስ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የመሰለፍ ፍላጎት እያላቸው ላለመጫወታቸው ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥምር ዜግነት አለመፍቀዱ ነው።

ለዚህ ተብሎ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ከባድ በመሆኑ መሰል ሕግ ያላቸው ሀገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፊፋ የስፖርት ፓስፖርትን እንደ አማራጭ ማስቀመጡ ይታወቃል። ያም ሆኖ የስፖርት ፓስፖርት በራሱ ውስብስብ ሂደቶች ያሉት በመሆኑ ለኢትዮጵያ አሁንም ድረስ መጥቀም አልቻለም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበት መንገድ በሙሉ ዝግ አይደለም።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ይህንኑ ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ያነሳ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ መሬት ወርዶ መታየት አልቻለም። ከሰሞኑ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር ተያይዞ በሰጠው መግለጫ ላይም ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን፤ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጋር ባለው ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይና በሌሎች መንግሥታዊ አካላት የሚከናወን እንደመሆኑም በዚህ ጊዜ ይጠናቀቃል ማለት አይቻልም፡፡ በርካታ አፍሪካውያን ሀገራት አሠራራቸውን በመቀየራቸው ደካማ የነበረው ብሄራዊ ቡድናቸው ተፎካካሪ ወደመሆን ተሸጋግረዋል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም እንደ ሞዛምቢክ፣ ኮሞሮስ ያሉ ሀገራት ትውልዳቸው ባህር ማዶ የሆኑ ተጫዋቾችን በማሰለፋቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያም በሌሎች ሀገራት ሊጎች የሚካፈሉ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ያሏት ከመሆኑ አንጻር ተመሳሳይ አካሄድ ለመከተል እንደሚያስፈልግ ሲነገር ቆይቷል። ፌዴሬሽኑም ከሁለት ዓመታት በፊት ይህንን ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ስፖርቱን ከሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ የሚገኝ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፊፋ ጋር አስፈላጊውን ሂደት መጨረስ እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማስፈጸምም ፌዴሬሽኑ ስፔን ካሉ የስፖርት ሕግ ባለሙያዎች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ይሁንና ከመንግሥታዊ ተቋሞቹ በፍጥነት መልስ ከማግኘት አንጻር አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውንም ነው የጽህፈት ቤት ኃላፊው ያብራሩት፡፡

ከዚህ ቀደም ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አሜሪካ ተጉዞ በፊፋ ያልተመዘገቡ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ባደረገበት ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድኑ ለማሰለፍ ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ በቅርቡም በአውሮፓ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት ማህበር ጋር በተደረገ ንግግር በርካታ ወጣቶች ለኢትዮጵያ መጫወት እንደሚፈልጉ ፌዴሬሽኑ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ እነዚህን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችም በሀገር ውስጥ ካሉ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች ጋር በማድረግ ተፎካካሪ መሆን የሚችል ቡድን መገንባት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይኸው የትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጉዳይ በቶሎ እንዲጠናቀቅና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው ፌዴሬሽኑ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You