ከኩረጃ ባሻገር የሚታዩ እንከኖች

ባለፉት ሶስት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ የሚታወስ ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት እንደ ምክንያት ሲነሳ የነበረው የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን በመቀየር ኩረጃን ማስቀረት መቻሉ እንደሆነ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በጉዳዩ ዙሪያ አደረኩት ባለው ጥናት እንደተመላከተው ኩረጃ ብቻውን ለውጤቱ ማሽቆልቆል ምክንያት አይደለም ይላል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የጥናቱን ግኝት በተመለከተም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ እንደገለፁት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለሁሉም ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። ነገር ግን የትምህርት ሥርዓቱ የፈተና አስተዳደር ሂደት ብልሹነትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች እየተፈተነ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡

በተለይም በ2014 ዓ.ም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ላይ ጉልህ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በዩኒቨርሲቲ መምህራን ቁጥጥር መሰጠት መጀመሩን አስታውሰው፤ የሀገር አቀፍ ፈተና አሠጣጡ መለወጡን ተከትሎ የተገኘው የትምህርት ውጤት ደካማ እንደሆነ አውስተዋል።

በተለይም በ2014 እና በ2015 ከሃምሳ በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 3 ነጥብ 2 እና 3 ነጥብ 3 በመቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የፈተናው ውጤት ተለዋዋጭነትና አንድምታ ጥልቅ ምሁራዊ ጥናት የሚፈልግ መሆኑን ገልፀው፤ ጥናቱ የተካሄደው የፈተና አስተዳደር ሂደቱን አስተዋጽኦና ክፍተት በመገምገም የትምህርት ቤት ልማቶችን፣ የመምህራን ድጋፍ ሥርዓትን፣ የተማሪዎች ተነሳሽነት በመዳሰስ እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን በመተንተን መሆኑን ጠቁመዋል።

የጥናት ውጤቱ እንደሚያሳየው አዲሱ የፈተና አስተዳደር የፈተና ጉድለቶችን በመቀነስ፣ በራስ መተማመንን በማጎልበት፣ የትምህርት ተሳትፎን በማነሳሳት፣ ማህበራዊ መስተጋብርን በማሳደግ የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የተማሪዎችን እውቅናና የመምህራንን ስም በማሳደግ እንዲሁም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን አንጥሮ በመለየት ረገድ የተሳካለት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፣ በተማሪዎች ላይ የሥነልቦና ተፅዕኖ፣ የሀብት ውስንነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና የተደራሽነት እጦት ጥቂቶቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለውጥን መቋቋም አለመቻል የቴክኒካልና መሰል አስተዳደራዊ ጉዳዮች ከአዲሱ አሠራር ጋር የመላመድ ችግር፣ የትምህርት ክትትልን በመቀነስና በፈተና ላይ ብቻ በማተኮር የትምህርት ጥራትን ችላ ማለትን ጨምሮ የቴክኖሎጂና የመማሪያ መረጃዎች ላይ ውስንነት መኖሩ በጥናቱ መለየቱን ጠቁመዋል፡፡

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ደሳለኝ አንሺሾ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጥናቱ የፀጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች ውጪ ያሉትን የሀገሪቱ አካባቢዎች ማካተቱን ገልፀዋል፡፡ አስር ዓመት ወደ ኋላ የነበሩ የሀገር አቀፍ ፈተና ውጤቶች በጥናቱ መዳሰሳቸውንም አስረድተዋል፡፡

በተለይም ምንም ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ ያልቻሉ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በቅርብ ጊዜ ማስተማር የጀመሩና ብዙ ልምድ የሌላቸው መሆናቸው እንደ አንድ ምክንያት በጥናቱ መመላከቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ሰላሳና አርባ ዓመት በማስተማሩ ልምድ ያላቸው ደግሞ ሃያና ሰላሳ ተማሪ ማሳለፍ መቻላቸውን ገልፀዋል።

ጥናቱን ከጀመሩ ጀምሮ ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በጋራ ሲሠሩ እንደነበር ገልፀው፤ በጥናቱ የተካተተውን የአስር ዓመት ሰነድም ያገኙት ከኤጀንሲው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሄዱባቸውንም ትምህርት ቤቶች የሚመለከት መረጃ የሚያገኙት ከኤጀንሲው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ የፈተና አሰጣጥ ኩረጃ መቀነሱ እንዳለ ሆኖ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦና ጫና መፍጠሩ አንዱ የጥናቱ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የሥነ ልቦና ጫናው ተማሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አካባቢ ከመምጣታቸውና ከአዲሱ አካባቢ ጋር ባልተላመዱበት ሁኔታ ወደ ፈተና ከመግባታቸው ጋር እንደሚያያዝ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በቀደመው ዓመት የተፈተኑ ተማሪዎችን ውጤት በማስታወስ ውጤት አላመጣም የሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደሚገቡ ነው የተናገሩት። ተምረው ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ሥራ አጥ መሆን እንዲሁም ሥራ ኖሯቸው አመርቂ ደመወዝ አለማግኘት ትምህርት ላይ ያላቸውን ተስፋ እያሳጣ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ቴክኖሎጂ ተኮር ሥርዓቶችን መከተል፣ መምህራን ላይ መሥራት፣ ተማሪዎችን ለፈተና ስናዘጋጅ ሥነልቦናዊ ድጋፍ ማድረግና የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከታች ጀምሮ መሥራት እንደሚገባ በጥናቱ ምክረ ሃሳብ ላይ ተመላክቷል፡፡

ነጻነት አለሙ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You